የአውሎ ሚዲያ ዋና አዘጋጅ በቃሉ አላምረው ዛሬ ረቡዕ ጠዋት በአዲስ አበባ ከሚገኘው መስሪያ ቤቱ በፖሊሶች ተይዞ መወሰዱን የስራ ባልደረቦቹ ተናገሩ። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የደንብ ልብስ የለበሱት ፖሊሶች፤ ሶስት ላፕቶፖችን ጨምሮ መገናኛ ብዙሃኑ ለስራ የሚጠቀምባቸውን ቁሳቁሶችን ከጋዜጠኛው ጋር አብረው መውሰዳቸውን አስታውቀዋል።
ስሙ እንዳይገለጽ የጠየቀ አንድ የአውሎ ሚዲያ ባልደረባ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደገለጸው፤ ዋና አዘጋጁ የተያዘው የመገናኛ ብዙሃኑ በየዕለቱ ጠዋት በዩቲዩብ ቻናል የሚያቀርበውን ዜና ለመስራት ጠዋት ሁለት ሰዓት ገደማ ወደ ቢሮ በሚገባበት ወቅት ነው። በወቅቱ ከጋዜጠኛው ጋር አብረው የነበሩት የድርጅቱ ሹፌር እና ጸሀፊ ስልኮቻቸውን ተቀምተው፣ በቢሮ ውስጥ ከእርሱ ጋር እንዲቆዩ ተደርገው እንደነበርም አስረድቷል።
በቁጥር ሶስት የሆኑት ፖሊሶች ቦሌ መድኃኒያለም ቤተክርስቲያን አጠገብ በሚገኘው አውሎ ህንጻ ላይ በሚገኘው የመገናኛ ብዙሃኑ ዝግጅት ክፍል፤ ፍተሻ ሲያካሄዱ መቆየታቸውን ቦታው ላይ ከነበሩ ሰዎች መስማቱን የድርጅቱ ጋዜጠኛ ገልጿል። ፖሊሶቹ የፍርድ ቤት ትዕዛዝም ሆነ መታወቂያ አለማሳየታቸውን “የዓይን እማኞች ነግረውኛል” ብሏል።
በቃሉ በቁጥጥር ስር በዋለበት ሰዓት፤ እርሱ እና ሌሎች ሁለት ጋዜጠኞች ወደ ስራ የሚያመጣቸውን የድርጅቱን መኪና በመጠባበቅ ላይ እንደነበሩ ገልጾ፤ ቢሮ በደረሱበት ሰዓት በአካባቢው በርካታ ፖሊሶች በማየታቸው መመለሳቸውን አብራርቷል። ፖሊሶች ዋና አዘጋጁን ወደየት እንደወሰዱት እስካሁን አለማወቃቸውንም አክሏል።
የአውሎ ሚዲያ ባልደረቦች በጸጥታ ኃይሎች ችግር ሲያጋጥማቸው የአሁኑ የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። በትግራይ የሚካሄደውን ምርጫ ለመዘገብ ባለፈው ጳጉሜ ወር ወደ መቀሌ ሊያመሩ የነበሩ ሶስት የድርጅቱ ሰራተኞች፤ በአውሮፕላን እንዳይሳፈሩ መደረጋቸው ይታወሳል። ሰራተኞቹ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ “ለጥቂት ጊዜያት ተይዘው መቆየታቸውን እና የስራ መሳሪያዎቻቸው እንዲሁም መታወቂያቸው በጸጥታ ኃይሎች ተወስዶባቸው እንደነበር” መናገራቸው አይዘነጋም። (በተስፋለም ወልደየስ -ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)