ለጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ ለሁለተኛ ጊዜ ዋስትና ተፈቀደ

በተስፋለም ወልደየስ

በ“ሽብር ማነሳሳት” ወንጀል ተጠርጥሮ በእስር እንዲቆይ የተደረገው ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ የ30 ሺህ ብር ዋስትና ተፈቀደለት። ለጋዜጠኛው ዛሬ ሰኞ፤ ሚያዝያ 12፤ 2012 ዋስትናውን የፈቀደው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው።

ጋዜጠኛ ያየሰው በመጀመሪያ በቁጥጥር ስር የዋለው “የሀሰት መረጃ በማሰራጨት” ወንጀል ተጠርጥሮ ነበር። “ኢትዮ ፎረም” የተሰኘ በትግራይ ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ የሚተላለፍ ሳምንታዊ የቴሌቪዥን የቃለመጠየቅ መሰናዶ አዘጋጅ የሆነው ያየሰው በተመሳሳይ ስያሜ በሚጠራው “ዩ ቲዩብ ቻናሉ” ያሰራጨው መረጃ ለእስሩ ምክንያት ሆኗል። የጋዜጠኛው መረጃ መንግስት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት “200 ሺህ የቀብር ጉድጓዶች እንዲዘጋጁ አዝዟል” የሚል ነበር። 

መረጃው “ሀሰተኛ ነው” ያለው የፌደራል ፖሊስ በጉዳዩ ላይ ምርመራ ለማካሄድ፤ ለሁለት ጊዜያት ያህል፤ የስድስት ቀናት የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ተፈቅዶለት ነበር። ፖሊስ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባቀረበው ሌላ የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ፤ ጋዜጠኛውን “በሽብር ማነሳሳት” ወንጀል መጠርጠሩን ገልጾ፤ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት አመልክቷል። 

የያየሰውን ምርምራ ሲያከናውን የቆየው የፌደራል ፖሊስ፤ የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄውን ያቀረበው “ተጨማሪ ሰነዶችን ለማሰባሰብ እንዲሁም የምስክሮችን ቃል ለመቀበል” በሚል ነበር። ፖሊስ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ፤ ሚያዝያ 8፤ በነበረው ችሎት “የጋዜጠኛውን የገንዘብ ዝውውሮች ያሳያሉ” ያላቸውን ሰነዶች ከ18 ባንኮች ማጣራት እንደሚቀረው አስታውቋል። ከብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎትም ተጨማሪ ሰነዶች ለመሰብሰብ ይችል ዘንድ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቋል።        

የያየሰው ጠበቃ አቶ ታደለ ገብረመድህን “የጊዜ ቀጠሮ ሊሰጥ አይገባም” ሲሉ ጥያቄውን በሐሙሱ ችሎት ተቃውመዋል። ጋዜጠኛው “የሚያጠፋው ማስረጃ ስለሌለ፣ የምስክሮች ማንነት የማይታወቅ በመሆኑ እና የጤና ችግር ስላለበት” የጊዜ ቀጠሮው ውድቅ ሆኖ፣ የደንበኛቸው የዋስትና መብት እንዲከበር ጠይቀዋል። 

የግራ ቀኙን ክርክር የመረመረው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት፤ ፖሊስ ያቀረባቸውን ምክንያቶች አለመቀበሉን በዛሬው ውሎ አሳውቋል። ፖሊስ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ለማሰባሰብ ያቀዳቸውን የሰነድ ማስረጃዎች ተጠርጣሪው ሊያጠፋ የሚችልበት መንገድ ያልተገለጸ በመሆኑ ይህን ምክንያት ፍርድ ቤቱ አለመቀበሉን አሳውቋል። 

የሰዎች ምስክር ቃልም ቢሆን ፖሊስ “በጊዜ ሂደት እንቀበላለን” በሚል መናገሩን ያስታወሰው ፍርድ ቤቱ ይህም ምክንያት ለምርምራ የጊዜ ቀጠሮ ተቀባይነት እንደሌለው አብራርቷል። ፖሊስ በያየሰው ላይ የጠቀሰው የሽብር ወንጀል፤ “ጉዳት ለመድረሱ በግልጽ ያመለከተ ባለመሆኑ የጋዜጠኛውን የዋስትና መብት እንደማያስከለክልም” ፍርድ ቤቱ አስረድቷል። በዚህ መሰረት ተጠርጣሪው የ30 ሺህ ብር ዋስትና በማስያዝ ከእስር እንዲፈታ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል። 

ከመጋቢት 18፤ 2012 ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ ያየሰው የዋስትና መብት ሲፈቀድለት የአሁኑ የመጀመሪያ አይደለም። በመጀመሪያ በተጠረጠረበት ሀሰተኛ መረጃ የማሰራጨት ወንጀል፤ ምርመራ እየተካሄደ ባለበት ወቅት፤ የጊዜ ቀጠሮውን ጉዳይ ሲመለከት የቆየው ችሎትም ተመሳሳይ ውሳኔ አሳልፎ ነበር። 

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎትምጋዜጠኛ ያየሰው የ25 ሺህ ብር ዋስትና አስይዞ ጉዳዩን በውጭ እንዲከታተል ቢፈቅድም ፖሊስ በውሳኔው ላይ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብሏል። ጉዳዩን የተመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዋስትና መብቱን ቢያጸናም ጋዜጠኛው ከእስር ሳይለቀቅ ቆይቷል። ፖሊስ ጋዜጠኛውን በእስር ያቆየው በ“ሽብር ማነሳሳት ወንጀል ጠርጥሬዋለሁ” በሚል ምክንያት ቢሆንም ይፋዊ ክስ ግን እስካሁን አለማቅረቡን የጋዜጠኛው ጠበቃ አቶ ታደለ ገብረመድህን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)