ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በትግራይ ባሉ ኢላማዎች ላይ ተጨማሪ የአየር ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል አስጠነቀቁ

በተስፋለም ወልደየስ 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በትግራይ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ባሉ ኢላማዎች ላይ፤ በቀንም ሆነ በማታ ተጨማሪ የአየር ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል አስጠነቀቁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ አርብ ማምሻውን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ  በመቐለ አካባቢ ትላንት እና ዛሬ የአየር ድብደባ መፈጸሙን አረጋገጠዋል።

በአየር ኃይል አማካኝነት እስካሁን በተፈጸሙ የአየር ጥቃቶች እስከ 300 ኪሎ ሜትር ድረስ መወንጨፍ የሚችሉ ሮኬቶች ጭምር መውደማቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ከሮኬቶቹ በተጨማሪ ራዳሮች እና ሚሳኤሎችም በአየር ጥቃቱ “ሙሉ በሙሉ” እንዲደመሰሱ ማድረጋቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እርምጃው የተወሰደውም “የጠላትን የማድረግ አቅም ለመግታት ነው” ሲሉ አክለዋል።  

“እነዚህን ሮኬቶች በመጠቀም ስግብግቡ ጁንታ ኃይል ብዙ ከተሞችን ሊያጠቃ ይችላል። ህዝባችንንም ሊያጠፋ ይችላል። ያን አያደርግም ብለን እንዳናስብ፤ ባለፉት ወራት በህዝባችን ላይ የደረሰው ጭፍጨፋ ‘እንደዚህ አይነት ሞራል ያለው ኃይል ነው’ ብለን ለመተማመን ያስቸግራል” በማለት የአየር ጥቃቱን ለመፈጸም ምክንያት ነው ያሉትን ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።

የሕወሓት ኃይል፤ የራሱን የምርጫ ቡድን እንደፈጠረው ሁሉ፤ በኢትዮጵያ ያለውን ብቸኛ የሲቪል አቪዬሽን መስሪያ ቤት ስልጣን የሚገዳደር መግለጫ ከሁለት ቀን በፊት ማውጣቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውሰዋል። በትግራይ አካባቢ ማንኛውንም በረራ ማድረግ እንደማይቻል የሚከለክለው መግለጫ እርምጃውን ለመውሰድ አንድ ምክንያት እንደነበር አብይ ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በትግራይ ውጊያ ከተቀሰቀሰ በኋላ በሕወሓት ኃይል በኩል “ሮኬቶችን ለመጠቀም ሙከራዎች እየተደረጉ መሆኑን” መረጃዎችን ማግኘታቸውን ጠቅሰዋል። “በመጀመሪያው ዕለት ተጨማሪ ማጣራት ለማድረግ የቆየን ሲሆን በሁለተኛ ቀን ፍላጎቱ ጠንካራ መሆኑን ስላረጋገጥን ራዳሮች፣ ሚሳኤሎች፣ ሮኬቶች ሙሉ በሙሉ እንዲጠፉ አድርገናል” ብለዋል።  

የትግራይ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ትላንት ሐሙስ ጥቅምት 26 ባወጣው መግለጫ የውጊያ ጀቶች በመቐለ አካባቢ ድብደባ መፈጸማቸውን ገልጾ ነበር። በመቐለ የሚገኙ አንድ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጭ የውጊያ ጀቶቹ የመቐለን ከተማ አቋርጠው ሲያልፉ የታዩት ትላንት ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ እንደነበር ተናግረዋል። 

የጀቶቹን ድምጽ የሰማው የከተማው ነዋሪ በወቅቱ በከፍተኛ ሁኔታ በመደናገጥ ወደ መንገዶች በመውጣት መመልከቱን እኚሁ ምንጭ አስረድተዋል። ጀቶቹ የአየር ድብደባ ፈጽመውበታል የተባለው ቦታ በመሶበ ሲሚንቶ ፋብሪካ አቅጣጫ የሚገኝ ቦታ እንደሆነ ሰምቼያለሁ ብለዋል። የትላንቱን ድብደባ ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች እየተካሄዱ ባሉ ውጊያዎች እስካሁን ድረስ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ ግልጽ መረጃ እንደሌለም ጠቁመዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዛሬው መግለጫቸው “የአየር ጥቃቱ በፍጹም የሲቪል ኢላማዎችን ታሳቢ ያደረገ አይደለም” ሲሉ በዚህ ረገድ የሚነሱ ስጋቶችን ለማረጋጋት ሙከራ አድርገዋል። ለዚህም ሁለት ምክንያቶችን አንስተዋል።    

“አንደኛ እነዚህ የሚሳኤል፣ የራዳር፣ የሮኬት ቦታዎች በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የተገዙ፣ በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ይጠበቁ የነበሩ [ናቸው]።  እያንዳንዱ ትጥቅ የት እንዳለ በዝርዝር ሙሉ ዕውቀት አለን። ሁለተኛ እኛ ከአየር ኃይል አንጻር ዝግጅታን ከፍ ላለ ደረጃ ስለነበረ፣ በተለይም ከዚህ ቀደም በነበረው መንገድ ብቻ ሳይሆን በቀንም በማታም፣ በአንድ ሜትር precision ካለችግር ሊያጠቁ የሚችሉ፣ በሰው የማይነዱ ዘመናዊ መሳሪያዎችን ስለታጠቅን፤ እንደዚህ አይነት ችግር ሳያጋጥም ኢላማዎቻችንን ለይተን ለማጥቃት የሚያስችል ብቃት ስላለን፤ በተቻለ መጠን ሲቪል የሀገራችን ህዝቦች በዚህ አካባቢ ጥፋት እንዳይደርስባቸው፤ collateral damage በጣም ያነሰ እንዲሆን ጥረት ተደርጓል። ወደፊትም ይደረጋል” በማለት አብራርተዋል። 

መሰል የአየር ጥቃቶች ወደፊትም እንደሚቀጥሉ በመግለጫቸው ደጋግመው የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ህዝቡ ከኢላማዎች አካባቢ ራሱን በማራቅ ከአደጋ እንዲጠብቅ በአጽንኦት አሳስበዋል። 

“በመቐለ፣ በአዲግራት፣ በአክሱም፣ በሽረ አካባቢ ያሉ በእነዚህ ከተማ የሚኖሩ ሰዎች መጠንቀቅ ያለባቸው ነገር ኤርፖርቶች፣ የትጥቅ ዲፖዎች፥ የነዳጅ ዲፖዎች አካባቢ አለመቅረብ ነው። ይህ ስግብግብ ጁንታ የሚሰባሰብባቸው ቦታዎች አለመቅረብ ነው። እነዚህ ኢላማዎች በቀንም፣ በማታም፣ በማንኛውም ሰዓት ጥቃት ሊፈጸምባቸው ይችላል”

– ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

“በመቐለ፣ በአዲግራት፣ በአክሱም፣ በሽረ አካባቢ ያሉ በእነዚህ ከተማ የሚኖሩ ሰዎች መጠንቀቅ ያለባቸው ነገር ኤርፖርቶች፣ የትጥቅ ዲፖዎች፥ የነዳጅ ዲፖዎች አካባቢ አለመቅረብ ነው። ይህ ስግብግብ ጁንታ የሚሰባሰብባቸው ቦታዎች አለመቅረብ ነው። እነዚህ ኢላማዎች በቀንም፣ በማታም፣ በማንኛውም ሰዓት ጥቃት ሊፈጸምባቸው ይችላል” ሲሉ በከተሞቹ ለሚኖሩ ነዋሪዎች የማስጠንቀቂያ መልዕክት አስተላልፈዋል። 

በቆቦ አካባቢም “የተከማቹ መድፎች እና ታንኮች አሉ” ያሉት አብይ፤ “እንደዚህ አይነት ከፍተኛ መሳሪያዎች የተከማቹባቸው አካባቢዎች” ተመሳሳይ ጥቃቶች በቀንም ይሁን በማታ ሊፈጸምባቸው እንደሚችል በድጋሚ አስታወሰዋል። በዚያ አካባቢ ያሉ ሚሊሺያዎች እና ነዋሪዎች ራሳቸውን ከስፍራዎቹ እንዲያርቁም መክረዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጠቀሷቸው አካባቢዎች ያሉ ሰዎች ለትግራይ ክልል በተደነገገው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሰረት “የሰዓት እላፊ እንዲያከብሩ”፣ “ከከተማ ውስጥ እንቅስቃሴ እና ከመሰባሰብ እንዲቆጠቡ በተጨማሪነት አሳስበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ስግብግብ ጁንታ” በማለት በተደጋጋሚ በመግለጫቸው የጠሩት ኃይል ወደ ሕግ እስከሚቀርብም “በሙሉ አቅም ጥቃቱ የሚቀጥል ይሆናል” ሲሉም አስጠንቅቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)