ምርጫ ቦርድ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳን ነገ ይፋ ሊያደርግ ነው

በተስፋለም ወልደየስ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመጪውን ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ በነገው ዕለት ይፋ ሊያደርግ ነው። ቦርዱ በምርጫ የጊዜ ሰሌዳው ላይ ከ47 የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር ለመምከር ለነገ ስብሰባ ጠርቷል።

በአዲስ አበባው ራዲሰን ብሉ ሆቴል በሚካሄደው በነገው የምክክር መድረክ ላይ፤ የድምጽ መስጫ ቀንን ጨምሮ ዝርዝር የምርጫ ክንውኖችን የያዘ የጊዜ ሰሌዳ ለፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚቀርብ የቦርዱ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ሶልያና ሽመልስ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ባለፈው ዓመት መጨረሻ ሊካሄድ ቀን ከተቆረጠለት በኋላ በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ የተራዘመው ስድስተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ፤ በያዝነው ዓመት ግንቦት ወር መጨረሻ አሊያም ሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ እንደሚካሄድ ቦርዱ ቀደም ሲል ጠቁሞ ነበር።

በነገው የምክክር መድረክ ላይ፤ የድምጽ መስጫ ቀንን ጨምሮ ዝርዝር የምርጫ ክንውኖችን የያዘ የጊዜ ሰሌዳ ለፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚቀርብ የምርጫ ቦርድ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ሶልያና ሽመልስ ተናግረዋል

ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ ይፋ ተደርጎ የነበረው የቦርዱ የጊዜ ሰሌዳ፤ መራጮች ድምጽ የሚሰጡበት ቀን ነሐሴ 23፤ 2012 እንዲሆን ወስኖ ነበር። ቦርዱ የተረጋገጠ የምርጫ ውጤት ከምርጫው ማግስት አንስቶ እስከ ጳጉሜ 3፤ 2012 አሳውቃለሁ ብሎ የነበረ ቢሆንም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በምርጫ 2012 ላይ የደቀነውን ችግር በመገምገም ያወጣውን የጊዜ ሰሌዳ መሰረዙ ይታወሳል። 

ቦርዱ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ምርጫውን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ማካሄድ እንደማይችል ማሳወቁን ተከትሎ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጓቸው ስብሰባዎች በ2012 ዓ.ም. ሊካሄድ የነበረው ምርጫ እንዲራዘም ውሳኔ ማሳለፋቸው ይታወሳል። ሆኖም ከወራት ቆይታ በኋላ፤ የጤና ሚኒስቴር “የኮሮና ወረርሽኝ ባይጠፋም፣ ቅድመ ሁኔታዎች ከተሟሉ፣ በዚህ ዓመት ጠቅላላ ምርጫ ማካሄድ እንደሚቻል” ለተወካዮች ምክር ቤት ምክረ ሃሳብ በማቅረቡ፤ የምርጫ ዝግጅት እንዲጀመር በፓርላማ ተወስኗል። 

ከዚህ ውሳኔ በኋላ ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆነው ምርጫ ቦርድ፤ መጪውን ጠቅላላ ምርጫ በተመለከተ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባለፈው ጥቅምት ወር መጨረሻ ምክክር አድርጓል። በምክክር መድረኩ ላይ የተሳተፉ በርከት ያሉ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፤ “ከምርጫ በፊት የብሔራዊ መግባባት ውይይት መደረግ እንደሚኖርበት” በተደጋጋሚ ቢያነሱም ሀሳባቸው እስካሁንም ድረስ በመንግስት በኩል ተግባራዊ አልተደረገም።

በርከት ያሉ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፤ በጥቅምት ወር በተደረገ የምርጫ ቦርድ የምክክር መድረክ ላይ “ከምርጫ በፊት የብሔራዊ መግባባት ውይይት መደረግ ይኖርበታል” የሚል ሀሳብ አንጸባርቀው ነበር

ምርጫ ቦርድ በነገው ዕለት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በሚያደርገው ምክክር ላይ የሚቀርቡ ሀሳቦችን ለውሳኔዎቹ በግብዓትነት ሊጠቀም እንደሚችል የቦርዱ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ለነገው ምክክር የተጠሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች በተሻሻለው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አዋጅ የተቀመጡ መስፈርቶችን ማሟላታቸው የተረጋገጠላቸው እና የቴክኒክ መስፈርቶችን ለማሟላት በሂደት ላይ ያሉ 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች መሆናቸው ታውቋል። 

ምርጫ ቦርድ ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ ታህሳስ 12፤ 2013 ባወጣው መግለጫ ገዢው የብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ 40 የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚፈለግባቸውን መስፈርቶች የማጣራት ሂደታቸውን ያጠናቀቁ መሆናቸውን ገልጾ ነበር። ቦርዱ “ማሟላት ያለባቸውን ሰነዶች አላቀረቡም” ያላቸውን 26 የፖለቲካ ፓርቲዎችን መሰረዙን በዚሁ መግለጫው አስታውቋል። ፍቃዳቸው ከተሰረዙት ፓርቲዎች ውስጥ የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ የመላው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ንቅናቄ (መኢብን)፣  የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኦብኮ) እንዲሁም አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ይገኙብታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)