የፌስቡክ የሶስተኛ ወገን መረጃ የማጣራት ስራ በኢትዮጵያ ሊጀመር ነው

ዓለም አቀፉ የማህበራዊ ትስስር ድረ ገጽ ፌስቡክ በሌሎች አፍሪካ ሀገራት እያካሄደ የሚገኘውን በሶስተኛ ወገን የሚካሄድ የመረጃ የማጣራት ስራ በኢትዮጵያም ሊጀምር መሆኑን ዛሬ አስታወቀ። መረጃ የማጣራት ስራው የፌስ ቡክ ተጠቃሚዎች ትክክለኛ ዜናዎችን እንዲያገኙ ከማገዙም ባሻገር በገጹ ላይ የሚስተዋለውን የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ለመቀነስ ያለመ ነው ተብሎለታል።

ፌስቡክ የመረጃ የማጣራት ስራውን ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በብሩንዲ እና ማሊም እንደሚጀመር ያስታወቀው ዛሬ ባወጣው መግለጫ ነው። የመረጃ ማጣራት ስራውን ከፌስ ቡክ ጋር በመሆን የሚያከናውነው መቀመጫውን በናይሮቢ ያደረገው “ፔሳ ቼክ” የተሰኘው ድርጅት መሆኑንም ገልጿል። 

“ፔሳ ቼክ” በየሀገራቱ የሚወጡ ጽሁፎችን፣ ፎቶዎችን እና ቪዲዮዎችን ትክክለኛነት የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ከሚሰጧቸውን ግብረ መልሶች ጋር በማቀናጀት የማጣራት ስራ ያከናውናል። ፌስ ቡክ ከድርጅቱ የሚያገኛቸውን ግብዓቶች በመጠቀም ሀሰተኛ የሆኑ ዜናዎች በመረጃ አጣሪዎች ዳግም እንዲታዩ ለማድረግ እንደሚጠቀምበት በዛሬው መግለጫ አስታውቋል።     

ፌስ ቡክ ይህን አይነቱን አሰራር ከሰሃራ በታች ባሉ 15 ሀገራት ሲተገብር ቆይቷል። የፌስቡክ የፐብሊክ ፖሊሲ ዳይሬክተር ኮጆ ቦአኬ የመረጃ የማጣራት ስራው ኢትዮጵያን ጨምሮ ሶስት የአፍሪካ ሀገራትን ማካተቱ ኩባንያው ለአህጉሪቱ ያለውን ቁርጠኛ አቋም ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል። “በፌስቡክ የሚደረጉ የሀሰተኛ ዜናዎች ስርጭትን የምንዋጋው ከፍ ባለ ኃላፊነት ነው” ሲሉም ኩባንያው ለጉዳዩ የሰጠውን ትኩረት አመላክተዋል።  (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)