የዘንድሮ የትምህርት ካላንደር የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ከግምት በማስገባት ሊከለስ ነው

 በሐይማኖት አሸናፊ 

የትምህርት ሚኒስቴር በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ለመለየት እና ለመፍታት ያዘጋጀው ጥናት የትምህርት ዘመን ካላንደር ክለሳ አማራጮችን አቀረበ። ሚኒስቴሩ በመጋቢት ወር አዘጋጅቶ ያጠናቀቀው ይህ ጥናት የተለያዩ የቢሆን ትንተናዎችን በማስቀመጥ የተዘጋጀ ነው። 

ጥናቱ በመጀመሪያ የተመለከተው የቢሆን ትንተና፤ ከአንደኛ እስከ 11ኛ ክፍል ላለው የመማር ማስተማር ሥራ፤ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ከግንቦት 7፤ 2012 ዓ.ም በፊት በቁጥጥር ስር ቢውል መደረግ የሚችለውን ነው። የኮሮና ቫይረስ እስከ ግንቦት 7 ባለው በማንኛውም ጊዜ በቁጥጥር ስር ከዋለ፤ የመማር ማስተማር ሂደቱ ወዲያው ተጀምሮ እስከ ሰኔ 19፤ 2012 ዓ.ም ድረስ እንደሚቀጥል “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ባለ 23 ገፅ ሰነድ ያሳያል። 

በዚህ ወቅት ሁሉንም የትምህርት አይነቶች ማስተማር ተጨባጭ ስለማይሆን ለቀጣይ ክፍሎች መሰረታዊ የሆኑ የትምህርት አይነቶች እንዲሁም ይዘቶች ተመርጠው የሚሰጡ ይሆናል። ከአንደኛ እስከ 11ኛ ክፍል ያለውን በአምስት ደረጃዎች ከፋፍሎ የተመለከተው ሰነዱ በየደረጃው ከአራት አስከ ሰባት የሚሆኑ የትምህርት አይነቶች ተመርጠው እንዲሰጡ ያስቀምጣል። 

ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች የአፍ መፍቻ ቋንቋ፣ እንግሊዝኛ፣ ሒሳብ እና አካባቢ ሳይንስ ትምህርቶች ተመርጠው እንዲሰጣቸው ጥናቱ ምክረ ሀሳብ አቅርቧል። የአምስተኛ እና የስድስተኛ ክፍል ተማሪዎችም በተመሳሳይ አራት የትምህርት አይነቶች ላይ እንዲያተኩሩ የሚመክረው ሰነዱ አንግሊዝኛ፣ ሒሳብ፣ የተቀናጀ ሳይንስ እና የሕብረተሰብ ሳይንስ እንዲማሩ ይደረጋል ብሏል ። 

የሰባተኛ ክፍል ተማሪዎች እንዲወስዷቸው የታሰቡት ስድስት የትምህርት አይነቶች ሲሆኑ የተመረጡት ትምህርቶች ፊዚክስ፣ እንግሊዘኛ፣ ሒሳብ፣ ባዮሎጂ፣ ኬሚስትሪ እና ማሕበራዊ ሳይንስ ናቸው። የዘጠነኛ እና 10ኛ ክፍል ተማሪዎች የሰባተኛ ክፍል ተማሪዎች ከሚማሯቸው ትምህርቶች በተጨማሪ የታሪክ ትምሀርት የሚማሩ ሲሆን ባጠቃላይ ሰባት ትምህርቶችን በሁለት ወር እንዲያጠናቀቁ ይጠበቃል።

የትምህርት ሚኒስቴር ጥናት ለ11ኛ ክፍል ተማሪዎች የቢሆን ትንተናውን የሰራው የማሕበራዊ እና ተፈጥሮ ሳይንስ በሚል ለሁለት ከፍሎ ነው። የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች እንግሊዘኛ፣ ሒሳብ፣ ፊዚክስ፣ ባዮሎጂ እና ኬሚስትሪ እንዲማሩ ታስቧል። የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች አራት ትምህርቶችን እንዲወስዱ ሲጠበቅ እነዚህም እንግሊዝኛ፣ ሒሳብ፣ ጂዮግራፊ እና ታሪክ ናቸው። 

በጥናቱ የተለዩት እነዚህ የትምሀርት አይነቶች ሙሉ በሙሉ የማይሰጡ ሲሆን የተመረጡ ይዘቶች ተዘጋጅተው በስራ ላይ እንደሚውሉ የትምሀርት ሚኒስቴር ያዘጋጀው ሰነድ የመጀመሪያ የቢሆን ትንትና ያስረዳል። በዚህ የቢሆን ትንተና ላይ የተጠቀሱትን ተግባራት በታቀደው መሰረት መፈፀም ካልተቻለ የተወሰነው ወደ 2013 የትምህርት ዘመን ሊሸጋገር እንደሚችል ሰነዱ አመልክቷል።

ሁለተኛው የቢሆን ትንተና የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ከግንቦት 07፤ 2012 በፊት መቆጣጠር ካልተቻለ “የተጠቀሱትን ተግባራት በሙሉ ወደ 2013 የትምህርት ዘመን ማሸጋገር ግዴታ” እንደሚሆን ሲል ሰነዱ ያትታል። ሰነዱ ለ8ኛ ክፍል ተፈታኞች መፍትሄ ነው ያለውን አስቀምጧል። 

ተፈታኞቹ ለፈተና ሲቀመጡ የሚቀርብላቸው የ7ኛ እና የ8ኛ ክፍል የትምህርት ይዘት እንደሚሆን ሰነዱ ጠቁሟል። “ተማሪዎች ትምህርት እስካቋረጡበት ጊዜ ድረስ የሁለቱን ክፍሎች ትምሀርት ቢያስ 75 በመቶ ሸፍነዋል ተብሎ ይገመታል” ሲል ሰነዱ ለምክረ ሀሳቡ መሰረት የሆነውን አብራርቷል። ሰነዱ እስከ ግንቦት 21፤ 2012 ባለው ጊዜ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በቁጥጥር ስር ውሎ ትምህርት ቤቶች የሚከፈቱ ከሆነ ቀሪውን 25 በመቶ ትምህርት ለመሸፈን፣ ተማሪዎች በስነ ልቦና እና በፈተና አወሳሰድ ዙሪያ እንዲዘጋጁ ለማድረግ ጊዜ ይኖራል ይላል። 

በተባለው ጊዜ ትምህርት ቤቶች ስራ የማይጀምሩ ከሆነ ግን ተማሪዎች ያልተማሯቸው 25 በመቶ የሚሆነው ቀርቶ ፈተናው እንዲዘጋጅ እንደሚደረግ ይጠቁማል። ፈተናው ቀደም ብሎ ከተዘጋጀ፤ ካልተሸፈኑ የትምህርት ይዘቶች የወጡት ጥያቄዎች በሚታረሙበት ጊዜ እንዲዘለሉ እንደሚደረግ ያብራራል። በመጀመሪያው የቢሆን ትንተና መሰረት የ2012 የ8ኛ ክፍል ፈተና ከ ሰኔ 22 እስከ 24፤ 2012 ዓ.ም የሚሰጥ ይሆናል። 

የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተናን በተመለከተም ሰነዱ መደረግ ይችላሉ ያላቸውን አካሄዶችን አመላክቷል። የ11ኛ እና የ12ኛ ክፍል ትምህርት እስከ  75 በመቶው ያህሉ ተሸፍኗል ተብሎ የሚገመት መሆኑን የሚጠቅሰው ሰነዱ እስከ ግንቦት 28፤ 2012 ዓ.ም ባለው በማንኛው ጊዜ ትምሀርት ከተጀመረ ቀሪው 25 በመቶ እንደሚሸፈን ጠቁሟል። 

በተባለው ጊዜ ግን ትምሀርት የማይጀመር ከሆነ ግን እስከ አሁን በተሸፈነው ልክ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና እንደሚዘጋጅ ሰነዱ አመልክቷል። ፈተናው ያልተሸፈኑ የትምህርት ይዘቶችን ካካተተ ደግሞ በተመሳሳይ በእርማት ወቅት እንዲዘለሉ ይደረጋል ብሏል። “ባጠቃላይ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በስነ ልቦና እና በአንፃራዊነት ችግር መቋቋም የሚችሉ በመሆናቸው እና ፈተናው በአዲስ ቴክኖሎጂ የሚሰጥ በመሆኑ ፈተናው ከሐምሌ 7 እስከ 10፤ 2012 ዓ.ም የሚሰጥ ይሆናል” ሲል ሰነዱ ያስረዳል። 

ጥናቱ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው በትምህርት ዘመኑ ካላንደር፣ በተማሪዎች፣ በወላጆች እንዲሁም በመምህራን ስነልቦና ሊጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ከግምት ውስጥ ማስገባቱን አትቷል። የትምህርት ሚኒስቴር ጥናት ያቀረባቸው አማራጮች በከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች ዘንድ ደረጃ ውይይት እየተደረገባቸው መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጭ ተናግረዋል፡፡ ከሚመለከታቸው አካላት የሚደረገው ይህ ውይይት ሲጠናቀቅ “ውሳኔ ላይ ይደረሳል” ተብሎ እንደሚጠበቅም ምንጩ ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)