በማይካድራ ከተማ በተፈጸመው ጥቃት በትንሹ 600 ሰዎች መገደላቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ

በተስፋለም ወልደየስ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጥቅምት 30 በማይካድራ ከተማ የነበረው የሰዎች ግድያ “በስልጣን ላይ በነበረው የአካባቢው መስተዳድር የጸጥታ መዋቅር እና ሳምሪ በተባለ ኢ-መደበኛ የወጣቶች ቡድን” የተፈጸመ መሆኑን ገለጸ። በጥቃቱ በትንሹ 600 ሰዎች መገደላቸውን የገለጸው ኮሚሽኑ፤ “ትክክለኛው ቁጥር ከዚህ ሊበልጥ ይችላል” ብሏል። 

ኢሰመኮ ይህን ያለው የማይካድራውን ግድያ ጨምሮ በአብርሀጅራ፣ በሳንጃ፣ በዳንሻ፣ በሁመራ እና በጐንደር ከተማ ተዘዋውሮ ባደረገው ምርመራ፤ የደረሰበትን ግኝት በተመለከተ ዛሬ ማክሰኞ ህዳር 15 ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ ነው። የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ፤ በማይካድራ ከተማ የተፈጸመውን ጥቃት፤ ግድያ፣ ጉዳት እና ውድመት፤ “ግፍና ጭካኔ የተሞላበት፤ በሲቪል ሰዎች ላይ የተፈጸመ የጭፍጨፋ ወንጀል” ሲል ጠርቶታል። 

“በአካባቢው የነበረው የሚሊሽያና የፖሊስ ጸጥታ መዋቅር፤ ሳምሪ ከተባለ መደበኛ ያልሆነ የትግራይ ወጣቶች ቡድን ጋር በማበርና በመተባበር፤ በተለይ ‘አማሮች እና ወልቃይቴዎች’ ያሏቸውን የአካባቢው ነዋሪ ሲቪል ሰዎች፤ ከቤት ቤት እየዞሩና በየጐዳናው ላይ በገመድ በማነቅ፤ በስለት፣ በመጥረቢያ፣ በዱላ በመደብደብ ገድለዋል”

– የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)

በማይካድራ ከተማ የተፈጸመው ጥቃት “ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት” መሆኑን የገለጸው ኮሚሽኑ፤ የምርመራው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት፤ ድርጊቱ “በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል” (crimes against humanity) እና “የጦር ወንጀል” (war crime) ሊሆን እንደሚችል ማመላከቱን ገልጿል። ኮሚሽኑ “ዝርዝር ማስረጃዎቹን እና ወንጀሎቹን የሚያቋቁሙትን የሕግ እና የፍሬ ነገር ትንተና” ካደረገ በኋላ ዝርዝሩን በሙሉ ሪፖርቱ አጣርቶ የሚያቀርብ መሆኑን አስታውቋል። 

የኢሰመኮ ሪፖርት በከተማይቱ ለተፈጸመው ግድያ እና ውድመት ተጠያቂ ያደረገው፤ የአካባቢውን የሚሊሽያ እና የፖሊስ ጸጥታ መዋቅር እንዲሁም “ሳምሪ” በመባል የሚታወቀውን ኢ-መደበኛ የትግራይ ወጣቶች ስብስብን ነው። ሁለቱ አካላት ጥቃቱን  ያደረሱት የፌደራል የመከላከያ ሰራዊት ከተማይቱን ከመቆጣጠሩ በፊት መሆኑንም ሪፖርቱ አመልክቷል።  

በትግራይ ክልል መንግስት እና በፌዴራል መንግስት መካከል ጥቅምት 25 ቀን 2013 ውጊያ መጀመሩን ተከትሎ፤ በማይካድራ ከተማ በሚኖሩ፣ የትግራይ ተወላጅ ባልሆኑ ሰዎች ላይ “ከባድ ስጋት እና ተጽዕኖ ተከስቶ” እንደነበር የኮሚሽኑ ሪፖርት ገልጿል። ስጋቱ በተለይ የጸናው “በአማራ እና ወልቃይት ተወላጆች ላይ” መሆኑንም ጠቅሷል። 

የመከላከያ ሰራዊት ወደ ማይካድራ ለመግባት መቃረቡ ሲሰማ፤ ከማይካድራ የሚያስወጡ ሁሉም ኬላዎች መዘጋታቸውን ሪፖርቱ ያስረዳል። የትግራይ ክልል ልዩ ኃይል እንዳያጠቃቸው በመስጋት ሽሽት የገቡ ነዋሪዎችም፤ በከተማው አራት ዋና ዋና መውጫዎች በተቋቋሙ ኬላዎች ላይ በተሰማሩ ሚሊሽያዎች እና በ“ሳምሪ” የወጣቶች ቡድን  ተመልሰው ወደ ቤታቸው እንዲገቡ መገደዳቸውን ገልጿል።

ጥቃቱ ከመጀመሩ በፊትም “የከተማው ፖሊሶች የትግራይ ተወላጅ የሆኑና ያልሆኑ ሰዎችን ለመለየት መታወቂያ ካርድ እየተመለከቱ” የነዋሪዎን ማንነታቸውን ያጣሩ እንደነበርም አብራርቷል። የኢሰመኮ ሪፖርት ጥቃቱ በተጀመረበት ጥቅምት 30 በከተማይቱ የተከሰተውንም በዝርዝር አስፍሯል።

“[ወጣቶቹ] የጭፍጨፋ ግድያውን ሲፈጽሙ፤ በየመንገዱ መታጠፊያዎች አድፍጠው ይጠባበቁ የነበሩት ሚሊሽያዎች እና ፖሊሶች፤ ከጥቃቱ ለመሸሽ የሚሞክረውን ሰው በጥይት ተኩስ በመመለስ፤ የአጥቂውን ቡድን የጭፍጨፋ ግድያ በቀጥታ ይፈጽሙና ያስፈጽሙ ነበር”

– የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)

“በአካባቢው የነበረው የሚሊሽያና የፖሊስ ጸጥታ መዋቅር፤ ሳምሪ ከተባለ መደበኛ ያልሆነ የትግራይ ወጣቶች ቡድን ጋር በማበርና በመተባበር፤ በተለይ ‘አማሮች እና ወልቃይቴዎች’ ያሏቸውን የአካባቢው ነዋሪ ሲቪል ሰዎች፤ ከቤት ቤት እየዞሩና በየጐዳናው ላይ በገመድ በማነቅ፤ በስለት፣ በመጥረቢያ፣ በዱላ በመደብደብ ገድለዋል፣ የአካል ጉዳት አድርሰዋል፣ እንዲሁም ንብረት አውድመዋል” ሲል መንግስታዊው የሰብዓዊ መብት ተቋም በዛሬው መግለጫው ወንጅሏል።

ጥቃቱ በዋነኛነት የተፈጸመው “ሳምሪ” በሚባለው የወጣቶች ስብስብ መሆኑን የገለጸው የኢሰመኮ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት፤ በአንድ ቡድን በአማካይ ከ20 እስከ 30 በመሆን ለግድያ ይንቀሳቀሱ እንደነበር አመልክቷል። እያንዳንዱ ቡድንም በግምት ከሶስት እስከ አራት በሚሆኑ፣ መሳሪያ በታጠቁ ፖሊስ እና ሚሊሽያዎች ይታጀቡ እንደነበርም ሪፖርቱ ጠቁሟል። 

“[ወጣቶቹ] የጭፍጨፋ ግድያውን ሲፈጽሙ፤ በየመንገዱ መታጠፊያዎች አድፍጠው ይጠባበቁ የነበሩት ሚሊሽያዎች እና ፖሊሶች፤ ከጥቃቱ ለመሸሽ የሚሞክረውን ሰው በጥይት ተኩስ በመመለስ፤ የአጥቂውን ቡድን የጭፍጨፋ ግድያ በቀጥታ ይፈጽሙና ያስፈጽሙ ነበር” ሲል ኢሰመኮ በሪፖርቱ ከስሷል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ የተወሰኑ የትግራይ ተወላጆች በማይካድራ ከተማ በጥቃት ፈጻሚዎች ሲሳደዱ የነበሩ ሰዎች ህይወት ማትረፋቸውን አውድሰዋል  

ኮሚሽኑ የትግራይ ወጣቶች ስብስብ “ከባድ ወንጀል” ፈጽመዋል ሲል ቢከስስም፤ ሌሎች የትግራይ ተወላጆች ደግሞ በተቃራኒው የአካባቢውን ነዋሪዎች ህይወት ማትረፋቸውን በበጎ ጎኑ ጠቅሷል። የትግራይ ተወላጆች፤ በጥቃት ፈጻሚዎች ሲሳደዱ የነበሩ ሰዎችን “በቤታቸው፣ በቤተክርስቲያን እና በእርሻ ቦታ ደብቀው በመሸሸግ” እንደታደጓቸው በምስክሮች ጭምር መረጋገጡን ኮሚሽኑ ገልጿል። ይህንን የሰው ህይወት የማዳን ተግባር፤ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ አውድሰዋል።   

“በማይካድራ ከተማ በአነስተኛ ጽንፈኛ ቡድን የተፈጸመው በብሔር ማንነት ላይ የተመሰረተ እጅግ ዘግናኝ ኢ-ሰብዓዊ ወንጀል ልብ ሰባሪ ቢሆንም፤ በአንጻሩ ኢትዮጵያውያን በብሔር ሳይለያዩ አንዱ የሌላው ጠባቂ ሆነው መታየታቸው ልብ ይጠግናል። ስለ ወደፊት በሰላም አብሮ መኖርም ተስፋ ይሰጣል” ብለዋል።

ዋና ኮሚሽነሩ “የተጐዱ ሰዎችን እና አካባቢዎችን መልሶ ማቋቋም እና መጠገን” እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል። ከዚህ በተጨማሪም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ “በሰብዓዊ መብቶች ወንጀል” የተሳተፉ ጥፋተኞችን በሕግ ፊት ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)