የኢትዮጵያ መንግሥት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እየተባባሰ በመምጣቱ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ ማወጁን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስታወቁ፡፡ አዋጁ በሀገሪቱ ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 መሠረት የተፈጸመ መሆኑንም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይም ሆነ ዝርዝር አተገባበሩ እንዴት እንደሆነ በይፋዊ የፌስ ቡክ ላይ ባወጡት መግለጫቸው ላይ አልጠቀሱም። “ይሄንን መሳይ ዐዋጅ ብዙ ሀገሮች ካወጁ ሰንብተዋል፡፡ እኛ እስክንዘጋጅና ሁኔታው የግድ እስኪለን ጠብቀናል፡፡ ጊዜው ሲጠይቅ ግን አውጀናል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው።
“ሀገርን ለማዳንና ትውልድን ለመታደግ ከዚህ በላይ ልንወስን እንደምችልም መታወቅ አለበት፡፡ ዜጎቻችንም ከዚህ በላይ ግዴታቸውን ለመወጣት ወገባቸውን አጥብቀው መጠበቅ አለባቸው” ሲሉም አሳስበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስታቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያወጀው በሀገሪቱ ህገ መንግስቱ መሰረት መሆኑንም አመልክተዋል። በመግለጫቸው የጠቀሱት የሕገ መንግሥት አንቀጽ ላይ የፌደራሉ መንግስት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመደንገግ ስልጣን እንዳለው ይደነግጋል።
በዚህ አይነት ሁኔታ የሚታወጅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሕገ መንግሥቱ መሰረት ተፈጻሚ የሚሆነው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ በሁለት ሶስተኛ ድምጽ ተቀባይነት ካገኘ እንደሆነ በሕገ መንግስቱ ተጽፏል። አዋጁ የተወካዮች ምክር ቤት በስራ ላይ ባልሆነበት ወቅት የሚታወጅ ከሆነ በአስራ አምስት ቀናት ውስጥ ለምክር ቤቱ መቅረብ እንዳለበትም ይጠቁማል።
የተወካዮች ምክር ቤት በኮሮና ቫይረስ ስጋት ሳቢያ መደበኛ ስብሳባዎቹን ላልተወሰነ ጊዜ እንደማያደርግ ከሶስት ሳምንት በፊት አስታውቆ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)