የመጪው ምርጫ ዕጣ ፈንታ በፖለቲካዊ ድርድር እንዲወሰን አብሮነት ጠየቀ

በሐይማኖት አሸናፊ

የሶስት ፓርቲዎች ጥምረት የሆነው “አብሮነት ለኢትዮጵያ አንድነት” የተሰኘው ስብስብ “መጪው ምርጫ መቼ እና እንዴት ይካሄድ?” ለሚለው ጥያቄ ብቸኛ መልሱ ፖለቲካዊ በመሆኑ ድርድር እንዲካሄድ ጥሪ አቀረበ። አሁን ባለው የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ “የሽግግር መንግስት ማቋቋም አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑ ግልፅ እየሆነ መጥቷል” ብሏል። 

የኢትዮጵያዊያን ሃገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሃን)፣ የኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) እና ህብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ህብር-ኢትዮጵያ) በጋራ የመሰረቱት ጥምረት ይህን ያስታወቀው እሁድ መጋቢት 27፤ 2012 ባወጣው መግለጫ ነው። ጥምረቱ መግለጫውን ያወጣው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነሐሴ 23 እንዲካሄድ እቅድ ተይዞለት የነበረውን አገራዊ ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል ማስታወቁን ተከትሎ ነው። 

ምርጫው ከተቆረጠለት ቀን እንዲራዘም ሲጠይቅ መቆየቱን ያስታወሰው የጥምረቱ መግለጫ አሁን “ምርጫው እንዳይራዘም ሲሰጡ የነበሩ ሕጋዊ ምክንያቶች ተሟጠው አልቀዋል” ብሏል። “ምርጫውን ለማራዘም የሚያስችል የሕግ ድንጋጌ የለም” የሚል ምክንያት ሲቀርብ እንደነበረ የጠቀሰው መግለጫው ሕጎች ባይፈቅዱም ከአገሪቷ ሁኔታ አንፃር እና ለህዝብ ደህንነት ሲባል ምርጫው እንዲራዘም ሲጎተጉት መቆየቱን ገልጿል። 

“በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት መሰረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስራ ዘመን አምስት አመት ብቻ ነው” ያለው የአብሮነት መግለጫ “ምክር ቤቱን በመበተንም ሆነ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ በማወጅ እድሜውን ማራዘም አይቻልም” ሲል አቋሙን አሳውቋል። ምርጫ ለማራዘም ሲባል የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ማወጅ ወይም የምክር ቤቱን እድሜ ለማራዘም ተብሎ ምክር ቤቱን መበተን፤ የህገ መንግስቱ ድንጋጌዎች አላማ እንዳልሆነም የጥምረቱ መግለጫ አብራርቷል።

“ምክር ቤቱን በመበተንም ሆነ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ በማወጅ እድሜውን ማራዘም አይቻልም”

“ለ 27 ዓመታት በተጭበረበረ ምርጫና አፈና፤ ላለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ ‘በአሻጋሪነት’ ስም ስልጣን ይዞ አገሪቱን በአግባቡ መምራት የተሳነው የትላንቱ ኢሕአዴግ፤ የዛሬው ብልጽግና ፓርቲ ከእንግዲህ በማንኛውም ስም እና ሰበብ ስልጣን ላይ የመቀጠል እድል ሊሰጠው አይገባም” ሲል “አብሮነት” በመግለጫው አፅንኦት ሰጥቷል። 

ሀገሪቱ ካገጠማት ህገ መንግስታዊ መፋለስ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጉዳት እና ይመጣል ተብሎ ከሚሰጋው ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመውጣት እና በቂ ዝግጅት የተደረገበት ምርጫ ለማካሄድ መፍትሄ ያለውን መግለጫው ጠቁሟል። እነዚህን ወቅታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ “አብሮነት” ያቀረበው ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት የማቋቋም ጥያቄ “አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑ ግልጽ እየሆነ መጥቷል” ብሏል ጥምረቱ።

“ምን ዓይነት የሽግግር መንግስት ይቋቋም? በማን እና እንዴት ሊቋቋም ይችላል? ዋና ሃላፊነት እና ተግባሩ ምን ይሆናል? ዕድሜው ስንት ነው?” የሚሉት ጥያቄዎች ግን “በመንግስት ብቻ ሳይሆን ሁሉን አቀፍ በሆነ አገራዊ የምክክር ሂደት ሊወሰን ይገባል” የሚል አቋም እንዳለውም ጥምረቱ ገልጿል። ከፖለቲካው ጉዳይ ይልቅ በአሁኑ ወቅት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው አንገብጋቢው የሀገሪቱ ችግር የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መሆኑን ጥምረቱ አሳስቧል። 

ለወረርሽኙ “ሙሉ ትኩረት መሰጠት አለበት” የሚል አቋሙን ያንጸባረቀው ጥምረቱ በሽታው በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ሀገራዊ ምክክር በአፋጣኝ እንዲጀመር ጥሪውን አቅርቧል። “ወረርሽኙን በብቃት መከላከላችን እርግጠኛ ከሆንን በኋላ በፍጥነት ሁሉን አቀፍ አገራዊ የምክክር ሂደት መጀመር እና አገራችንን ወደፊት ሊገጥማት ከሚችል ከፍተኛ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ አደጋ ሊታደጋት የሚችል ሁኔታ ይመቻች” ሲል ጥምረቱ ጠይቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)