የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በሚል እንዲቋረጥ ተደርጎ የነበረው የሀገር አቋራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት ዛሬ ሐሙስ፤ ሚያዝያ 8 መጀመሩን የፌደራል የትራንስፖርት ባለስልጣን አስታወቀ። አገልግሎቱ የሚሰጠው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተቀመጡ ደንቦችንና መመሪያዎችን በጠበቀ ሁኔታ ብቻ እንደሚሆን መስሪያ ቤቱ ገልጿል።
የሀገር አቋራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት ዛሬ የተጀመረው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በሚያስተዳድራቸው እና በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙት ስድስት መናኸሪያዎች ነው። የሀገር አቋራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት ዛሬ የተጀመረው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በሚያስተዳድራቸው እና በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙት ስድስት መናኸሪያዎች ነው። በመናኸሪያዎቹ ተጓዦችን ከሚጭኑ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች በተጨማሪ መነሻቸው ከመስቀል አደባባይ የሆነ ዘመናዊ አውቶብሶችም ወደ ቀደመ አገልግሎታቸው ተመልሰዋል።
ዛሬ ከረፋዱ ጀምሮ፤ በርከት ያሉ ተጓዦች፤ መስቀል አደባባይ ጎን በሚገኝ የተሽከርካሪ ማቆሚያ ቦታ ላይ ተሰልፈው አውቶብሶችን ሲጠብቁ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ተመልክቷል። የፌደራል የትራንስፖርት ባለስልጣን ለሀገር አቋራጭ፤ ለአነስተኛ እና መለስተኛ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ዛሬ ባወጣው ማሳሰቢያ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ማድረግ የሚገቧቸውን ተግባራት የዘረዘረ ሲሆን ይህን ማድረግ ለማይችሉቱ ስምሪት መስጠት እንደሚቸገር ገልጿል።
የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎቹ ለአሽከርካሪዎች፣ ለረዳቶች፣ ለገንዘብ ተቀባዮች እና ለማህበራት ሰራተኞች ጓንት፣ የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል (ማስክ)፣ ሳኒታይዘር አሊያም አልኮል ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አሳስቧል። አገልግሎት ሰጪዎቹ የተሸከርካሪዎቻቸውን ስምሪት ከመውሰዳቸው በፊት ከየመናኸሪያው አስተዳደር ጋር በመሆን በህዝብ መጓጓዣዎቹ ላይ የኬሚካል ርጭት ማካሄድ አለባቸውም ብሏል።
የሀገር አቋራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ከሚያደርጓቸው የንጽህና መጠበቂያ ተግባራት በተጨማሪ የተሳፋሪዎችን የሙቀት መጠን በመለካት ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አስገንዝቧል። ህዝብ የማጓጓዝ አገልግሎቶቹ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተቀመጡ ደንቦችን እና መመሪያዎችን የተከተሉ መሆን እንዳለባቸውም መስሪያ ቤቱ አመልክቷል።
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የጸደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈጸሚያ ደንብ “ማንኛውም ሀገር አቋራጭ የህዝብ ትራንስፖርት የሚሰጥ ሰው በማንኛውም ጊዜ ከተሽከርካሪው ወንበር ብዛት 50 በመቶ በላይ ሰዎችን ጭኖ መንቀሳቅስ የተከለከለ ነው” ሲል ደንግጓል።
በደንቡ ላይ ከተቀመጠው ከዚህ ክልከላ ባሻገር፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ በሚሆንባቸው አምስት ወራት ውስጥ፤ የትራንስፖርት አጠቃቀም እና አሰጣጡ እንዴት እንደሚካሄድ የሚያስረዳ ዝርዝር መመሪያ መዘጋጀቱን የትራንስፖርት ሚኒስቴር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጿል። መመሪያው በዛሬው ዕለት እንደሚጸድቅም ሚኒስቴሩ አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[* በዚህ ዜና ላይ ተጨማሪ መረጃ እና ፎቶዎች ታክለውበታል]