የሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዳፀቀው በተገለጸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈፀሚያ ደንብ መሰረት ማንኛውም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄዱ ስብሰባዎች ከአራት ሰው በላይ ማሳተፍ እንዳይችሉ እንዲሁም በአራቱ ሰዎች መካከል የሁለት የአዋቂ እርምጃ ርቀት እንዲጠበቅ መደንገጉን ጠቅላይ ዓቃቤ ህጓ አዳነች አበቤ ገለፁ፡፡ ቀብር እና ሌሎች አስፈላጊ ጉዳዮች ሲኖሩ ግን እየታዩ ይፈቀዳሉ ብለዋል፡፡
ደንቡ ማንም አሰሪ በዚህ ወቅት የስራ ውል ማቋረጥ ወይም ሰራተኛ መቀነስ እንደማይችል መከልከሉን ያስታወቁት ጠቅላይ ዓቃቤ ህጓ ሆኑም የቤት ኪራይን መቀነስ ወይም መተው ግዴታ ያለመሆኑን አመልክተዋል፡፡ ነገር ግን በደንቡ መሰረት ማንም አከራይ ተከራዩን በዚህ ወቅት “ማባረር አይችልም” ብለዋል፡፡
ታራሚዎች ስንቅ ከመቀበል ውጪ ማንንም በአካል የማያገኙ ሲሆን ከጠበቆቻቸው ጋር ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲነጋገሩ ግን ደንቡ ፈቅዷል፡፡ በአካል የመማር ማስተማር ሂደትን፣ ለአዋቂም ሆነ ለህፃናት በመጫወቻ ስፍራዎች ተገኝቶ መጫወትን የከለከለው ደንቡ በእጅ መጨባበጥ ሰላምታንም በህግ አግዷል፡፡ የአገር አቋራጭ መኪናዎች ከአቅማቸው በግማሽ ቀንሰው እንዲሰሩም አዝዟል፡፡
አራት ክፍሎች አሉት የተባለው የአስቸኳይ ጊዜ የማስፈፀሚያ ደንብ ክልከላን የሚያስቀምጥ፣ ግዴታ የሚጥል፣ የአስፈፃሚ አካላትን ክንውን እንዲሁም ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን የያዘ ነው፡፡ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የማስፈፀሚያ ደንቡን ከማብራራት ውጪ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ሙሉ ይዘቱን በይፋ አላሰራጨም፡፡ (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)