በአዲስ አበባ አድዋ ድልድይ ስር ዛሬ ረቡዕ፤ ህዳር 2 ጠዋት ከፍተኛ የፍንዳታ ድምጽ መስማታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች እና የዓይን እማኞች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ፍንዳታው የተከሰተው ወድቆ የተገኘ ቦምብ ፈንድቶ መሆኑን ገልጾ በአንድ ግለሰብ ላይም ቀላል የአካል ጉዳት ማድረሱን አስታውቋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች ፍንዳታውን የሰሙት ጠዋት ከአንድ ሰዓት ተኩል እስከ ሁለት ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ እንደነበር ይናገራሉ። “ፍንዳታውን ስሰማ የሲኖትራክ ጎማ የፈነዳ መስሎኝ ነበር” ሲል አንድ ነዋሪ ሁኔታውን ገልጸውታል። ሌላ ነዋሪ ደግሞ ፍንዳታውን የመብራት ትራንስፎርመሮች ሲፈነዱ ከሚሰማው ድምጽ ጋር አነጻጽረውታል። ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው ጠዋት ከተሰማው ፍንዳታ በፊት ንጋት አስራ አንድ ሰዓት አካባቢ ሌላ የፍንዳታ ድምጽ እንደነበር ገልጸዋል።
ፍንዳታው እንዴት እንደደረሰ እንደማያውቁ የሚናገሩት የዓይን እማኞች፤ ሆኖም በፍንዳታው የተጎዳ አንድ ሰው ከድልድይ ስር ወጥቶ በአምቡላንስ ወደ ሆስፒታል ሲወሰድ መመልከታቸውን አስረድተዋል። ተጎጂው ከድልድዩ ስር ከሚጣለው ቆሻሻ ጠቃሚ ነገሮችን የሚያፈላልግ ይሁን አሊያም ፍንዳታውን ለመፈጸም ሲሞክር ጉዳት ይድረስበት ማወቅ አለመቻላቸውን አክለዋል።
በፍንዳታው አንድ ሰው መጎዳቱን ያረጋገጠው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፤ ግለሰቡ በምኒልክ ሆስፒታል ህክምና እየተከታተለ እንደሚገኝ ገልጿል። ፖሊስ የተጎጂውን ማንነት በዝርዝር ባይገልጽም በታክሲ ረዳትነት ስራ የተሰማራ መሆኑን ግን አስታውቋል። ግለሰቡ ጉዳት የደረሰበት ለመጸዳዳት ወደ ድልድይ በገባበት ወቅት በማዳበሪያ የተጠቀለለ እቃ ተመልክቶ በእግሩ መርገጡን ተከትሎ እንደሆነ የአዲስ አበባ ፖሊስ መግለጫ አመልክቷል።
ረፋዱን የፌደራል እና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት፤ ፍንዳታው በደረሰበት የአድዋ ድልድይ ክፍል ያለውን ስፍራ እግረኞች እንዳይተላለፉ በገመድ አጥረው ምርመራ ሲያደርጉ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ተመልክቷል። የፌደራል ፖሊስ የፎረንሲክ እና ፈንጂዎች ምርምራ ቡድን ተሽከርካሪዎችም እስከ ረፋዱ አምስት ሰዓት ድረስ በአካባቢው ቆመው ታይተዋል። የቡድኑ መርማሪዎችም በምርመራው ላይ ተሳትፎ ሲያደርጉ ተስተውለዋል።
ፍንዳታው ከደረሰ በኋላ የአድዋ ድልድይም ሆነ ሌሎች መንገዶች ለተሽከርካሪዎች ዝግ ባይደረጉም፤ በርከት ያሉ ፖሊሶች በአካባቢው የጸጥታ ቁጥጥር ሲያደርጉ ቆይተዋል። ፍንዳታው ደረሰበት በተባለበት የአድዋ ድልድይ ጎን ከሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ደጃፍም የፖሊሶች እንቅስቅሴ ከወትሮው በዛ ብሎ ታይቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)