የአዲስ አበባው ሃያት ሪጀንሲ ሆቴል በኮሮና ስጋት አገልግሎት አቋረጠ

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ምክንያት በአዲስ አበባ የሚገኘው የሃያት ሪጀንሲ ሆቴል ከዛሬ መጋቢት 28 ጀምሮ አገልግሎት መስጠት አቋረጠ። ሆቴሉ አገልግሎቱን ያቆመው ለቀጣዩ አንድ ወር ከ25 ቀን ነው። 

ዛሬ ረፋዱን መስቀል አደባባይ አጠገብ ባለው ሃያት ሪጀንሲ የተገኘው “የኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ የሆቴሉ ደንበኞች ከበር ላይ ሲመለሱ ተመልክቷል። ሆቴሉ በድረ ገጹ ባወጣው አጠር ያለ ማስታወቂያ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ መደበኛ አገልግሎቱን ላልተወሰነ ጊዜ ማቋረጡን አረጋግጧል። በዚህም ምክንያት የምግብ ቤት፣ የባር እና ሌሎችም አገልግሎቶችን እንደማይሰጥም ገልጿል። 

“የእንግዶቻችን እና የሰራተኞቻችን ደህንነት እና ጤንነት ሁሌም ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ነው” ያለው ሆቴሉ እንግዶችን የማስተናገድ ጥያቄ የሚቀበለው ከግንቦት 24፤ 2012 በኋላ እንደሆነ ጠቁሟል። በታህሳስ 2011 ተመርቆ ስራውን የጀመረው ሃያት ሪጀንሲ 188 መኝታዎች እና ስድስት ምግብ ቤቶችን በውስጡ የያዘ ሆቴል ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)