የሚኒስትሮች ምክር ቤት የመብት እገዳዎችን የመደንገግ ስልጣን “ገደብ የለሽ አይደለም” ተባለ

በተስፋለም ወልደየስ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አማካኝነት የተሰጠው የመብት እገዳዎችን የመደንገግ ስልጣን ገደቦች እንደተጣሉበት ተገለጸ። ምክር ቤቱ የሚያወጣቸው ደንቦች እና የሚወስዳቸው እርምጃዎች የመንግስት ስያሜን፣ የኢ-ሰብዓዊ አያያዝ መከ’ልከልን፣ የእኩልነት መብትን እንደዚሁም የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መብቶችን “በማንኛውም ሁኔታ መገደብ አይችሉም” ተብሏል።

ይህ የተገለጸው የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ስርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማብራሪያ ላይ ነው። ማብራሪያው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማጽደቅ ዛሬ ሚያዝያ 2፤ 2012 በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት አዳራሽ ተሰብስበው ለነበሩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሰራጨ ነው። 

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያገኘችው ባለ 11 ገጽ ማብራሪያ እንደሚያስረዳው የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት “ልዩ ጥበቃ” ያደረገላቸው ድንጋጌዎች “በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውድ ውስጥ እንኳ ሊታገዱ አይችሉም”። ሕገ መንግስቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጅበትን ሁኔታ እና ስርዓት በተነተነበት አንቀጽ 93 ላይ ስለማይገደቡ መብቶች በግልጽ መዘርዘሩን ማብራሪያው አስታውሷል።

ባለ 106 አንቀጾች ከሆነው የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ውስጥ “ልዩ ጥበቃ” እንደሚደረግላቸው የተጠቀሱት አራት ድንጋጌዎች ብቻ ነው። ድንጋጌዎቹ ከሕገ መንግስቱ የመጀመሪያ አንቀጽ አንስቶ እስከ አንቀጽ 39 ድረስ ያሉ ናቸው። 

ከድንጋጌዎቹ አንዱ የሆነው እና በሕገ መንግስቱ አንቀጽ አንድ ላይ የተቀመጠው የኢትዮጵያ መንግስት ስያሜን የሚመለከት ነው። ሕገ መንግስቱ የኢትዮጵያ የመንግስት አወቃቀር ፌደራላዊ እና ዴሞክራሲያዊ መሆኑን እንደሚደነግግ በዚህ አንቀጽ ላይ ተቀምጧል።

በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት አንቀጽ 18 ላይ የሚገኘው እና ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ ስለመከልከሉ የሚዘረዝረው ክፍልም ሌላው ገደብ የማይጣልበት መብት መሆኑ ተገልጿል። ይህ አንቀጽ “ማንኛውም ሰው ጭካኔ ከተሞላበት፣ ኢ-ሰብዓዊ ከሆነ ወይም ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት አለው” ሲል ይደነግጋል። 

ሶስተኛው “ልዩ ጥበቃ” የሚደረግለት ድንጋጌ “የእኩልነት መብት” የተሰኘው ነው። በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 25 የተቀመጠው ይህ መብት “ሁሉም ሰዎች በሕግ ፊት እኩል ናቸው፤ በመካከላቸውም ማንኛውም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግ በሕግ እኩል ጥበቃ ይደረግላቸዋል” ይላል። ሁሉም ሰዎች ያለምንም ልዩነት፣ የሕግ ዋስትና የማግኘት መብት እንዳላቸውም ያትታል።  

የሕገ መንግስቱን አንቀጽ 39 የያዘው አራተኛው የማይገደብ ድንጋጌ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መብት ነው። የእዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማብራሪያ ላይ በጉልህ ተጠቅሰዋል። ንዑስ አንቀጽ 1 “ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከ መገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው” ይላል። 

ንዑስ አንቀጽ 2 በበኩሉ “ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ በቋንቋው የመናገር፣ የመጻፍ፣ ቋንቋውን የማሳደግ እና ባሕሉን የመግለጽ፣ የማዳበርና የማስፋፋት እንዲሁም ታሪኩን የመንከባከብ መብት አለው” ሲል ይደነግጋል።  

ባለ 106 አንቀጾች ከሆነው የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ውስጥ “ልዩ ጥበቃ” እንደሚደረግላቸው የተጠቀሱት አራት ድንጋጌዎች ብቻ ነው

ከተወካዮች ምክር ቤት አዳራሽ ውጭ በመካሄድ ታሪካዊ በሆነው በዛሬው የፓርላማ ስብሰባ ላይ የመብት ገደቦች እና እርምጃዎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለምን እንዳልተዘረዘሩ ጥያቄ ተነስቶ ነበር። “እነዚህን ገደቦች እና እርምጃዎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ዘርዝሮ ማስቀመጥ ያልተቻለው አስፈላጊ የሚሆኑት ገደቦች እና እርምጃዎች ከጊዜ ወደ ጊዜና በሃገሪቱ ውስጥ ከቦታ ቦታም ሊለያዩ ስለሚችሉ ነው” ሲል ማብራሪያው ምላሽ ሰጥቷል። 

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማብራሪያው ስለ መብት እገዳዎች እና እርምጃዎች ምንነትም አጠር ያለ ፍቺ አስቀምጧል። የመብት እገዳዎች ሲባል “በሕገ መንግስቱ ምዕራፍ ሶስት የተዘረዘሩትን መብቶች ተፈጻሚነት ወይም ህጋዊ ውጤት እንዳይኖራቸው ማድረግ ነው” ሲል ማብራሪያው ያስረዳል። የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ምዕራፍ ሶስት መሰረታዊ መብቶች እና ነጻነቶች የተዘረዘሩበት ነው።

የአዋጁ ማብራሪያ “እርምጃዎች መውሰድ ሲባል ምን ማለት ነው?” የሚለውንም ተመልክቷል። “እርምጃዎች መውሰድ ሲባል መብቶችን ከማገድ ጋር ቀጥተኛም ሆነ ተዘዋዋሪ ግንኙነት ያላቸው ውሳኔዎች፣ አስተዳደራዊ እርምጃዎች ወይም የሚሰጡ መመሪያዎች ወይም አቅጣጫዎች ሊሆኑ ይችላሉ” ብሏል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት የመብት እገዳዎቹ እና እርምጃዎቹን ዝርዝር ሁኔታ የመወሰን ስልጣን የተሰጠው ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቢሆንም ምክር ቤቱ ኃላፊነቱን ለዚህ ዓላማ ተብሎ ለተቋቋመ የሚኒስትሮች ኮሚቴ በውክልና ማስተላለፍ እንደሚችል በማብራሪያው ተጠቅሷል።  (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)