የአማራ ክልል ለተሰናባች የመከላከያ ሰራዊት አባላት ጥሪ አቀረበ

በተስፋለም ወልደየስ

የአማራ ክልል መንግስት ከመከላከያ ሰራዊት በተለያየ ምክንያት የተሰናበቱ አባላት፤ የክልሉን የጸጥታ ኃይል እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቀረበ። ክልሉ ለሰራዊቱ አባላት ጥሪ ያቀረበው የሕወሓት ኃይልን “ስርዓት ለማስያዝ እና ህግ ለማስከበር” እወስደዋለሁ ባለው “ጥቃት” ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ነው። 

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ዛሬ ጠዋት በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት የክልሉ መንግስት የሕወሓትን ኃይል “ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ” ከፌደራል መንግስት ጋር ተባብሮ የሚሰራ ይሆናል። ይህንን ተግባራዊ ለማድረግም ከክልሉ አጠቃላይ የጸጥታ ኃይሎች በተጨማሪ ተመላሽ የሰራዊት አባላትም የዘመቻው አካል እንዲሆኑ ጠይቀዋል።      

“ከሰራዊት በተለያየ ምክንያት ተገፍተው በነበረው ስርዓት የተመለሱ ምልስ የሰራዊት አባላትም በዚህ አጋጣሚ የክልሉ መንግስት ጥሪ አቅርቧል። [አባላቱ] ወደ ሰራዊት ተቀላቅለው፤ እስካሁን ሲያሸብር እና ሲያስቸግር የነበረን ኃይል ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ስርዓት ማስያዝ እንዳለብን በዚህ አጋጣሚ ጥሪ ማስተላለፍ እፈልጋለሁ” ሲሉ ርዕሰ መስተዳድሩ በክልላቸው ቴሌቪዥን ጣቢያ በተላለፈ መግለጫቸው አስታውቀዋል።  

የትግራይ ክልልን እያስተዳደረ የሚገኘውን ሕወሓትን “የአማራ ህዝብ ስትራቴጂክ ጠላት” ሲሉ የጠሩት አቶ ተመስገን፤ በድርጅቱ “ዘራፊ፣ ሌባ፣ የተተፋ እና የተገፋ ኃይል” ሲሉ ገልጸውታል። ሕወሓት በመከላከያ ሰራዊት እና በክልሉ ላይ “ጦርነት ከፍቷል” ሲሉም ወንጅለዋል።

ጦርነት መቀስቀሱን በቅድሚያ ይፋ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም በተመሳሳይ መልኩ ሕወሓትን ለጥቃቱ ተጠያቂ አደርገዋል። በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ከንጋት ጀምሮ በተደጋጋሚ የተላለፈው የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ፤ በትግራይ ክልል መቀሌን ጨምሮ በተለያየ አካባቢ ባለው የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት መሰንዘሩን አመልክቷል።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተሻለ ዝርዝር መረጃዎችን የያዘው የአቶ ተመስገን መግለጫ፤ በሰሜን ዕዝ በሚገኙ በመከላከያ ሰራዊት ካምፖች እና ዲፖዎች ላይ ጥቃት የተሰነዘረው ከምሽቱ አራት ወይም አምስት ሰዓት ገደማ ጀምሮ እንደነበር ጠቁሟል። የትግራይ ልዩ ሃይል እና ሚሊሺያ በተቀናጀ መልኩ ተፈጸሟል የተባለው ይህ ጥቃት የተለያዩ የመሰረተ ልማት ያሉባቸው አካባቢዎችን መሸፈኑንም መግለጫቸው ጠቅሷል።

“ሰራዊታችን በሚሊሺያ እና በልዩ ሃይሉ ከበባ ውስጥ የነበሩ የተወሰኑ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ማዳን እና ከውስጥ ማውጣት ችሏል። አንዳንድ ከባድ መሳሪያዎችን እንደዚያው ወደ እኛ ማውጣት ችለናል” ሲሉም የአማራ ክልል ልዩ ኃይል የወሰደውን እርምጃ አብራርተዋል።   

በመከላከያ ሰራዊት ደረሰ ከተባለው ጥቃት በተጨማሪ በአማራ ክልል በዳንሻ በኩልም ጥቃት መፈጸሙን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ተናግረው ነበር። በአማራ ክልል ላይ ጥቃት መድረሱን ያረጋገጡት የክልሉ ርዕስ መስተዳደር፤ ሁኔታውን “የውጊያ ሙከራ” ሲሉ ገልጸውታል። ጥቃቱ የተፈጸመው ሶሮቃ እና ቅራቅር በተባሉ አካባቢዎች መሆኑን የጠቀሱት አቶ ተመስገን፤ እርሱንም ቢሆን የክልሉ ልዩ ኃይል “መክቷል” ብለዋል። 

የጠገዴ ወረዳ ዋና ከተማ በሆነችው ቅራቅር አጠገብ ከለሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ “ጦርነት” እንደነበር የወረዳ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዩች ጽህፈት ቤት አስታውቋል። ጽህፈት ቤቱ ዛሬ ረፋዱን በፌስ ቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ፤ በጦርነቱ ምክንያት ቅራቅር ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎች “ቤታቸውን እየለቀቁ በመውጣት ላይ ናቸው” ብሏል። “የአካባቢውን ህዝብ ለማዳን የክልሉ ልዩ ኃይል እና ሚሊሺያ ወደ ጦርነት ለመግባት መገደዱንም” ጠቅሷል። በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ተጨማሪ የጸጥታ ኃይል በፍጥነት ወደ አካባቢው እንዲሰማራም ወረዳው ጥያቄ አቅርቧል።  

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በበኩላቸው የክልሉ አጠቃላይ የጸጥታ ኃይል በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ተንቀሳቅሶ እንዲመከት ከዛሬ ጀምሮ መታዘዙን አስታውቀዋል። ከመከላከያ ሰራዊት በጋራ የተዋቀረ ኮማንድ ፖስት እንዳለ የጠቆሙት አቶ ተመስገን፤ ከኮማንድ ፖስቱ በሚሰጣቸው ትዕዛዝ የክልሉ ልዩ ሃያሎች፣ ሚሊሺያዎች እና መደበኛ ፖሊስ እንደሚሰማሩም ተናግረዋል። 

“በኮማንድ ፖስቱ ትዕዛዝ መሰረት በሚኖር ስምሪት በየትኛውም አካባቢ ላይ የሚደርስን ጥቃት መከላከል የሚያስችል ቁመና አለን። ይሄንን አቀናጅተን እና አስተባብረን ጠላታችንን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ መደምሰስ የሚያስችል ስራ መስራት አለብን” ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ ተደምጠዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)