በተስፋለም ወልደየስ
በኤልቲቪ ቴሊቪዥን ጣቢያ ታቀርባቸው በነበሩ አነጋጋሪ ቃለ መጠየቆቿ የምትታወቀው ቤተልሔም ታፈሰ፤ የስራ እና የግል ህይወቷን የተመለከቱ ማስታወሻዎችን ያሰፈረችበት መጽሐፍ ለንባብ ሊበቃ ነው። “እኔ እና የኤልቲቪ ምስጢሮቼ” የተሰኘ ርዕስ የተሰጠው መጽሐፍ አሁን በማተሚያ ቤት የሚገኝ ሲሆን በሚቀጥለው ሳምንት መጀመሪያ ለገበያ እንደሚቀርብ ቤተልሔም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግራለች።
ደራሲዋ ከድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ እስከ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፤ ከጃዋር መሐመድ እስከ ጌታቸው ረዳ፣ ከዳውድ ኢብሳ እስከ እስክንድር ነጋ፣ ከሌንጮ ለታ እስከ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፣ ከአንዳርጋቸው ጽጌ እስከ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ያሉ እንግዶቿ ጋር የነበራትን ቆይታ እና የጀርባ ታሪኮች ይተርካል። ከአንዳንዶቹ ጋር የነበራትን ወዳጅነት እና ከእነርሱ ጋር ያሳለፈቻቸውን ጊዜያቶችም ያስቃኛል።
“[መጽሐፉ] የነበሩትን ቃለ- መጠየቆች በሙሉ አላካተተም፤ የተከታተላችኋቸውን ሙግቶች ቃል በቃል የመድገም አካሄድ የለውም። አነጋጋሪ የነበሩትን ብቻ መርጬ፤ ከእንግዶች ግብዣ ጀምሮ ምን እንደተፈጠረና ከስቱዲዩ ውጭ ያሉ ጉዳዮችን ሁሉ ለመዳሰስ ሞክሬያለሁ” ስትል ቤተልሔም በመጽሐፉ መግቢያ አስፍራለች።
ሃጫሉ ወደ ኤልቲቪ የቴሊቪዥን ጣቢያ ስቱዲዩ ለመግባት በር ላይ እንደቆመ፤ “ ‘የኦነግ አባል ነህ ወይ?’ ብለሽ ጠይቂኝ አለኝ” ትላለች ቤተልሔም። በወቅቱ ጥያቄው አስደንግጧት “እርግጠኛ ነህ?” ማለቷን እና ምን እንደሚጠቅመው እንዲነግራት መጠየቋን ታስታውሳለች። ቃለ መጠየቁ ከተጀመረ በኋላ ይኸው ጥያቄ ሲቀርብለት የኦነግ አባል “አይደለሁም” በማለት ፊቱን ቅጭም አድርጎ መመለሱን ታነሳለች። አመላለሱ እና ሁኔታው “ድንግርግር” አድርጓት እንደነበርም ጽፋለች።
የድምጻዊው ታሪክ ለራሱ ከተመደበለት ምዕራፍ በተጨማሪ፤ በመጽሐፉ ላይ ስለ ጃዋር መሐመድ በሚተርከው ክፍል ላይም ብቅ ይላል። ከባለታሪኩ ጋር የግል ትውውቅ የነበራት ቤተልሔም፤ “ሃጫሉን ሳውቀው፤ እንደ ቆቅ ንቁ ነው። እጅግ ተጠራጣሪ ባህሪ ቢኖረውም ድፍረቱ ደግሞ ልክ የሌለው የጀግና ባህሪ የተላበሰ ነው” ስትል በመጽሐፏ ትገልጻዋለች። ሃጫሉ ከመገደሉ ከአንድ ሰዓት በፊት ስልክ ደውሎላት እንደነበርም በመጽሐፏ ጠቅሳለች።
ለመጽሐፉ የጀርባ ሽፋን የተመረጡት ሁለተኛ ሰው የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ናቸው። ቤተልሔም አቶ ጌታቸውን ቃለ መጠይቅ ያደረገችላቸው ከካሜራ ባለሙያዎቿ ጋር መቐለ ከተማ ድረስ ተጉዛ ነበር። የቃለ መጠየቁን ቀረጻ ለመጀመር በዝግጅት ላይ እያለች አቶ ጌታቸው ላይ ያየችውን ነገር በመጽሐፏ ጀርባ ላይ አስፍራዋለች።
“በድንገት አቶ ጌታቸው ረዳ ደከምከም አላቸውና ትንፋሻቸው ቁርጥ ቁርጥ እያለ እጃቸውን ራሳቸው ላይ አደረጉ” ትላለች ቤተልሔም በመጽሐፏ። የእውቁ ፖለቲከኛ ሁኔታ ያሳሰባት ጠያቂዋ፤ “ደህና ነዎት አቶ ጌታቸው?” በማለት ጥያቄ ታቀርባለች። ሆኖም ለጥያቄዋ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ወደ ጠባቂያቸው መመልከታቸውን ታወሳለች። ጠባቂያቸው ዝም ማለቱን ተመልክታም “ውሃ ልስጥዎት?” ስትል በድጋሚ ትጠይቃለች። አሁንም አቶ ጌታቸው ምንም ባለማለታቸው በድንጋጤ ከተቀመጠችበት ተነስታ መቆሟን እና ከዚያ በኋላ የነበረውን ሁነት በመጽሐፏ በዝርዝር ከትባለች።
“እኔ እና የኤልቲቪ ምስጢሮቼ”፤ ደራሲዋ ከእንግዶቿ ጋር የነበራትን ይህን መሰል ቆይታ ብቻ ሳይሆን ተያያዥ ጉዳዩችን በማጠቀሻነት አንስቷል። ቤተልሔም ከአቶ ጌታቸው ቃለ መጠይቅ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ መቐለ በሄደችበት ወቅት ያጋጠማትን የነፍስ ውጪ፤ ነፍስ ግቢ ትዕይንት ምስል ከሳች በሆነ ሁኔታ ተርካለች። “የጃዋር መሐመድ ጠባቂዎች ሊነሱ ነው” ከተባለ በኋላ በተፈጠረ ብጥብጥ በርካታ ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ በእርሱ ቤት የነበረውን የሽምግልና ሂደት ምን ይመስል እንደነበር አስቃኝታለች።
መጽሐፉ በተለምዶ “አይነኬ” የሚባሉ ግላዊ ጉዳዮች ጭምር ተካተውበታል። ደራሲዋ “ከአንዳንድ ተጠያቂዎች ጋር የፍቅር ግንኙነት እንዳላት” እንደሚወራ በመጽሐፏ ጠቅሳ፤ ለውንጀላው ምላሿን ሰጥታለች። ቃለ ምልልስ እያደረገች ከአንድም ሁለቴ “የፍቅር ስሜት ተሰምቷት” እንደሚያውቅም ባልተለመደ ግልጽነት ትናዘዛለች።
“ምናልባት እንደዚያ የተሰማኝ፤ የሸሚዛቸውን ቁልፍ ከፈት በማድረጋቸውና ከፊል የደረታቸውን ክፍል በማየቴ ሊሆን ይችላል” ትላለች። ቤተልሔም በመጽሐፉ መግቢያ ላይ ያሰፈረችው መንደርደሪያ እንዲህ አይነት ታሪኮችን በመጽሐፉ ለምን ማካተት እንደፈለገች ጥቆማ የሚሰጥ ይመስላል።
“በዚህ ጽሑፍ ድካሜን፣ ስህተቴን እና ሽንፈቴን እንዲሁም ጥንካሬዬን አምኛለሁ። ወደፊት የሚመጡ አዳዲስ የሚዲያ ሰዎች ከድክመቴም፣ ከብርታቴም እንዲማሩበት፣ ሴቶች ቀና እንዲሉ፣ ልጆች ተስፋ እንዲያደርጉና ያም ከሚዲያ ሕይወቴ ጋር የተያያዘው አነጋጋሪ ታሪክ እንዳይረሳ በማሰብ ቀርቧል”
– ቤተልሔም ታፈሰ (“እኔ እና የኤልቲቪ ምስጢሮቼ”)
“በዚህ ጽሑፍ ድካሜን፣ ስህተቴን እና ሽንፈቴን እንዲሁም ጥንካሬዬን አምኛለሁ። ወደፊት የሚመጡ አዳዲስ የሚዲያ ሰዎች ከድክመቴም፣ ከብርታቴም እንዲማሩበት፣ ሴቶች ቀና እንዲሉ፣ ልጆች ተስፋ እንዲያደርጉና ያም ከሚዲያ ሕይወቴ ጋር የተያያዘው አነጋጋሪ ታሪክ እንዳይረሳ በማሰብ ቀርቧል” ስትል ጽፋለች።
ቤተልሔም በተደጋጋሚ ከተተችባቸው ጉዳዩች አንዱ በሆነው በዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ቃለ-መጠየቅ የተካተተበትን ቪዲዮ በምሳሌነት በማንሳት ስህተት መስሯቷን አምና ትቀበላለች። ጉዳዩ በወቅቱ ሲነሳላት “ምንም አይነት መጸጸት” አለማሳየቷን አስታውሳ፤ በስተኋላ ላይ በደረሰችበት መረዳት ግን ትችቱ “አግባብነት ያለው” መሆኑን ታምናለች።
“መጽሐፉ ራሴን ለማስተዋወቅ ወይም ምን ያህል የዋህ እንደሆንኩ ለማሳመን አሊያም ደግሞ በእኔ ላይ ያላችሁን የትኛውንም አይነት ሃሳብ ለመቀየር ታልሞ የተዘጋጀ መጽሐፍ አይደለም” ስትል በመግቢያዋ ላይ የምታሳስበው ቤተልሔም፤ “ስለ እኔ እስከፈለጋችሁት ድረስ እንድታስቡ፤ እንድትወዱኝም ሆነ እንድትጠሉኝ፤ እንድትቀልዱብኝና እንድትተቹኝ ተፈጥሮ የሰጠቻችሁ ነጻነት ስላለ፣ እኔ ከአመለካከታችሁ ጋር የምገጥመው ግብግብ የለኝም” በማለት የአንባቢዋቿን የተለያዩ ምልከታዎች እንደምታከብር ጠቁማለች።
የጋዜጠኝነት ሙያ በልጅነቷ ትመኛቸው ከነበሩ የስራ መስኮች መካከል አንዱ እንደነበር በመጽሐፏ የምትጠቅሰው ቤተልሔም፤ የዝግጅቷ ተከታታዮች በጋዜጠኝነት መስፈርት መዝነው ትችት ቢያዥጎደጉዱባትም፤ እርሷ ራሷን እንደ ጋዜጠኛ እንደማትመለከት ታስረዳለች።
“እናንተ እንጂ፤ እኔ ራሴን ጋዜጠኛ ብዬ ጠርቼ አላውቅም። እኔ የተፈጠርኩት ለመጠየቅ ነው። ‘አይባልም፤ አይጠየቅም የሚባልን ጥያቄ ለመጠየቅ የተፈጠርኩ ጠያቂ ብቻ ነኝ” ትላለች። “ ‘ጋዜጠኛ’ን ከስሜ ፊት የደነቀራችሁት እናንተው [ሆናችሁ]፤ መልሳችሁ ደግሞ ‘ጋዜጠኛ አይደለችም’ ትሉኛላችሁ። አጃኢብ ነው!” ስትል ግርምቷን ታካፍላለች።
በ222 ገጾች የተዘጋጀው የቃለ መጠይቅ አድራጊዋ መጽሐፍ፤ የሚደመደመው ደራሲዋ “በስራና እና በሕይወት ጉዞዎቿ ታዘብኳቸው” በምትላቸው ምልከቷዎቿ ነው። “የዕውቀት ድርቅ”፣ “ህልሟን ፈቺ ያጣች አገር”፣ “የማይነኩ፡ ንኩ ባዮች”፣ “የአንድ አይነትነት ምኞት”፣ “ሴት አልባ ስኬት?” እና “ያለቁልፍ መክፈት?” በሚሉ ንዑስ ርዕሶች የተከፋፈሉት የቤተልሔም ትዝብቶች፤ ደራሲዋ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያሏትን አቋሞች፣ ትችቶች እና ምኞቶች ሰብስቦ ይዟል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)