ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም ሂዩማን ራይትስ ዎች፤ የኢትዮጵያ የፌደራል እና የክልል ባለስልጣናት ጸጥታን በተመለከተ የሚወስዷቸው እርምጃዎች፤ የዜጎቻቸውን “መብት በሚጠብቅ መልክ ሊሆኑ እንደሚገባ” አሳሰበ። የሀገሪቱ ባለስልጣናት በትግራይ የተቋረጠውን የቴሌኮምንኬሽን ግንኙነቶች ወደ መደበኛ አገልግሎት እንዲመልሱም ጠይቋል።
ተቋሙ ይህን ያስታወቀው በትግራይ የተከሰተውን ቀውስ ተከትሎ ከሰዎች መብቶች ጋር በተያያዘ ያሉ አሳሳቢ ጉዳዩችን በተመለከተ ዛሬ ረቡዕ ባወጣው መግለጫ ነው። “ኢትዮጵያውያን ባለፈው ዓመት በየዕለቱ ብጥብጥ እና ስቃይ ሲጋፈጡ ቆይተዋል” ሲሉ በመግለጫቸው ያመለከቱት የሂዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ዳይሬክተር ማውሲ ሴጉን፤ “በኢትዮጵያ የቀጠለውን ቀውስ ለመፍታት ቀላል መፍትሄ የለም” ሲሉ ችግሩ ጥልቅ መሆኑን አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ያጋጠመውን የጸጥታ መታወክ ተከትሎ፤ “ዓለም አቀፍ አጋሮች በአብዛኛውን ዝምታን መምረጣቸውን” ዳይሬክተሯ ጠቅሰዋል። ሆኖም አጋሮቹ፤ የፌደራል እና የክልል ባለስልጣናት “የሁሉንም ኢትዮጵያውያንን መብት በሚጠበቅ መልኩ” ይንቀሳቀሱ ዘንድ “መልዕክት ሊያስተላልፉ ይገባል” ብለዋል።
አሜሪካ አዲስ አበባ ባለው ኤምባሲዋ በኩል ዛሬ ከሰዓት ባወጣችው መግለጫ፤ በትግራይ ክልል ያለው ወቅታዊ ውጥረት በአፋጣኝ እንዲረግብ አሳስባለች። ሀገሪቱ ሁለቱም ወገኖች “የተመጠኑ እርምጃዎችን” እንዲወስዱም ጠይቃለች። የአሜሪካ ኤምባሲ በአጭር መግለጫው ማጠቃለያ ላይ “ሁሉም ወገኖች የሰላማዊ ህዝብን ደህንነት እና ጸጥታ ቅድሚያ እንዲሰጡ አበክረን እናበረታታለን” ብሏል።
ተመሳሳይ መልዕክት ያስተላለፈው የብሪታንያ ኤምባሲም፤ ሁሉም ወገኖች የሰላማዊ ሰዎችን ደህንነት እንዲጠብቁ አሳስቧል። ስዊዲን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ባስተላለፈችው አን ሊንደ በኩል ባስተላለፈችው መልዕክት፤ ሀገሪቱ በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ በጥልቅ እንዳሳሰባት አስታውቃለች።
ሀገራቸው በኢትዮጵያ ያሉ ሁነቶችን እየተከታተለች እንደሆነ በትዊተር ገጻቸው ያሰፈሩት ሚኒስትሯ፤ ስዊዲን ሁሉም ወገኖች በአፋጣኝ የውይይትን መንገድ እንዲከተሉ እንደምታሳስብ ገልጸዋል። “ብጥብጥ የመጪው ጊዜ መንገድ ሊሆን አይገባም” ያሉት ሊንደ፤ እንዲህ አይነቱ አካሄድ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ቀጠናውን ጭምር የማናጋት አደጋ እንዳለው ጠቁመዋል።
ሂዩማን ራይትስ ዎች በመግለጫው ያነሳው ሌላው ጉዳይ በትግራይ ክልል የተቋረጠውን የቴሌኮምንኬሽን ግንኙነት ጉዳይ ነው። ግንኙነቱ ወደ ቀድሞ ይዞታው እንዲመለስ የጠየቁት ማውሲ፤ ለዚህም ምክንያት ያሉትን በመገለጫቸው ዘርዝርዋል። የአገልግሎቱ መቋረጥ ተጽዕኖ ከሚያሳድርባቸው ጉዳዩች አንዱ “የተቺ ዘገባዎች መገደብ” መሆኑን አንስተዋል። እንዲህ አይነት ዘገባዎች በሰላማዊ ህዝብ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ክስተቶችን ተከታትለው የሚያሳውቁ መሆናቸውንም አስታውሰዋል።
የፌደራል መንግስት ያቋረጠው የቴሌኮምንኬሽን አገልግሎት፤ ዜጎች ሊያገኙ የሚገባቸው መረጃ ላይም ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል። መረጃዎቹ ጤንነታቸው እና ደህንነታቸውን የሚጎዱ ጉዳዩችን የተመለከቱ ሊሆኑ እንደሚችሉም ጠቅሰዋል። መንግስት “ስለክስተቶች የሚያወጣቸው መረጃዎች ላይ “ጥያቄ የማቅረብ መብታቸውን የሚሸርሽር ነው” ሲሉ አብራርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)