በባህር ዳር እና ጎንደር ላይ ሮኬት ተተኩሶ ጉዳት መድረሱን የኢትዮጵያ መንግስት ገለጸ

በተስፋለም ወልደየስ 

ትላንት ምሽት በባህር ዳር እና ጎንደር የደረሰው ፍንዳታ በከተሞቹ በሚገኙ አውሮፕላን ጣቢያዎች ላይ በተተኮሰ ሮኬት የደረሰ መሆኑን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ አስታወቀ። ሮኬቱ የተተኮሰው በህወሓት “ጁንታ” ቡድን መሆኑም ተገልጿል።

የህወሓት “ጁንታ በእጁ ያሉትን የመጨረሻዎቹን መሣሪያዎች ጠጋግኖ ሞክሯል። ይህም ከመሞቱ በፊት የመጨረሻውን አቅሙን እየሞከረ መሆኑን ያመለክታል” ሲል የመረጃ ማጣሪያው በይፋዊ ገጹ አስታውቋል። የክስተቱን ዝርዝር ጉዳዮች መርማሪ ቡድን ተመድቦ እያጣራው  መሆኑንም ገልጿል።

በትላንቱ ፍንዳታ በሁለቱም ከተሞች “አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ መጠነኛ ጉዳት” መድረሱን የመረጃ ማጣሪያው አስታውቋል።  ፍንዳታዎቹ የተከሰተቱት በባህር ዳር ከተማ መከላከያ ኮንስትራክሽን ድርጅት (መኮድ) እና ጎንደር ከተማ አዘዞ አካባቢ እንደነበር የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ትላንት ምሽት ገልጾ ነበር። 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የዛሬ ሳምንት በሰጡት መግለጫ፤ 300 ኪሎ ሜትር ድረስ መወንጨፍ የሚችሉ ሮኬቶች በህወሓት እጅ ገብተው እንደነበር አስታውቀው ነበር። በመቐለ አካባቢ በአየር ኃይል በተፈጸመ ጥቃት ሮኬቶቹን ጨምሮ ራዳሮች እና ሚሳኤሎች ጭምር በአየር ጥቃቱ “ሙሉ በሙሉ” እንዲደመሰሱ ማድረጋቸውንም በወቅቱ በሰጡት መግለጫ ማብራራታቸው ይታወሳል። 

“እነዚህ የሚሳኤል፣ የራዳር፣ የሮኬት ቦታዎች በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የተገዙ፣ በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ይጠበቁ የነበሩ [ናቸው]።  እያንዳንዱ ትጥቅ የት እንዳለ በዝርዝር ሙሉ ዕውቀት አለን” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በባለፈው ሳምንት መግለጫቸው ጠቅሰዋል። 

የጠቅላይ ሚኒስትሩን መግለጫ ተከትሎ የህወሓት ስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ከጽምጺ ወያኔ ቴሌቪዥን ጣቢያ ባደረጉት ቃለ ምልልስ አውሮፕላኖቹ የሚነሱባቸውን የአየር ማረፊያ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት እንደሚያደርሱ ዝተው ነበር። አቶ ጌታቸው “የአብይ አውሮፕላኖች የሚነሱባቸው ኤርፖርቶች የትም ይሁኑ የትም የተነሱትን አውሮፕላኖች እንመታለን። ድንገት ያመለጠ አውሮላን ካለ፣ አውሮፕላኖቹ የተነሱበት ኤርፖርቶች የትም ይሁኑ የትም በእጥፍ እርምጃ እንወስዳለን” ሲሉ ለቴሌቪዥን ጣቢያው መናገራቸው አይዘነጋም።

አቶ ጌታቸው ዛሬ ቅዳሜ ህዳር 5፤ እኩለ ቀን ገደማ ለትግራይ ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ፤ በባህር ዳር እና በጎንደር ትላንት ምሽት የደረሰው ጥቃት በትግራይ ክልል ኃይል የተፈጸመ መሆኑን  አረጋግጠዋል። ጥቃቱ በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ለተካሄደው የአየር ድብደባ የተሰጠ “አጸፋዊ ምላሽ” መሆኑንም አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ትላንት በሁለቱ ከተሞች የተሰነዘረው ጥቃት “በሮኬት” መሆኑን ቢገልጽም፤ አቶ ጌታቸው ግን ጥቃቱ የተፈጸመው “በሚሳኤል” ነው ባይ ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)  

[ይህ ዘገባ ዘግየት ብሎ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]