ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት ተከሰሰ

በተስፋለም ወልደየስ

ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ በቅርቡ የጸደቀውን የሐሰተኛ መረጃን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ በመተላለፍ ዛሬ፤ ማክሰኞ ሚያዝያ 13፤ ክስ እንደተመሰረተበት የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ። የያየሰው ጠበቃ በበኩላቸው ጋዜጠኛው ዛሬ ወደ ፍርድ ቤት ቢወሰድም ችሎት ፊት አለመቅረቡን እና ክሱም እንዳልደረሰው ለ”ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዛሬ ከሰዓት በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ላይ ባወጣው መረጃ ያየሰው የተከሰሰው በአዋጁ የተከለከለውን የሐሰተኛ መረጃ ማሰራጨት የሚከለክለውን አዋጅ በመተላለፉ መሆኑን ገልጿል። በጋዜጠኛው ተጥሷል የተባለው የአዋጁ አንቀጽ “ማንኛውም ሰው የጥላቻ ንግግርን በብሮድካስት፣ በህትመት ወይም በማህበራዊ ሚዲያዎች ወይም በሌላ ተመሳሳይ ዘዴዎች አማካኝነት በጽሁፍ፣ በምስል፣ በድምጽ ወይም በቪዲዮ ማሰራጨት የተከለከለ ነው” ሲል ይደነግጋል። 

በክሱ ተጠቅሷል የተባለው ሌላኛው የአዋጁ አንቀጽ “የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ወንጀሉ የተፈጸመው ከአምስት ሺህ በላይ ተከታይ ባለው የማህበራዊ ድረ ገጽ ከሆነ ቅጣቱ እስከ ሶስት ዓመት የሚደርስ ቀላል እስራት እና ከመቶ ሺህ ብር ያልበለጠ መቀጮ ይሆናል” ይላል። ጠቅላይ አቃቤ ህግ ያወጣው የክስ ዝርዝርም፤ ያየሰውን ለክስ ያበቃ፤ በራሱ ስም በሚጠቀመው የፌስ ቡክ ገጽ አማካኝነት የተሰራጨ የሐሰት መረጃ እንደሆነ አመልክቷል።

ያየሰው መጋቢት 18 በቁጥጥር ስር ከመዋሉ አንድ ቀን አስቀድሞ “ኢትዮ ፎረም” በተሰኘ የ“ዩ ቲዩብ ቻናሉ” ያሰራጨው መረጃ መንግስት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት “200 ሺህ የቀብር ጉድጓዶች እንዲዘጋጁ አዝዟል” የሚል ነበር። ጋዜጠኛው ይህንኑ መረጃ በራሱ የፌስ ቡክ ገጽ ካጋራ በኋላ በርካታ ትችቶችን አስተናግዷል። ከሰዓታት በኋላ የፌስ ቡክ ገጹ መዘጋቱን በግል የትዊተር ገጹ ያስታወቀው ያየሰው “በዚህ ልክ አስደንጋጭ እንደሚሆን አልገመትሁም ነበር። በተፈጠረው ነገር ሁሉ ይቅርታ እጠይቃለሁ” ሲል የመጨረሻ ቃሉን አስፍሯል። 

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በበኩሉ “ተከሳሽ የመረጃውን ሐሰተኝነት እያወቀ ወይም ካለበት አጠቃላይ ሁኔታ አንፃር የመረጃውን እውነተኝነት ለማጣራት በቂ ጥረት ሳያደርግ ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ” የሐሰት መረጃን በጽሁፍ በማሰራጨቱ መከሰሱን ገልጿል። አቃቤ ህግ ያየሰው ተከስሶ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት መቅረቡን በመረጃው ቢጠቅስም የጋዜጠኛው ጠበቃ አቶ ታደለ ገብረ መድህን ግን ይህን አስተባብለዋል። 

ያየሰው ከስድስት ሰዓት ጀምሮ ልደታ ወደሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ተወስዶ በዚያው ቢቆይም ችሎት ፊት አለመቅረቡን ጠበቃው ለ”ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። እስከ ቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ደንበኛቸው በመኪና ውስጥ መቆየቱንም የተናገሩት ጠበቃው ይፋዊ ባልሆነ መንገድ ክስ እንደሚመሰረትበት ሲሰሙ መቆየታቸውንም አስረድተዋል። ከዘጠኝ ሰዓት በኋላ ደንበኛቸው ፍርድ ቤት ሳይቀርብ፣ ከመጋቢት 18 ጀምሮ ታስሮ ወዳለበት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በመወሰዱ ቅጽር ግቢውን ለቅቀው መውጣታቸውን አብራርተዋል። ያየሰው “መከሰሱንም የሰማሁት በፌስ ቡክ ነው” ብለዋል።

ጉዳዩን ለማጣራት ዘጠኝ ሰዓት ተኩል ገደማ ወደ ፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ያቀናው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ የችሎትም ሆነ የአቃቤ ህግ ጽህፈት ቤት ሰራተኞችን ማግኘት ሳይችል ቀርቷል። ሰራተኞቹ ከትላንት ጀምሮ ተግባራዊ በሆነው የፌደራል መስሪያ ቤቶች አዲስ የስራ ሰዓት መሰረት ከዘጠኝ ሰዓት ተኩል በኋላ በስራ ገበታቸው ላይ እንደማይገኙ ተገልጾለታል።  

በተመሳሳይ ቅጽር ግቢ ውስጥ የሚገኘው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት፤ በትላንትናው ውሎው ጋዜጠኛ ያየሰው በ30 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈታ ወስኖ ነበር። የጋዜጠኛው ቤተሰቦች እና ጓደኞች ለዋስትና ማስከበሪያ ማሟላት የሚገባቸውን ትላንት ከሰዓቱን ቢያጠናቅቁም “መርማሪው የለም” በሚል ሳይፈታ ማደሩን ገልጸዋል። ዛሬ ጠዋት የማስፈቻ ሂደቱን ካጠናቀቁ በኋላ “ጠብቁ” ተብለው መቆየታቸውን እና በስተመጨረሻ ወደ ፍርድ ቤት ሲወስዱት ክስ ሊመሰረትበት እንደሆነ መረዳታቸውን ተናግረዋል።   

ጋዜጠኛ ያየሰው ባለፈው ሳምንትም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በዋስትና እንዲፈታ ከተወሰነለት በኋላ ከእስር ሳይለቀቅ አድሮ በሽብር ወንጀል እንደሚፈልግ መገለጹ ይታወሳል። የያየሰውን ጉዳይ ሲመረምር የቆየው የፌደራል ፖሊስ ጋዜጠኛውን “በሽብር ማነሳሳት” ወንጀል መጠርጠሩን ገልጾ 14 የምርመራ ቀናት እንዲፈቀድለት ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት አመልክቶ ነበር።

ጉዳዩን የተመለከተው ችሎቱ የምርመራ ጊዜ ጥያቄውን ውድቅ አድርጎ፤ የጋዜጠኛው የዋስትና መብት ተከብሮ ከእስር እንዲፈታ ወስኖ ነበር። ጋዜጠኛ ያየሰው “ኢትዮ ፎረም” የተሰኘ በትግራይ ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ የሚተላለፍ ሳምንታዊ የቴሌቪዥን የቃለመጠየቅ መሰናዶ አዘጋጅ ሲሆን በተመሳሳይ ስያሜ የሚጠራ የራሱ “ዩ ቲዩብ ቻናል” አለው።  (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)