የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ዛሬ ስብሰባ ሊያደርግ ነው

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ዛሬ ማክሰኞ ስብሰባ ሊያደርግ ነው። በቪዲዮ ኮንፍረንስ ይደረጋል የተባለው ይሄው ስብሰባ ለህዝብ ክፍት እንዳልሆነ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት የዲፕሎማቲክ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።

በተመድ የአልጀዚራ ዘጋቢ የሆነችው አማንዳ ፕራይስ፤ የምክር ቤቱ ስብሰባ “ኢ-መደበኛ ምክክር” እንደሆነ ከዲፕሎማቶች መስማቷን በትዊተር ገጿ ጽፋለች። የጸጥታው ምክር ቤት የስብሰባ ስርአትን የሚያውቁ አንድ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጭ እንዲህ አይነት ጉዳዮች የሚስተናገዱት ለዕለቱ የተያዘው አጀንዳ ከተጠናቀቀ በኋላ ባለው ጊዜ እንደሆነ ተናግረዋል። “ሌሎች ጉዳዮች” በመባል የሚታወቁት እኒህን መሰል ጉዳዩች የሚካሄዱትም በዝግ መሆኑንም አስረድተዋል።

የጸጥታው ምክር ቤት ለዛሬ በዋናነት ለመነጋገር የያዘው አጀንዳ፤ በኢራቅ ያለው የተባበሩት መንግስታት የእገዛ ተልዕኮን የተመለከተ እንደሆነ በተመድ ድረ ገጽ የወጣው የስብሰባ መርሃ ግብር ያሳያል። ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚነጋገረው ከዚህ ስብሰባ መጠናቀቅ በኋላ ሊሆን እንደሚችል የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጭ ጠቁመዋል። ስብሰባውን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም። 

የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት በትግራይ ክልል ስላለው ሁኔታ ለመነጋገር ስብሰባ ሲጠራ የአሁኑ የመጀመሪያው ነው። በትግራይ ክልል የተከፈተው ወታደራዊ ዘመቻ ዛሬ ሶስተኛ ሳምንቱን ይደፍናል። (በተስፋለም ወልደየስ- ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)