በተስፋለም ወልደየስ
በኢትዮጵያ የኮሮና ወረርሽኝ በዚሁ ከቀጠለ በሰኔ ወር መጨረሻ 33 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች በቫይረስ ሊጠቁ እንደሚችሉ አንድ የባለሙያዎች ጥናታዊ ግምት አመለከተ። ህብረተሰቡ አካላዊ ንክኪን በግማሽ መቀነስ ከቻለ የተጠቂዎችን ቁጥር ወደ 15 ሚሊዮን ገደማ ማውረድ እንደሚቻልም ጥናቱ ጠቁሟል።
“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ይህ ጥናት በኢትዮጵያ እና አዲስ አበባ ያለውን የኮቪድ 19 ስርጭት አካሄድ ገምግሞ መጪውን ጊዜ በግምታዊ ትንተና የተነበየ ነው። የጥናቱ የተወሰነ ክፍል ትላንት ሚያዝያ 4 ለንባብ በበቃው የጥቁር አንበሳ “የኢፒዲሞሎጂክ” አነስተኛ መጽሔት ላይ ታትሞ ወጥቷል።
በጥናቱ መሰረት የኮሮና ወረርሽኝ የከፋ ደረጃ ላይ ይደርሳል ተብሎ በሚገመትበት በመጪው ሰኔ ወር መጨረሻ 60 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ለቫይረሱ ሊጋለጥ ይችላል። እንደ ጥናቱ ከሆነ በመጪው ግንቦት ወር ብቻ 1.94 ሚሊዮን ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ይለከፋሉ።
ጥናቱ የኮሮና ወረርሽኝ የከፋ ደረጃ ላይ ይደርሳል በሚል ያስቀመጠው ግምታዊ ቀን ቫይረሱ በኢትዮጵያ መኖሩ ከተረጋገጠ ጀምሮ ባለው 110ኛ ቀን ላይ የሚከሰት ነው። በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ የተገኘው የዛሬ ወር፤ መጋቢት 4፤ 2012 ሲሆን ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ከተረጋገጠ 110ኛ ቀን የሚሞላው ደግሞ ሰኔ 24፤ 2012 ይሆናል።
በዚህ ቀን በኮሮና ቫይረስ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር ወደ 33 ሚሊዮን 697 ሺህ ገደማ እንደሚደርስ የባለሙያዎቹ ጥናት ይተነብያል። የቫይረሱ ስርጭት “ጣሪያ ይነካል” ተብሎ በሚጠበቅበት በዚህ ወቅት በህብረተሰቡ ዘንድ ያለውን ንክኪ በግማሽ መቀነስ ከተቻለ ወደ 15 ሚሊዮን ገደማ ሰዎችን በበሽታው እንዳይያዙ መታደግ እንደሚቻል ጥናቱ አሳስቧል።

በግምታዊ ሁኔታዎች ላይ ተመስርቶ በጤና ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባለፈው መጋቢት ወር የተዘጋጀ ሌላ ሰነድ 28 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ ሊያዙ እንደሚችሉ ግምቱን አስቀምጦ ነበር። በሁለቱ መንግስታዊ የጤና ተቋማት ያሉ ባለሙያዎች ከአዲስ አበባ እና ከጎንደር ዩኒቨርስቲ አቻዎቸው ጋር በጋራ ባደረጉት አዲስ ጥናት መሰረት ግን በቫይረሱ ሊጠቁ የሚችሉ ሰዎች ቁጥር በአምስት ሚሊዮን ጭማሪ ሊያሳይ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያገኘችው የመጋቢቱ ሰነድ ከከተማ ነዋሪዎች አጠቃላይ የህዝብ ብዛት ውስጥ 21 በመቶው በኮሮና ቫይረስ የመጠቃት አደጋ ያሰጋዋል። ይህም በቁጥር ሲገመት 23 ሚሊዮን እንደሆነ ሰነዱ ጠቆሞ ነበር። ትላንት ለንባብ የበቃው የባለሙያዎች ጥናት በበኩሉ የቫይረሱ ስርጭት ወደ ወረርሽኝ በሚያድግበት ወቅት ከአዲስ አበባ ህዝብ ውስጥ 50 በመቶ ያህሉ ለኮሮና ቫይረስ ሊጋለጥ እንደሚችል ስጋቱን አስቀምጧል።
በአዲስ አበባ በያዝነው የሚያዝያ ወር ብቻ በቫይረሱ የሚጠቁ ሰዎች ወደ 250 ሺህ ሊደርስ እንደሚችል የባለሙያዎቹ ጥናት ገምቷል። በቀጣይ ወር ውስጥ ይህ ቁጥር ወደ 1.4 ሚሊዮን ሊያሻቅብ ይችላል ብሏል ጥናቱ። በህብረተሰቡ ውስጥ ያለው ንክኪ በግማሽ መቀነስ ከተቻለ ግን 872,243 ሰዎችን ከበሽታው መከላከል እንደሚቻልም በጥናቱ ተመልክቷል።

በዓለም ጤና ድርጅት ምደባ መሰረት በኢትዮጵያ አሁን ያለው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ሁለተኛ ምዕራፍ ላይ መግባቱን ሰነዶች ያመለክታሉ። ይህ ምዕራፍ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ የሚመጣበት እና ስርጭቱ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች መሰራጨቱ የተረጋገጠበት ነው። በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች 74 መድረሳቸውን የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ዛሬ፤ ሰኞ ሚያዝያ 5 ባወጡት ዕለታዊ መግለጫቸው አስታውቀዋል።
በሀገሪቱ እስካሁን በምርመራ ውጤታቸው የተረጋገጡ አብዛኞቹ የኮሮና ቫይረሱ ተጠቂዎች ከውጭ ሀገር የተመለሱ እና በአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑ ናቸው። የቫይረሱ ተጠቂ ከአዲስ አበባ ውጭ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተገኘ ወዲህ በአማራ ክልል ባህር ዳር እና አዲስ ቅዳም እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ ተጨማሪ ታማሚዎች ተገኝተዋል።
ያለባቸውን ተጓዳኝ በሽታ ለመታከም ወደ አዲስ አበባው ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል መጥተው የነበሩ አንዲት የዱከም ከተማ ነዋሪ የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል። እኚህ የ65 ዓመት አዛውንት በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ ሶስተኛ ሰው ሆነዋል። እኚህ ኢትዮጵያዊት የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ የሌላቸው እና በቫይረሱ መያዙ ከተረጋገጠ ሰው ጋር ግንኙነት ያላቸው መሆኑ አለመረጋገጡን የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ መጋቢት 28 2012 ባወጡት መግለጫ ጠቁመው ነበር።
“ወረርሽኙ በቁጥጥር ስር ካልዋለ አሊያም የስርጭቱ ፍጥነት እንዲቀንስ ካልተደረገ የኢትዮጵያ የጤና ስርዓት ከፍተኛ ጫና ይደርስበታል። መወገድ የሚችል የበርካታ ሰዎች ሞት አይቀሬ ይሆናል”
የዓለም ጤና ድርጅት ሶስተኛው ምዕራፍ ብሎ በሚጠራው ወቅት ከሚታዩ ምልክቶች አንዱ ከዚህ ቀደም በኮሮና ቫይረስ ከተጠቁ ሰዎች ጋር ግንኙነት በሌላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ዘንድ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት መከሰት ነው። በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ በተደረጉ ምርመራዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ከተረጋገጠ ሶስት ሰዎች መካከል ሁለቱ የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክም ሆነ ከበሽታው ጋር ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው የጤና ሚኒስትሯ በዛሬው መግለጫቸው ዘርዝረዋል።
በጥቁር አንበሳ “የኢፒዲሞሎጂክ” አነስተኛ መጽሔት ላይ ትላንት የወጣ የባለሙያዎች ጽሁፍ ኢትዮጵያ በቅርቡ ወደ ሶስተኛው ምዕራፍ እንደምትሸጋገር አሳስቧል። “ወረርሽኙ በቁጥጥር ስር ካልዋለ አሊያም የስርጭቱ ፍጥነት እንዲቀንስ ካልተደረገ የኢትዮጵያ የጤና ስርዓት ከፍተኛ ጫና ይደርስበታል። መወገድ የሚችል የበርካታ ሰዎች ሞት አይቀሬ ይሆናል” ሲል ጽሁፉ ያስጠንቅቃል።
ይህ ሁኔታ ጥብቅ ክትትልን እና በሁሉም ደረጃ ዝግጁነት እንደሚጠይቅ ጽሁፉ ይመክራል። ዝግጁነቱ በሀገር አቀፍ እና በተቋማት ብቻ ሳይሆን በግለሰቦች ደረጃም እንደሚያስፈልግ የባለሙያዎቹ ጽሁፍ አስገንዝቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)