በኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ በትላንትናው ምሽት 1 ሰዓት ከ50 ገደማ “ከፍተኛ ተከታታይ ድምጾች” መሰማታቸውን በኤርትራ የአሜሪካ ኤምባሲ አስታወቀ። ኤምባሲው በአስመራ ለሚገኙ ዜጎቹ ዛሬ እሁድ ባሰራጨው የማስጠንቀቂያ መልዕክት፤ ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች በአስመራ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ቅጽር የሚፈነዱ መሳሪያዎች ሳይኖሩ እንዳልቀሩ አመላክተዋል ብሏል።
ሆኖም ኤምባሲው “የአስመራ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ስለመጠቃቱ ምንም ዓይነት ማመላከቻ የለም” ሲል ቀደም ሲል ከተሰራጩ ዘገባዎች ጋር የሚቃረን መልዕክት አስፍሯል። ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የዲፕሎማቲክ ምንጮቻቸውን ጠቅሰው እንደዘገቡት፤ በትላንትናው ምሽት በትንሹ ሶስት ሮኬቶች ወደ አስመራ ከተማ መተኮሳቸውን ገልጸው ነበር። ሁለቱ ሮኬቶች የአስመራ አየር ማረፊያን መምታቸውን “ሮይተርስ” ዲፕሎማቶችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
ትላንት ምሽት በአስመራ ከተማ የተሰማውን ፍንዳታ ተከትሎ የመብራት እና የቴሌኮሚዩኒኬሽን ግንኙነቶች በመቋረጣቸው፤ ስለ ክስተቱ ከከተማይቱ ነዋሪዎች ዝርዝር መረጃ ማግኘት አልተቻለም። ፍንዳታው እንዴት እንደተከሰተ በኤርትራ መንግስት በኩል እስካሁን በይፋ የወጣ መረጃ የለም።
የአስመራው የቅዳሜ ምሽት ፍንዳታ እንደተሰማ በርካቶች ጉዳዩን ከህወሓት የሚሳኤል ጥቃት ዛቻ ጋር አያይዘውታል። የህወሓት ስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት ጌታቸው ረዳ ቅዳሜ እኩለ ቀን ገደማ “ለድምጺ ወያኔ” ቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ቃለ ምልልስ፤ የትግራይ ኃይል “በምጽዋ እና አስመራ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን ለማምከን የሚያስችሉ የሚሳኤል ጥቃቶችን እንደሚያደርግ” አስጠንቅቀው ነበር።
የትግራይ ሴንትራል ኮማንድ ቃል አቃባይ መሆናቸው የተነገረላቸው አቶ ጌታቸው፤ “ከኤርትራም ወገን ሆነ ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል የሚደረጉ ጥቃቶችን ለማምከን የሚያስችሉ የሚሳኤል የአጸፋ እርምጃዎችን መውሰድ የምንቀጥል መሆናችንን በዚህ አጋጣሚ መግለጽ እፈልጋለሁ” ሲሉ ለቴሌቪዥን ጣቢያው ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ መንግስት ዕውቅና የተነፈገውን የትግራይ ክልል መንግስትን በፕሬዝዳንትነት የሚመሩት ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል፤ የክልሉ ኃይሎች በአስመራ ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ዛሬ እሁድ ለ“ሮይተርስ” የዜና አገልግሎት አረጋግጠዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)