በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ የአዲስ አበባ ሆቴሎች በየወሩ 35 ሚሊዮን ዶላር ሊያጡ ይችላሉ ተባለ

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ በተጣለው የዓለም አቀፍ የጉዞ እገዳ ምክንያት በአዲስ አበባ ያሉ ሆቴሎች በወር 35 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ገቢ እንደሚያጡ የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማህበር ያካሄደው የዳሰሳ ጥናት አመለከተ። የማህበሩ አባል ከሆኑ 130 ሆቴሎች ውስጥ 88 በመቶ ያህሉ ሙሉ ለሙሉ አሊያም በከፊል ሊዘጉ እንደሚችሉ ጥናቱ ጠቁሟል። 

ዛሬ ረቡዕ ሚያዝያ 14 ይፋ የተደረገው የማህበሩ የዳሰሳ ጥናት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአዲስ አበባ የሆቴል እና መስተንግዶ ዘርፍ ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ የገመገመ ነው። በወረርሽኙ ሳቢያ በመዲናይቱ ያሉ ሆቴሎች ያሏቸው የመኝታ ክፍሎቻቸው እንግዳ የመያዝ መጠናቸው ክፉኛ ማሽቆልቆሉን ጥናቱ አሳይቷል።

መቶ ሰላሳዎቹ የማህበሩ አባል ሆቴሎች ያሏቸው የመኝታ ክፍሎች ብዛት 8,667 መሆኑን የዳሰሳ ጥናቱ ጠቅሷል። የመኝታ ክፍሎቹ በእንግዶች የመያዝ መጠን ባለፈው ዓመት 64 በመቶ እንደነበር ያስታወሰው ጥናቱ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ መጠኑ ከሁለት በመቶ በታች መውረዱን ገልጿል። 

በዚህም ምክንያት 88 በመቶ ያህሉ የማህበሩ አባላት ሙሉ ለሙሉ አሊያም በከፊል ሆቴሎቻቸውን ለመዝጋት መወሰናቸውን ጥናቱ ይፋ አድርጓል። በማህበሩ ጥላ ስር ከተሰባሰቡት ሆቴሎች ውስጥ 38 በመቶው ባለ ሶስት ኮኮብ ደረጃ ያላቸው ሲሆን 19 በመቶው ደግሞ ባለ አራት ኮኮብ ደረጃን የተጎናጸፉ ናቸው። ቀሪዎቹ በባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሚሰጠውን የደረጃ ምደባ በመጠባበቅ ላይ ያሉ ናቸው።

የማህበሩ የዳሰሳ ጥናት አባል ሆቴሎቹ ከመኝታ ክፍሎች፣ ከምግብ እና መጠጥ መስተንግዶ፣ ከሚሰናዱ ድግሶች እና ሌሎችም አገልግሎቶች በየወሩ ሊያገኙ ይችሉ የነበረውን 35 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ እንደሚያጡም ገልጿል። ሆቴሎቹ ከእነዚህ አገልግሎቶች የሚያገኙት ገቢ በዚሁ ከቀጠለ ከ15 ሺህ በላይ ለሆኑት ሰራተኞች ደሞዝ መክፈል ይቅርና ወጪዎቻቸውን እንኳ መሸፈን እንደሚያዳግታቸው አመልክቷል። የየሆቴሉ ባለቤቶች ሰራተኞቻቸውን እስከ መቀነስ ሊጓዙ እንደሚችሉም ጠቁሟል።

በአዲስ አበባ በአሁኑ ወቅት በራቸውን ለደንበኞች ክፍት ካደረጉ ሆቴሎች መካከል 12 በመቶው ከውጭ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ ለሚገቡ ተጓዦች በለይቶ ማቆያነት የሚያገልግሉ መሆናቸውን ጥናቱ አመልክቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)