ከአምስት ቀናት በፊት የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ አንደሆኑ የተረጋገጠው እና በፅኑ ህሙማን መርጃ ውስጥ ክትትል ሲደረግላቸው የቆዩት የ65 ዓመት የዱከም ከተማ ነዋሪ አዛውንት ህይወት አለፈ፡፡
ግለሰቧ የውጪ ጉዞ ታሪክ ያልነበራቸው እና በቫይረሱ መያዙ ከተረጋገጠ ሰው ጋር የተረጋገጠ ግንኙነት እንዳልነበራቸው ሰኞ መጋቢት 28፤ 2012 ዓ.ም የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በሰጡት መግለጫ ገልፀው ነበር፡፡ ግለሰቧ በሌላ ተጓዳኝ ህመም ምክንያት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ተኝተው ሲታከሙ በነበረበት በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን የሚያሳዩ ምልክቶች በማሳየታቸው ምርመራ ተደርጎላቸው በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋገጧል ፡፡
ለታማሚዋ የሕክምና አገልግሎትን ሲሰጡ ከነበሩ በርካታ የጤና ባለሙያዎች መካከል በወቅቱ “አስፈላጊውን አልባሳት አልተጠቀምንም ወይም አጠቃቀማችን በቂ አይደለም” ያሉ ሰባት ባለሙያዎች ተለይተው ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ሆስፒታሉ በወቅቶ አስታውቆ ነበር፡፡፡፡ ከእነዚህ ባለሙያዎች መካከል ሁለቱ ታማሚዋን በቅርብ ሲከታተሉ የነበሩ ናቸው መባሉም ይታወሳል፡፡
የ65 ዓመቷ ታማሚ ከመጋቢት 28 ጀምሮ በኤካ ኮተቤ ሆስፒታል በጽኑ ህክምና ክፍል ክትትል ሲደረግላቸው መቆየቱን የተናገሩት ዶ/ር ሊያ ህይወታቸው ዛሬው ሚያዝያ 2 ማለፉን በትዊተር ገጻቸው ይፋ አድርገዋል፡፡ በኢትዮጵያ በአጠቃላይ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር 65 የደረሰ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ሶስቱ በበሽታው ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)