የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በቦሌ አየር ማረፊያ ተጨማሪ መታወቂያ መጠየቁን በተመለከተ ማብራሪያ ጠየቀ

በተስፋለም ወልደየስ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በቦሌ አየር ማረፊያ የሚጓዙ ኢትዮጵያውያን መንገደኞች ከፓስፖርት በተጨማሪ የቀበሌ መታወቂያ ወረቀት እንዲያቀርቡ መገደዳቸውን በተመለከተ ማብራሪያ ጠየቀ። አዲሱ አሰራር “ዜጎችን በብሔራቸው በመለየት ለጥርጣሬ እና መድልዎ እንዲጋለጡ የሚያደርግ ነው” ብሏል።  

መንግስታዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም ጥያቄውን ያቀረበው ለኢትዮጵያ ሲቪል አሺዬሽን ባለስልጣን እና ለአዲስ አበባ ቦሌ ኤርፖርት ደህንነት ቢሮ ትላንት ማክሰኞ ህዳር 1፤ 2013 በጻፈው ደብዳቤ ነው። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችውና የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ፊርማ ያረፈበት ደብዳቤ፤ በግልባጭ ለጠቅላይ አቃቤ ህግ ጽህፈት ቤት፣ ለትራንስፖርት ሚኒስቴር እና ለአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር መላኩም ታውቋል። 

በሁለት ገጽ የተዘጋጀው የኮሚሽኑ ደብዳቤ፣ የአገር ውስጥ ወይም የውጭ ጉዞ የሚያደርጉ ኢትዮጵያውያን፤ የታደሰ የቀበሌ አሊያም የወረዳ የመታወቂያ ወረቀት በተጨማሪነት ስለ መጠየቃቸው ጥቆማዎች ለመስሪያ ቤቱ መቅረቡን ይጠቅሳል። ጥቆማዎቹ፤ የሲቪል አሺዬሽን ባለስልጣን ይህን አስገዳጅ አሰራር ወይም መመሪያ በቦሌ አየር ማረፊያ ተግባር ላይ እያዋለ መሆኑን እንደሚያመለክቱም ገልጿል። 

አሰራሩ በሁለት ምክንያቶች የሰብዓዊ መብት ጥያቄ ሊያስነሳ እንደሚችል ኮሚሽኑ በደብዳቤው ጠቁሟል። ትኮሚሽኑ በቀዳሚነት ያቀረበው ምክንያት አዲሱ አሰራር ወይም መመሪያ “የሰዎችን የመንቀሳቀስ ወይም የመዘዋወር መሰረታዊ መብት ያለአግባብ ሊገድብ የሚችል ነው” የሚል ነው። “ፓስፖርት በራሱ የተሟላ የመታወቂያ ካርድ” መሆኑን የሚጠቅሰው ደብዳቤው፤ ተጨማሪ መታወቂያ የማቅረብ አስፈላጊነት ላይ ጥያቄ አንስቷል።  

“ይህ አዲስ መመሪያ ወይም አሰራር በተለይ አሁን በኢትዮጵያ ከተፈጠረው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ዜጎችን በብሄራቸው ማንነት በመለየት ለጥርጣሬ እና መድልዎ (ethnic profiling) እንዲጋለጡ የሚያደርግ ምክንያታዊ ስጋት መፍጠሩን ተረድተናል”

– የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን

በአዲስ አበባ ከተማ በአሁኑ ወቅት አዲሱን የዲጂታል የነዋሪዎች መታወቂያ የማውጣት ሂደት ለጊዜው መቋረጡን ኮሚሽኑ በተጨማሪ ነጥብነት ጠቅሷል።  በተለምዶም ቢሆን በከተማይቱ “የነዋሪነት የመታወቂያ ወረቀት ለማግኘት ከፍተኛ መጨናነቅ እና ችግር” እንደሚስተዋልም አስታውሷል። በእነዚህ ምክንያቶችም መንገደኞች ተጨማሪ መታወቂያ እንዲያቀርቡ መገደዳቸው የሰዎችን የመዘዋወር መብት እንደሚገድብ አጽንኦት ሰጥቷል። 

ኮሚሽኑ ከሰብዓዊ መብት አንጻር ያነሳው ሁለተኛ ምክንያት “አንዳንድ የቀበሌ መታወቂያዎች የሰዎችን የብሔር ማንነት የሚገልጹ ወይም በዲጂታል መሳሪያ በመጠቀም ለማወቅ የሚያስችሉ” መሆናቸውን ነው። “ይህ አዲስ መመሪያ ወይም አሰራር በተለይ አሁን በኢትዮጵያ ከተፈጠረው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ዜጎችን በብሄራቸው ማንነት በመለየት ለጥርጣሬ እና መድልዎ (ethnic profiling) እንዲጋለጡ የሚያደርግ ምክንያታዊ ስጋት መፍጠሩን ተረድተናል” ሲል ኮሚሽኑ በደብዳቤው ገልጿል። 

የኢትዮጵያ ሲቪል አሺዬሽን ባለስልጣን እንዲህ አይነት ጉዳዩች ተከስተው ከሆነ፣ የፈጠሩትን ስጋቶች ተመልክቶ በአፋጣኝ ማስተካከያ እንዲያደርግ ኮሚሽኑ አሳስቧል። ኮሚሽኑ የአሰራሩን ተገቢነት ከሰብዓዊ መብቶች አንጻር ለማጣራት ይቻለው ዘንድም፤ ባለስልጣኑ በአስቸኳይ የተሟላ ማብራሪያ እንዲሰጥም በደብዳቤው ጠይቋል። 

የኮሚሽኑ ደብዳቤ እንደደረሳቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያረጋገጡት የኢትዮጵያ ሲቪል አሺዬሽን ባለስልጣን ዳይሬክተር ጄነራል ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው፤ ጉዳዩ እርሳቸው የሚመሩትን መስሪያ ቤት የሚመለከት እንዳልሆነ ተናግረዋል። ለደብዳቤው መስሪያ ቤታቸው በነገው ዕለት ምላሽ እንደሚሰጥም ገልጸዋል።    

“እኛ መታወቂያ አንቆጣጠርም። የእኛ ስራ ከዚህ ጋር አይገናኝም። እኛ ስራችን ትራንስፖርቱን መቆጣጠር ነው። ስታንደርዱን ጠብቆ ደህንነት መኖሩን መቆጣጠር ነው ትልቁ ስራችን። ያ ስራ ከመታወቂያ ጋር ምንም አይገናኝም” ሲሉ በደብዳቤው ላይ የተጠቀሰውን ጉዳይ በተመለከተ ኮሎኔል ወሰንየለህ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምላሽ ሰጥተዋል።  

“ፖስፖርትም ላይ ቢሆን ዓለም አቀፍ ስታንደርድ አለው። ‘ፖስፖርት ምን መሆን አለበት?’ የሚለውን የሚሰራው ኢሚግሬሽን ነው። ደብዳቤው ለእኛ መሆን አልነበረበትም” ሲሉም ዳይሬክተር ጄነራሉ በተጨማሪነት አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)