በኦሮሚያ ከተሞች የሕዝብ ትራንስፖርት በከፊል ስራ ጀመረ

በኦሮሚያ ክልል ሙሉ በሙሉ አገልግሎት እንዲያቆሙ ተደርገው የነበሩት የሕዝብ ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎች ዛሬ ሰኞ መጋቢት 28፤ 2012 በከፊል ወደ ስራ መግባታቸውን በተለያዩ የክልሉ ከተሞች ያሉ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ በተወሰኑ ከተሞች ተዘግተው የነበሩ የንግድ ቤቶችም ወደ አገልግሎት መመለሳቸውን ገልጸዋል። 

በአዳማ እና ቢሾፍቱ ያሉ ነዋሪዎች ለ”ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት ባለ ሶስት እግር ተሸከርካሪዎች አንድ ሰው ብቻ እንዲጭኑ እንዲሁም ሚኒባስ ታክሲዎች ከሙሉ አቅማቸው በግማሽ ብቻ እንዲንቀሳቀሱ ውሳኔ ተላልፏል፡፡ ውሳኔው ባለፈው አንድ ሳምንት በተሽከርካሪዎች ስራ ማቆም ለእንግልት መዳረጋቸውን ለገለጹት የሁለቱ ከተማ ነዋሪዎች እፎይታን ፈጥሯል።

ነዋሪዎቹ መሰረታዊ ፍጆታዎችን ለመግዛት በእግራቸው ረጅም ርቀት ከመሄድ ባሻገር የግል መስሪያ ቤቶች ስራ ባለማቆማቸው ሰራተኞች በእግራቸው ወደ ስራ ቦታ ሲጓዙ መሰንበታቸውን ገልፀዋል፡፡ በመጓጓዣ ላይ ከተጣለው የእንቅስቃሴ እግድ በተጨማሪ በአዳማ የተወሰኑ ንግድ ቤቶች እንዲዘጉ ተደርገው እንደነበር አስረድተዋል። በከተማይቱ ተዘግተው የቆዩ የንግድ ቤቶች ዛሬ ወደ ስራ መግባት መጀመራቸውንም አክለዋል፡፡ 

የኦሮሚያ ክልል ቀደም ሲል ያስተላለፈው ውሳኔ ላይ ማሻሻያዎች ቢያደርግም በደቡብ፣ በአማራ እና በትግራይ ክልል ግን ተመሳሳይ እርምጃዎች አለመወሰዳቸውን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ማረጋገጥ ችሏል፡፡ (በሐይማኖት አሸናፊ – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)