የሆሳዕና በዓል በተጨናነቀ ሁኔታ ተከብሮ ማለፉ ስጋትን ፈጥሯል 

በሐይማኖት አሸናፊ 

በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትላንት እሁድ ሚያዚያ 4፤ 2012 የተከበረው የሆሳዕና በዓልን ምዕመናን በብዛት ወደ አብያተ ክርስቲያናት በመሄድ በተጨናነቀ መልኩ አክብረው መዋላቸውን በደቡብ ክልል እና በኦሮሚያ ያሉ ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለፁ። ምንም እንኳን የየአብያተ ክርስቲያናቱ ወጣት አገልጋዮች ምዕመኑ አንድ ሜትር ያክል ተራርቆ በግቢ ውስጥ እንዲገለገል ቢያደርጉም ፀበል በመረጨት ወቅት እና ሃይማኖታዊ ስነ ስርዓቶቹ ከተጠናቀቁ በኋላ ወደ ቤት በመመለሻ ጊዜ መገፋፋቶች መታየታቸውን ተናግረዋል።

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ከተከሰቱት ሶስት ህልፈተ ህይወቶች መካከል አንዱን ያስተናገደችው የዱከም ከተማ ከፍተኛ መጨናነቅ ከታየባቸው ከተሞች አንዷ ነበረች። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው አንድ የከተማዋ ነዋሪ “በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ርቀትን ጠብቆ ለመቆም የሚቻል አልነበረም” ብለዋል። “በጣም ብዙ ሰው ግቢውን ሞልቶ ነበር፤ ወጣቶች ግን ርቀት ለማስጠበቅ ሲሞክሩ ታይተዋል” ሲሉም አክለዋል።

ከዱከም ከተማ በ10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የቢሾፍቱ ከተማ በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙ ምዕመን ከዚህ ቀደም እንደነበረው ባይሆንም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ መመልከታቸውን ተናግረዋል። ከበዓሉ መጠናቀቅ በኋላም የከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች በሰዎች ተጨናንቀው መስተዋላቸውን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ሌላ አንድ ነዋሪ ገልጸዋል። 

በወላይታ ሶዶ የሚኖሩ አንድ ምዕመን በበኩላቸው “ጸበል ለመረጨት ከፍተኛ ግፊያ እና መጠጋጋት ነበር” ብለዋል። ምዕመኑ ወጥቶ በሚሄድበትም ወቅት “በጋራ ተሰብስቦ ታይቷል” ሲሉ የዓይን እማኝነታቸውን ሰጥተዋል። ሕዝበ ክርስቲያኑ ሌሎች ስርአቶችን በሚታደምበት ወቅት ሁለት እርምጃ ተራርቆ በቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ ቢገለገልም ከአገልግሎቱ መጠናቀቅ በኋላ ግን ያ አለመቀጠሉን ነዋሪው አስረድተዋል።

“ህብረተሰቡ ለ2,000 ዓመታት ሲገነባው የቆየውን ይህንን የሃይማኖት ስነ ስርዓት ‘ተዉ’ ሲባል በቀላሉ ይለምደዋል ተብሎ አይጠበቅም”

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንም ይህንን ችግር ማስተዋሏን በቤተክርስቲያኑ የስብከተ ወንጌል እና ሃዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ኃላፊ መጋቢ ሰላም ሰለሞን ቶልቻ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ችግሩ “ከእውቀት ማነስ እና ካለመታዘዝ የመጣ ነው” ሲሉም አክለዋል።

“ህብረተሰቡ ለ2,000 ዓመታት ሲገነባው የቆየውን ይህንን የሃይማኖት ስነ ስርዓት ‘ተዉ’ ሲባል በቀላሉ ይለምደዋል ተብሎ አይጠበቅም” የሚሉት መጋቢ ሰላም ሰለሞን “ቤተክርስቲያንም መስቀል አትሳለሙ እስከሚል ከባድ ትዕዛዝ እስከመስጠት ስትደርስ ፈታኝ መሆኑን ሳትገነዘብ ቀርታ አይደለም” ይላሉ። 

“በሽታው መድሃኒት የለውም ቢባልም መጠንቀቅ መድሃኒት ነው” ያሉት ኃላፊው በመፅሃፍ ቅዱስ በመፅሃፈ ሲራክ ላይ ያለ ቃል ይሄንኑ ሀሳብ እንደሚያጠናክር ይገልጻሉ። ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስም “አለመታዘዝ በራሱ ጠንቅ መሆኑን አስረድቶናል” ሲሉም አጽንኦት ይሰጣሉ። 

የያዝነው ሳምንት የዐቢይ ፆም መጠናቀቂያ እንደመሆኑ “የተለያዩ ስነ ስነ ስርዓቶች ይከናወናሉ” ያሉት መጋቢ ሰላም ሰለሞን “ይህንን ምዕመኑ በቤቱ ውስጥ ሆኖ በመገናኛ ብዙሃን እንዲከታተል ቤተክርስቲያን ሰፊ ስራ ትሰራለች” ብለዋል። ይህም በክልል ከተሞች በተዋቀሩ መዋቅሮች በሰፊው የሚሰራ ይሆናልም ብለዋል።  

ከትናንት በስቲያ ሚያዚያ 3፤ 2012 ዓ.ም የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን ለመፈፀም የወጣው የሚኒስትሮች ምከር ቤት ደንብ ከአራት በላይ ሆኖ በአንድ ቦታ መሰብሰብን መከልከሉ የሚታወስ ነው። ክልከላው በሃይማኖታዊ እና አምልኮ ቦታዎች የሚደረጉ መሰባሰቦችን ይጨምራል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)