ኢትዮጵያዊው ፎቶ ጋዜጠኛ ዓለም አቀፍ ሽልማት አሸነፈ

105

ኢትዮጵያዊው ፎቶ ጋዜጠኛ ሙሉጌታ አየነ በዘንድሮው የ“ወርልድ ፕሬስ ፎቶ” ዓለም አቀፍ ሽልማት ውድድር በአንድ ምድብ አሸነፈ። ሙሉጌታ ሽልማቱን ያሸነፈው ባለፈው ዓመት ቢሾፍቱ አቅራቢያ የተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላንን በተመለከቱ የፎቶግራፍ ስብስቦቹ ነው። 

ሙሉጌታ ስመ ጥር ለሆነው “ወርልድ ፕሬስ ፎቶ” ሽልማት የዘንድሮ ውድድር የታጨው በሶስት ምድቦች ነበር። የፎቶ ጋዜጠኛው “የዓመቱ ፎቶ” እና “የዓመቱ የፎቶ ታሪክ” ምድቦች ለመጨረሻ ዙር ካለፉ ስድስት ባለሙያዎች ተርታ ቢሰለፍም ሽልማቶቹን ሳያገኝ ቀርቷል። በዕጩነት በቀረበበት “የዋና ዜና የፎቶ ታሪክ” ምድብ በተካተቱ 10 የፎቶ ስብስቦች ግን በለስ ቀንቶታል። 

ከፎቶ ስብስቦቹ ውስጥ አብዛኞቹ በመጋቢት 2011 የመከስከስ አደጋ በደረሰበት አውሮፕላን ህይወታቸውን ያጡ መንገደኞች፤ ቤተሰቦች የደረሰባቸውን ጥልቅ ሀዘን በሚገባ ያሳዩ ናቸው። ሙሉጌታ ብዙዎቹን ፎቶዎች፤ ለሚሰራበት አለም አቀፍ የዜና ወኪል አሶሴትድ ፕሬስ ያነሳው፤ አደጋው በደረሰበት ስፍራ በመገኘት ነው። 

ለ63ኛ ጊዜ በተካሄደው በዘንድሮው ውድድር ከ125 ሀገራት የተውጣጡ 4,282 የፎቶ ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል። ለውድድር የቀረበላቸውን 73,996 ፎቶዎች የመዘኑት ዳኞች 44 የፎቶ ባለሙያዎች መርጠው ለመጨረሻ ዙር እንዲያልፉ አድርገዋል። ሙሉጌታን ጨምሮ ለሽልማት በዕጩነት የቀረቡት እነዚህ ፎቶግራፈሮች 24 ሀገራትን የወከሉ ነበሩ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)