የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በመንግስት ያሉ ገደቦችን ያስቀራል ተባለ

በሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ የጸደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ በመንግስት ሥልጣን ላይ ያሉ ገደቦች ወይም የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን ተፈጻሚነት፤ ለጊዜው በተለየ ሁኔታ እንደሚያስቀር የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ። አዋጁ ከጸደቀበት ቀን አንስቶ ለአምስት ወር ተፈጻሚ ሆኖ እንደሚቆይ መስሪያ ቤቱ ይፋ አድርጓል።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የአስቸኳይ ጊዜ ድንጋጌውን አስመልክቶ ማምሻውን በሰጠው ማብራሪያ አዋጁ የወጣው የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ስርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ እንደሆነ ገልጿል። የአዋጁ አላማ ከቫይረሱ ስርጭት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ተጓዳኝ ተግዳሮቶችን አስመልክቶ፤ ለስራ አስፈጻሚው የመንግስት አካል፤ አስፈላጊውን እርምጃዎች የመደንገግ ስልጣን መስጠት እንደሆነም ጠቁሟል።

አዋጁ የታወጀው “መንግሥት የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን በሚወስድበት ጊዜ የተሻለ ነጻነት እና አቅም እንዲኖረው” በማሰብ እንደሆነ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አብራርቷል። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን “ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የሚወሰዱ እርምጃዎችን ለማሳለጥ እና ውጤታማ ለማድረግ ከተለመደው አሠራር እና ሕገ-መንግሥታዊ ማዕቀፍ ወጥቶ በልዩ ሁኔታ መንቀሳቀስ ይጠይቃል” ብሏል።

በዚህ መሰረትም የሚኒስትሮች ምክር ቤት “እንደሁኔታው እና እንደአስፈላጊነቱ” “ደንብ በማውጣት፣ የመብት እገዳዎችን ማድረግ እና እርምጃዎችን መውሰድ” እንደሚችልም አመልክቷል። ሆኖም ከዚህ ቀደም ተግባራዊ በተደረጉ አዋጆች ላይ በግልጽ ይሰፍሩ የነበሩ ገደቦች እና እርምጃዎች ዛሬ በጸደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ አለመካተታቸው በጠቅላይ አቃቤ ህግ ማብራሪያ ላይ ተገልጿል። 

“እነዚህን የመብት ገደቦች እና እርምጃዎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወስጥ ዘርዝሮ ማስቀመጥ ያልተቻለ፤ አስፈላጊ የሚሆኑት ገደቦች እና እርምጃዎች፤ ከጊዜ ጊዜ እና በሃገሪቱ ውስጥ ከቦታ ቦታም ሊለያዩ ስለሚችሉ ነው” ሲል ምክንያቱን አስረድቷል። 

አስፈላጊ የሆኑት ገደቦች እና እርምጃዎች “እንደወረርሽኙ ስርጭት የስፋት አድማስ እና እንደሚያስከትለው ጉዳት ሊለዋወጡ” እንደሚችሉ የሚገልጸው ማብራሪያው ዝርዝር እና ቋሚ የመብት እገዳዎችን እና እርምጃዎችን ከመዘርዘር ይልቅ የሚኒስትሮች ምክር ቤት “እንዳስፈላጊነቱ ተለዋዋጭ (flexible)” በሆነ ሁኔታ በየጊዜው በሚያወጣው ደንብ እንዲካተቱ በአዋጁ መደንገጉን ተንትኗል። 

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረት የተደነገጉ የመብት እገዳዎችን፣ እርምጃዎችን፣ የተላለፉ መመሪያዎችን ወይም ትዕዛዞችን ሆን ብሎ የጣሰ ግለሰብ ባእስር አሊያም በገንዝብ እንደሚቀጣ በጠቅላይ አቃቤ ህግ ማብራሪያ ተጠቅሷል። በዚህም መሰረት ድንጋጌዎችን ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም ሰው እስከ ሶስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም ከ1,000 ብር እስከ 200 ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ሊቀጣ እንደሚችል ተገልጿል።

አዋጁ የመብት እገዳዎችን እና እርምጃዎችን የማስፈጸም ስልጣን ለፌደራል፣ የክልል የሕግ አስከባሪ ተቋማት እና ሌሎች በሕግ ሥልጣን ላላቸው አካላት ይሰጣል ተብሏል። የህግ አስከባሪ ኃይሎች ይህን የሚያስፈጽሙት “ተመጣጣኝ ኃይል” በመጠቀም እንደሆነም በማብራሪያው ተመልክቷል ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)