በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ያለው አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ (ኤ. ኤም. ኤን) ቴሌቪዥን ጣቢያ ሃይማኖታዊ ስነ-ስርዓቶችን በቀጥታ ስርጭት ማስተላለፍ ጀመረ፡፡ ጣቢያው ስርጭቱን የጀመረው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታት በቤተ እምነቶች የሚደረጉ የሰዎች መሰባሰቦችን ለማስቀረት እንደሆነ የጣቢያው ምንጮች ገልጸዋል፡፡
የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ የጣቢያው ከፍተኛ አመራሮች ባስተላለፉት ውሳኔ መሰረት የሃይማኖታዊ ስነ-ስርዓቶችን ስርጭት የጀመረው ከትላንት አርብ፤ መጋቢት 25 ጀምሮ ነው፡፡ ጣቢያው በትላንትና ስርጭቱ ለጁምዓ የስግደት እና የጸሎት ስነ-ስርዓት የቀጥታ ሽፋን ሰጥቷል፡፡ ተመሳሳይ ስርጭቶች በነገው ዕለት እንዲካሄዱ መወሰኑን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው አንድ የጣቢያው ጋዜጠኛ ተናግረዋል። አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ዛሬ አመሻሹን በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጹ ይህንኑ ያረጋገጠ መረጃ አውጥቷል፡፡
“አዲስ ቴቪ” በተሰኘው የቀድሞ መጠሪያው ይበልጥ የሚታወቀው የቴሌቪዥን ጣቢያ ከነገ መጋቢት 27 ጀምሮ ዘወትር እሁድ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ የዕለተ ሰንበት ሃይማኖታዊ ክንዋኔዎችን እንደሚያስተላልፍ ኤ. ኤም. ኤን አስታውቋል፡፡ ለነገ ሃይማኖታዊ ስነ-ስርዓቶቻቸውን እንዲያሰራጩ መርኃ ግብር የተያዘላቸው የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያን እና የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት መሆናቸውን መገናኛ ብዙሃኑ ገልጿል፡፡ ስርጭቶቹ ከቴሌቪዥን በተጨማሪ በአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ የፌስ ቡክ ገጽም በቀጥ ይተላለፋሉ ተብሏል፡፡ (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)