በተስፋለም ወልደየስ
በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የመጀመሪያዋ ሰለባ የሆኑት የ60 ዓመት ኢትዮጵያዊት እናት የቀብር ስነ ስርዓት በድጋሚ ተከናወነ። የመጀመሪያው የቀብር ስነ ስርዓት ያለ ሟች ቤተሰብ እውቅና እንዲከናወን አድርገዋል የተባሉ አንድ የአዲስ አበባ ከተማ የየካ ክፍለ ከተማ ኃላፊም ከስራቸው መባረራቸውን ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ባለፈው እሁድ መጋቢት 27፤ 2012 ህይወታቸው ያለፈው ኢትዮጵያዊት እናት የመጀመሪያ የቀብር ስነ ስርዓት የተፈጸመው የዕለቱ ዕለት፣ ምሽት ሶስት ሰዓት ገደማ፣ በቀጨኔ የመቃብር ስፍራ ነበር። በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ እንዲገኙ ያልተደረጉት ቤተሰቦቻቸው ባቀረቡት ቅሬታ የሟች አስክሬን በነጋታው 10 ሰዓት ገደማ ከተቀበረበት ተቆፍሮ ወጥቶ፤ ከሁለት ሰዓት በኋላ በለቡ ገብርኤል ቤተክርስቲያን በድጋሚ መቀበሩን ጉዳዩን በቅርበት የተከታተሉ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች ገልጸዋል።
የመጀመሪያው የቀብር ስነ ስርዓት እየተካሄደ በነበረበት ወቅት የሟች ቤተሰቦች አስክሬን ተቀብለው ለመቅበር እስከ ምሽቱ አምስት ሰዓት በለቡ ገብርኤል ቤተክርስቲያን እየተጠባበቁ እንደነበር በቦታው የነበሩ ምንጭ ገልጸዋል። ቀብሩ በለቡ ገብርኤል እንዲካሄድ ቤተሰቦቻቸው የፈለጉት፤ ለ38 ዓመት በትዳር አብረዋቸው የቆዩ ባለቤታቸው ያረፉት በዚያ ቤተክርስቲያን በመሆኑ እንደነበር እኚሁ ምንጭ ተናግረዋል።
የሟች ቤተሰቦች ውሳኔያቸውን ለኤካ ኮተቤ ሆስፒታል አስተዳደር አሳውቀው ስምምነት ተደርሶ እንደነበር ጉዳዩን በቅርበት የተከታተሉት ምንጭ አስረድተዋል። “ሆስፒታል አስክሬን በሚሰጥበት ጊዜ እንደተለመደው እንደድሮው ለቤተሰብ አይሰጥም። ኮሮና አሁን የተለየ ነገር ስለሆነ ፕሮቶኮሉ ይታወቃል። በእነርሱ ቁጥጥር ስር ሆኖ ነው የሚሄደው። ግን የቤተሰብ ፍቃድ ተጠይቋል። ከሆስፒታሉ ጋር ‘የት ቤተክርስቲያን ይሁንላችሁ’ ተብሎ ውይይት [ጭምር] ነበር” ብለዋል።
ሆኖም ከዚህ በተቃራኒ ከቤተሰቦች እውቅና ውጭ ቀብሩ በሌላ ስፍራ መፈጸሙ የሟች ቤተሰቦችን እንዳሳዘነ እኚሁ ምንጭ አብራርተዋል። የ60 ዓመቷ እናት ለስድስት ቀናት በጽኑ ህሙማን መርጃ ውስጥ የቅርብ ክትትል ሲደረግላቸው ሆስፒታሉ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ግንኙነት እንደነበረው እና የሚጠየቁትንም መድኃኒት ያቀርቡ እንደነበር ያስታውሳሉ። በስተመጨረሻም ለሆስፒታሉ የሬሳ ሳጥን ሁሉ ማቅረባቸውን እና ከአስተዳደሩ የተገባውን ቃል በማክበር በለቡ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ሲጠብቁ ቢቆዩም ስምምነቱ አለመከበሩን በቅሬታ አንስተዋል።
የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈጻሚ ዳዊት ኪዳኔ ግን የቀብር ስነ ስርዓቱ ከመጀመሪያው ጀምሮ የተዘጋጀው መንግስት ያወጣውን ፕሮቶኮል ተከትሎ እንደነበር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የእሁዱ ቀብር ስነ ስርዓት ከመሸ እንዲፈጸም የተደረገው ሆስፒታላቸው አስክሬን የሚያቆይበት “የማቀዝቀዣ ክፍል” ስሌለው እንደሆነ ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ህይወታቸውን የሚያጡ ግለሰቦችን በተመለከተ መንግስት ያወጣው ፕሮቶኮል የቀብር ስነ ስርዓቱ በ24 ሰዓት እንዲፈጸም ስለሚያዝዝ በዚያ መሰረት ተግባራዊ ማድረጋቸውን አብራርተዋል።
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለሚሞቱ ሰዎች የሚደረግ ጥንቃቄ እና የቀብር አስተዳደርን አስመልክቶ የተዘጋጀው ፕሮቶኮል በኮሮና ምክንያት የሞተ ግለሰብ አስክሬን የዕለቱ ዕለት ወደ ቀብር ስፍራ መወሰድ እንዳለበት ያዝዛል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ፕሮቶኮል አስክሬኑ ወደ ቤትም ሆነ ወደ ሃይማኖታዊ ቦታ መወሰድ እንደሌለበትም ያስጠነቅቃል። በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ የሚሳተፉ ስዎች ቁጥርም አነስተኛ መሆን እንዳለበት ያስቀምጣል።
በሟች ቤተሰብ ወገን ጉዳዩን በቅርበት የተከታተሉት የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጭ፤ ቤተሰብ ይህንኑ አውቆ፤ በዚያ መሰረት ተዘጋጅቶ እንደነበር ይገልጻሉ። “ቀብሩ የተለየ ቦታ ነው የሚፈጸመው። የተለየ ቦታ ማለት በየቤተክርስቲያኒያቱ ተክልሎ ያለ ቦታ ማለት ነው። ለቡ’ም ተወስዶ ሲቀበር በሌሎች ቦታዎች ላይ አይደለም የተፈጸመው። ለዚሁ ተከልሎ በተቀመጠ ቦታ ነው” ይላሉ።
የሟች ቤተሰቦች በዚህን መልኩ የመንግስትን ትዕዛዝ ተግባራዊ ቢያደርጉም የሆስፒታሉ አስተዳደር ግን ቃሉን አለመጠበቁ “በቤተሰብ ዘንድ ቅሬታን ፈጥሯል” ብለዋል። የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈጻሚ በበኩላቸው በሆስፒታላቸው ሲታከሙ የቆዩትን ታማሚ አስክሬን ቤተሰቦቻቸው ወደጠየቁበት ለቡ ገብርኤል ቤተክርስቲያን እንዲሄድ ለቀብር አስፈጻሚዎች ማስረከባቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ነገር ግን አስክሬኑ ከሆስፒታሉ ከወጣ በኋላ የመረጃ መጣረስ (miscommunication) መፈጠሩን አስረድተዋል።
“ለምን ቀጨኔ መድኃኒያለም እንደሄደ የማውቀው ነገር የለም” የሚሉት ዳዊት “እኔ መንገድ ላይ የተፈጠረን ችግር ማስተካከል አልችልም” ሲሉ ለዚህ ተጠያቂ የሚሆነው የቀብር አስፈጻሚው አካል እንደሆነ ጠቁመዋል።
እሁድ አመሻሹን በኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ተገኝተው የነበሩ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢዎች “የቀብር ስነ ስርዓት ይመለከታቸዋል” በተባሉ የተለያዩ አካላት መካከል አለመግባባቶች እንደነበሩ ታዝበዋል። የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስፈጻሚ የቀብር ጉዳይን ከሚከታተሉት የየካ ክፍለ ከፍለ ከተማ ኃላፊዎች ጋር ተደጋጋሚ የስልክ ልውውጥ ቢያደርጉም ቁርጥ ያለ መልስ ማግኘት አልቻሉም ነበር። ኃላፊዎቹ ለመዘግየታቸው ከሚሰጡት መልስ መካከል “ግብዐተ መሬቱን የሚፈጽሙ ወጣቶችን ለማግኘት ተቸግረናል” የሚል ነበር።
በዚህ የስልክ ልውውጥ መካከል ለአጀባ በአስቸኳይ ተጠርተው የመጡ፤ በሁለት መኪና የተጫኑ፤ የፌደራል ፖሊስ አባላት ከሆስፒታሉ ደጃፍ ለሰዓታት እንዲቆዩ ተገድደዋል። ከህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የመጡ የፈጣን ምላሽ ቡድን አባላትም እንዲሁ ለረጅም ጊዜ ሲጠብቁ ታይተዋል። አስክሬኑን ወደ ቀብር ስፍራ ለመውሰድ የተመደቡ የየካ ክፍለ ከተማ አምቡላንስ ሹፌር እና ባልደረባቸውም ጉዳዩ እልባት እስካገኘበት እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት ተኩል ድረስ ስራ ፈትተው ቆይተዋል።
በፌደራል ፖሊስ አባላት ታጅበው ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ግድም ወደ ቀብር ቦታ ማምራት የጀመሩት ሁለት አምቡላንሶች ድንገት ከመሃል መንገድ እንዲቆሙ ተደርጎ ስለቀብር ቦታው ምልልስ ሲደረግ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢዎች ተመልክተዋል። “የቀብር ቦታው የት ነው?” የሚለው ጥያቄ ላይ መደናገር ተፈጥሮም ነበር። ከጥቂት ቆይታ በኋላ ተሽከርካሪዎቹ ካቆሙበት ጉዟቸውን ቀጥለው ወደ ወደ ቀጨኔ የመቃብር ስፍራ አምርተዋል። የመጀመሪያው የቀብር ስነ ስርዓትም በዚያ ተፈጽሟል።
ለቀብር የተዘጋጀው ቦታ ለኮሮና ሰለባዎች በመንግስት የተዘጋጀ እንደሆነ ቢነገርም ግብዐተ መሬቱን የሚፈጽሙ ወጣቶች እንኳ ስለጉዳዩ እምብዛም እውቀት እንዳልነበራቸው ታይቷል። ወጣቶቹ እንደ አምቡላንስ ሹፌሩ እና ረዳቱ ሁሉ ራሳቸውን የሚሸፍኑበት የፕላስቲክ አልባሳት እንዲለብሱ ቢደረግም ስጋታቸውን በግልጽ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
የቀብር ስነ ስርዓቱ ከተጠናቀቀ በኋላ የተሰማው ግን ማንም ያልገመተው ነበር። የቀጨኔ የመቃብር ስፍራን ሲጠብቁ ለነበሩ የጸጥታ ኃይሎች አዛዥ የተነገራቸው፤ ከደቂቃዎች በፊት የቀብር ስነ ስርዓታቸው የተፈጸመው ኢትዮጵያዊት እናት ቤተሰቦች፤ በሌላ ቤተክርስቲያን ቀብር ለመፈጸም እየጠበቁ እንደሆነ ነበር።
ለጉዳዩ መፍትሄ እስኪያበጁ ድረስ በቀብሩ ላይ የተሳተፉት ሰዎችን በሙሉ፤ በመቃብር ስፍራው መግቢያ ላይ እንዲቆይ ያደረጉት አዛዡ፤ ከሚመለከታችው አካላት ጋር ለደቂቃዎች በስልክ ተወያይተዋል። የጊዜውን መምሽት እና ለባለሙያዎች በቂ አልባሳት አለመኖርን ከግምት ያስገቡት አዛዡ በስተመጨረሻ ሁሉም ወደ መጣበት እንዲመለስ ከውሳኔ ደርሰዋል።
እሁድ ምሽት የተፈጠረው ይህን ችግር የመንግስት ኃላፊዎች ከሰሙ በኋላ፤ የተፈጠረውን ለማወቅ፤ ይመለከታቸዋል የተባሉ አካላት በማግስቱ ስብሰባ ማካሄዳቸውን ጉዳዩን የሚያውቁ አንድ ምንጭ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በዚህ ስብሰባ ላይ ተሳትፈው እንደነበር የተጠየቁት የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈጻሚ እና ጥበቃ ላይ የነበሩት የጸጥታ ኃይሎ አዛዥ ግን ጭርሱኑ “ስብሰባው መደረጉን አናውቅም” ብለዋል።
በስብሰባው ላይ በተላለፈ ውሳኔ መሰረት፤ ለተፈጠረው ችግር ተጠያቂ ናቸው የተባሉ አንድ የየካ ክፍለ ከተማ የስራ መሪ፤ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ መደረጉን ስለ ስብሰባው የሚያውቁት ምንጭ ገልጸዋል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የእኚህን ኃላፊ ከስራ መባረር ከሌሎች ሁለት ምንጮች ብታረጋግጥም ኃላፊዋን አግኝታ ለማነጋገር ያደረገችው ሙከራ ግን ሳይሳካ ቀርቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)