ባህር ዳር ለሶስተኛ ጊዜ በሮኬት ተመታች

ወደ ባህር ዳር ከተማ ዛሬ ሰኞ ህዳር 14 ንጋት ላይ ሮኬቶች መተኮሳቸውን የከተማይቱ ነዋሪዎች ለ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ሮኬቶቹ በከተማይቱ አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ መውደቃቸውንም ገልጸዋል።

አንድ የከተማይቱ ነዋሪ ተከታታይ የሆኑ ሁለት የሮኬቶች ድምጽ የሰሙት ከንጋቱ 12 ሰዓት ከ15 ገደማ እንደሆነ ተናግረዋል። የሮኬቶቹ ድምጽ ከዚህ ቀደም በለሊት ወደ ከተማይቱ ከተተኮሱት “አነስ ያለ” እንደነበርም ጠቅሰዋል።

የሮኬቶቹን መተኮስ በትግራይ እና አማራ ክልል አዋሳኝ ቦታ ከሚኖሩ ሰዎች በሰሙ ሶስት ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ድምጹን መስማታቸውን አስረድተዋል። ከትግራይ ክልል አቅጣጫ ተወነጨፉ የተባሉትን ሮኬቶች አይተው የደወሉላቸው በጠለምት ወረዳ የምትገኘው የደጃች ሜዳ ከተማ ነዋሪዎች መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በባህር ዳር የሮኬቱ መውደቅ ከተሰማ በኋላ የእሳት አደጋ ተሽከርካሪዎች ወደ አየር ማረፊያ ጣቢያው አቅጣጫ ሲሄዱ መመልከታቸውን የከተማይቱ ነዋሪ ገልጸዋል። የዛሬውን ክስተት በተመለከተ ከአማራ ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዩች ጽህፈት ቤት መረጃ ብንጠይቅም ጥቃት ስለመድረሱ ማረጋገጫ ማግኘት አልቻልንም።

በባህር ዳር ከተማ ላይ ከዚህ ቀደም በሁለት የተለያዩ ጊዜያት የሮኬት ጥቃቶች መፈጸማቸውን ይታወሳል። ለጥቃቶቹ ህወሓት ኃላፊነቱን ወስዷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)