እነ ጃዋር መሐመድ ለደህንነታቸው ሲባል የፍርድ ሂደታቸው የሚታይበት ቦታ እንዲቀየር ጥያቄ አቀረቡ

በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ጃዋር መሐመድ እና አቶ በቀለ ገርባ፤ ለደህንነታቸው ሲባል የፍርድ ሂደታቸው የሚታይበት ቦታ እንዲቀይር ጥያቄ አቀረቡ። ሁለቱ ተከሳሾች በደህንነት ስጋት ምክንያት ዛሬ አርብ፤ ህዳር 18 በነበረው የችሎት ውሎ ሳይገኙ ቀርተዋል።

በአቶ ጃዋር መሐመድ ስም በሚጠራው የክስ መዝገብ ስር የተካተቱ 24 ተከሳሾች ጉዳያቸው እየታየ የሚገኘው፤ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሕገ መንግስታዊና ጸረ ሽብር ችሎት ነው። በመዝገቡ በአንደኛነት እና ሁለተኛነት የሰፈሩት አቶ ጃዋር እና አቶ በቀለ፤ ሀገሪቱ አሁን ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ እና ቀደም ሲል በእነርሱ ላይ “በመገናኛ ብዙሃን ይቀርብ ነበር” ባሉት ፕሮፖጋንዳ የተነሳ፤ የደህንነት ስጋት እንዳለባቸው በጠበቆች በኩል ለችሎቱ ባቀረቡት ደብዳቤ አመልክተዋል።

ከጠበቆቻቸው አንዱ የሆኑት አቶ ከዲር ቡሎ ለ”ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት፤ ተከሳሾቹ “በእነርሱ ላይ አንድ ችግር ቢደርስ በሀገር ደህንነት ላይ ጭምር ችግር ሊያስከትል እንደሚችል” በደብዳቤያቸው ላይ ጠቁመዋል። በዚህም ምክንያት የፍርድ ሂደታቸው በታሰሩበት አቅራቢያ ባለ ቦታ እንዲካሄድ ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

የተከሳሾችን ጉዳይ የሚመለከተው ችሎት በማመልከቻው ላይ ከበላይ አካላት ጋር ተነጋግሮ ውሳኔ ለመስጠት ለታህሳስ 8፤ 2013 ቀጠሮ ሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)