በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ላይ በደረሰ ጥቃት ቢያንስ 34 ሰዎች መገደላቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ

139

በተስፋለም ወልደየስ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ላይ በደረሰ ጥቃት ቢያንስ 34 ሰዎች መገደላቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በድባጤ ወረዳ፣ ትላንት ቅዳሜ ህዳር 5 ከወንበራ ወደ ቻግኒ በመጓዝ ላይ በነበረ የሕዝብ ማመላሻ አውቶብስ ላይ በተፈጸመ ጥቃት በትንሹ 34 ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ። የተጎጂዎች ቁጥር ከዚህ በላይ ሊጨምር እንደሚችል ኮሚሽኑ ገልጿል።

ኮሚሽኑ ዛሬ እሁድ ባወጣው መግለጫ በሕዝብ ማመላለሻ ላይ የደረሰውን ጥቃት “ዘግናኝ” ሲል ጠርቶታል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዩች ጽህፈት ቤት ጥቃቱን በተመለከተ ትላንት ባወጣው መግለጫም ተመሳሳይ አገላለጽ ተጠቅሟል።

ጽህፈት ቤቱ ጥቃቱ የደረሰው ከወምበራ – ቡለን – ድባጤ – ቻግኒ በሚወስደው መስመር ሲንቀሳቀስ በነበረ የሕዝብ ማመላለሻ ላይ መሆኑን ገልጾ ነበር። ጥቃት አድራሾቹ “የሕዝብ ማመላለሻ አስቁመው በተሳፋሪዎች ላይ ዝግናኝ ጥቃት አድርሰዋል” ሲል በትላንት መግለጫው አስፍሯል። የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ በመተከል ዞን በደረሰው በዚሁ ጥቃት ቁጥራቸው እስካሁን በወል ያልታወቀ ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። 

በጥቃቱ ከቆሰሉት መካከል የድባጤ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ደበሊ በልጋፎ እንደሚገኙበት የክልሉ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዩች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ ተናግረዋል

“መነሻውን ዶቢ ያደረገ አውቶብስ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ተሳፋሪዎች ይዞ፤ ቡለንን አልፎ ወደ ድባጤ እየመጣ ባለበት ወቅት ነው መኪና አቁመው በጣም አሳፋሪ ድርጊት ነው የፈጸሙት። አቁመው ተኮሱ። ያመለጠው አመለጠ፤ የገደሉትን ገደሏቸው” ሲሉ የክልሉ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዩች ጽህፈት ቤት ኃላፊ የተከሰተውን አብራርተዋል።   

አቶ መለሰ በጥቃቱ የቆሰሉ ሰዎች በድባጤ ጤና ጣቢያ አስፈላጊ ህክምና እየተደረገላቸው እንደሆነም ጠቁመዋል። በጥቃቱ ከቆሰሉት መካከል የድባጤ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ደበሊ በልጋፎ እንደሚገኙበትም ጨምረው ገልጸዋል። 

“በያምፕ ቀበሌ በነበረው ውጊያ ተጨማሪ ኃይል ይዞ እየተንቀሳቀሰ ባለበት፤ ጠዋት ላይ ደፈጣ ይዘው መጠነኛ የመቁሰል አደጋ አድርሰውበታል። እጁ አካባቢ ነው የመቱት። ያን ያህል ለክፉ የሚሰጥ አይደለም” ብለዋል። 

በድባጤ ወረዳ በምትገኘው ያምፕ ቀበሌ ከትላንት በስቲያ አርብ እና ትላንት ቅዳሜ ጠዋት ተኩስ እንደነበር የገለጹት አቶ መለሰ፤ የጸጥታ ኃይሎች ችግሩን ለመቆጣጠር ጥረት ማድረጉን አስረድተዋል። የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዩች ጽህፈት ቤት ኃላፊው “ጸረ- ሰላም” ሲሉ የጠሯቸው ኃይሎች፤ ዓላማቸው “በቀጥታ ወደ ድባጤ ከተማ መግባት” እንደነበር አመልክተዋል።

“እነዚህ ኃይሎች ወደ ድባጤ ከተማ እንዳይገቡ የመከላከያ ሰራዊት፣ የክልሉ ጸረ-ሽምቅ ኃይል፣ ፖሊስ፣ ሚሊሺያ፣ የአካባቢው ማህበረሰብ በተደራጀ መልኩ ሰፊ የሆነ የመከላከል እርምጃ ወስደዋል” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።   

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ እነዚህን ጥቃቶች ሊያስቆም የሚችል አዲስ ክልላዊ የፀጥታ ስትራቴጂ ሊነድፍ እንደሚገባ አሳስበዋል

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ጥቃቱ የበለጠ እንዳይባባስ በፍጥነት እርምጃ መውሰዳቸው አበረታች” መሆኑን ቢጠቅሱም፤ ሆኖም በክልል በሲቪል ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ፋታ የማይሰጥ ሆኖ መቀጠሉን በአሳሳቢነት አንስተዋል። ለጉዳዩ የተሻለ መፍትሄ በአፋጣኝ ሊፈለግለት እንደሚገባም አመልክተዋል። 

“[ጥቃቱ] በፌዴራልና በክልሉ መንግሥታት የፀጥታ ኃይሎች መካከል በፍጥነትና ንቁ ሆኖ መጠበቅ ላይ የተመሰረተ የተሻለ ቅንጅት የሚሻ ነው” ያሉት ዶ/ር ዳንኤል፤ “የፌዴራልና የክልሉ የፀጥታና የፍትሕ አካላት ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመሆን እነዚህን ጥቃቶች ሊያስቆም የሚችል አዲስ ክልላዊ የፀጥታ ስትራቴጂ ሊነድፉ ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)