ላለፉት አራት ወራት ገደማ በእስር ላይ የቆዩ ሁለት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (አነግ) መካከለኛ አመራሮች እያንዳንዳቸው የ20 ሺህ ብር ዋስትና በማስያዝ ተፈቱ። ዛሬ ከእስር የተፈቱት የኦነግ የወጣቶች ክንፍ ኃላፊ አቶ ለሚ ቤኛ እና በአዲስ አበባ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ድርጅታዊ ጉዳዩች ኃላፊ አቶ ዳዊት አብደታ ናቸው።
ከሁለቱ አመራሮች ጋር አብሮ ክስ የቀረበበት አቶ ደምሴ በንቲ የተባለ የኦነግ አባልም እንዲሁ በ10 ሺህ ብር ዋስትና ዛሬ ከእስር መለቀቁን የኦነግ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ባቴ ኡርጌሳ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ሁለቱ አመራሮች እና የኦነግ አባሉ የተለቀቁት፤ በፍርድ ቤት የተከሰሱበት ሁከት የማነሳሳት ወንጀል “የዋስትና መብት አያስከለክልም” በመባሉ መሆኑን አቶ ባቴ ገልጸዋል።
የሶስቱን ተከሳሾች የዋስትና መብት እንዲጠበቅላቸው በትላንትናው ዕለት ውሳኔ ያስተላለፈው የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበታ ልዩ ችሎት መሆኑንም አክለዋል። ፍርድ ቤቱ ቀጣይ የክስ ሂደቱን ለመመልከት ለመጪው ህዳር 14፤ 2013 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በርከት ያሉ የኦነግ አመራሮች እና አባላት መታሰራቸውን ፓርቲው በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል። ዛሬ በዋስትና የተፈቱት አቶ ለሚ እና አቶ ዳዊትም ከሃጫሉ ግድያ በኋላ ከታሰሩት አመራሮች መካከል መሆናቸውን አቶ ባቴ አስታውሰዋል። ሁለቱ አመራሮች በተለያየ ቦታ ሲታሰሩ መቆየታቸውን ያስታወሱት የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ፤ በዋስትና የተለቀቁት በሰበታ ከተማ ዳለቴ በሚባል ቦታ ካለ እስር ቤት እንደሆነ ጠቁመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)