በኤርትራ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በሀገሪቱ የሚገኙ ዜጎቹ በቤት ውስጥ እንዲቆዩ አሳሰበ። አሜሪካውያን አሁንም ጥንቃቄ እንዳይለያቸው እና የግድ አስፈላጊ ካልሆነ ጉዞ እንዳያደርጉም መክሯል።
ኤምባሲው ማሳሰቢያውን የሰጠው በአስመራ ለሚገኙ ዜጎቹ ዛሬ ሰኞ ህዳር 14 ምሽት ባሰራጨው የማስጠንቀቂያ መልዕክት ነው። ለማሳሰቢያው መነሻ ምክንያት የሆነው በኤርትራ መንግስት ባለስልጣናት ትዕዛዝ ለአስመራ ነዋሪዎች የተነገረ መልዕክት ነው።
የአሜሪካ ኤምባሲ ያገኛቸውን ሪፖርቶች ጠቅሶ እንዳስታወቀው በተወሰኑ የአስመራ ክፍል የሚገኙ የአካባቢ ጥበቃዎች፤ የከተማይቱ ነዋሪዎች ምሽቱን በቤታቸው እንዲያሳልፉ ነግረዋቸዋል። የአስመራ ከተማ ነዋሪዎች ከቤት ውጭ እንዳያንቀሳቀሱ የተነገራቸው በምን ምክንያት እንደሆነ ኤምባሲው የሰጠው ማብራሪያ የለም።
የኤርትራዋ መዲና ባለፈው ህዳር 5 ምሽት ከትግራይ ክልል በተወነጨፉ ሚሳኤሎች መመታቷ ይታወሳል። የሚሳኤል ጥቃቱን ያደረሰው የትግራይ ክልል ኃይል እንደሆነ የህወሓት አመራሮች በወቅቱ ገልጸው ነበር። የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት የሚሳኤል ጥቃቱን አጥብቀው መኮነናቸው አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)