የመስቀል አደባባይ መልሶ ማልማት ግንባታ ተጀመረ

የመስቀል አደባባይ መልሶ ማልማት እና የአረንጓዴ ስፍራ ግንባታ ዛሬ ረቡዕ፤ መጋቢት 30፤ 2012 ተጀምሯል። መልሶ ግንባታው ስፍራውን ለህዝባዊ አደባባይነት በሚመጥን መልኩ ለማስተካከል ያለመ መሆኑን የአዲስ አበባ አስተዳደር ገልጿል። 

በከተማይቱ የከንቲባ ጽህፈት ቤት የበላይ ተቆጣጣሪነት በተጀመረው በአደባባዩ መልሶ ግንባታ እስከ 1,400 ተሽከርካሪዎች ለማቆም የሚያስችል የመኪና ማቆሚያ ግንባታ ይከናወናል ተብሏል። ግንባታው የውሃ ፏፏቴ እና የተለያዩ መዝናኛዎችንም እንደሚያካትት ተነግሯል። 

የመልሶ ግንባታውን ስራዎች የሚያከናውነው የቻይናው CCCC የተሰኘው ኩባንያ ነው። የኩባንያው ሰራተኞች ዛሬ መስቀል አደባባይን ከዋናው አውራ ጎዳና የሚለይ አጥር ለመገንባት ቆፋሮ ሲያደርጉ ታይተዋል። በስራው ላይ ቻይናውያን ባለሙያዎችም ተሳትፈዋል።

በመስቀል አደባባይ የመልሶ ግንባታው ከመጀመሩ ሳምንታት አስቀድሞ አካባቢውን የማዘጋጀት ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል። ዙሪያውን በአደባባይ ጥግ ተሰቅለው የነበሩ ትላልቅ ማስታወቂያዎችም እንዲወርድ ተደርገዋል። የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ፤ ባለፈው ሐሙስ መጋቢት 24፤ 2012 ፤ ከሌሎች የስራ ኃላፊዎች ጋር በስፍራው ተገኝተው ቅድመ ዝግጅቱን ተመልክተው ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)