በሐይማኖት አሸናፊ
ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው የኮሮና ቫይረስን አስመልክቶ የዘመሩት “ማረን” የተሰኘ አዲስ መዝሙር ዛሬ ይፋ ተደረገ። መዝሙሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዕይታ የበቃው በስማቸው በተከፈተው የዩቲዩብ ገጽ ላይ ነው።
“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በቀዳማዊ እመቤት ጽህፈት ቤት ካሉ ምንጮቿ ማረጋገጥ እንደቻለችው መዝሙሩ የተለቀቀበት የዩቲዩብ ገጽ የራሳቸው የወይዘሮ ዝናሽ ነው። ባለፈው ሳምንት የተዘጋጀው መዝሙር “የኮሮና ቫይረስ በዓለማችን መከሰት ጋር ተያይዞ የወጣ መሆኑን ተረድቻለሁ” ሲሉ የጽህፈት ቤቱ ምንጭ ተናግረዋል።
የዝማሬው ግጥም እና ዜማ በራሳቸው በቀዳማዊት እመቤቷ የተዘጋጀ ሲሆን ሃሙስ መጋቢት 24፤ 2012 በቤተ መንግስት መቀረጹን በመዝሙሩ የተሳተፉ ባለሙያዎች ተናግረዋል።
“በር ላይ ከነበረው ፍተሻ ውጪ ምንም አይነት የተለየ የሚያስጨንቅ አይነት ቁጥጥር አላጋጠመንም። በቀረፃ ወቅትም የተለየ ጥበቃ አልነበረም። ቀዳማዊት እመቤቷ እንደማንኛውም ዘማሪ ነበር የተቀበሉን” ሲሉ በመዝሙሩ ላይ የተሳተፉ አንድ ባለሙያ ለ”ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
መዝሙሩን ያቀናበረው ኤርሚያስ ሰንበቶ ሲሆን ሚክሲንግ እና ማስተሪንግ በንፁህ ይልማ መዘጋጀቱን ለማወቅ ተችሏል። በአጠቃላይ ስድስት ሙዚቀኞች በመዝሙሩ ላይ ተሳትፈዋል።
ቀዳማዊት እመቤት ከባለቤታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ጋር ኃላፊነት ከወሰዱ በኋላ በሚሊኒየም አዳራሽ አንድ ዝማሬ ማቅረባቸው የሚታወስ ሲሆን ከዚህ ቀደም በቤተክርስቲያን ውስጥም ያገለግሉ እንደነበር ይታወቃል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)