የኮሮና ወረርሽኝ ያጠላበት የረመዳን ዋዜማ በድሬዳዋ

182

በሐይማኖት አሸናፊ 

ወትሮውንም ግርግር የማያጣት ድሬዳዋ በረመዳን ጾም መያዣም ምግብ፣ የቤት እቃ፣ ጭሳጭስ እና ሌሎች ለረመዳን ወር አስፈላጊ ነገሮችን በሚገበያዩ ነዋሪዎቿ ደምቃ ውላለች፡፡ በጾመኞች የሚዘወተሩት ሩዝ፣ አብሽ፣ ምስር፣ ቴምር፣ የተለያዩ ጁሶች፣ የስንዴ ዱቄት እና ጣፋጭ ምግቦች ዛሬ በድሬዳዋ ገበያ በሰፊው ሲገበዩ የነበሩ ናቸው፡፡ 

የረመዳን ፆም ከመግባቱ ከ10 ቀናት ጀምሮ ምንጣፍ፣ መጋረጃ፣ የፈዲ ወይም የሶፋ ልብሶች እንዲሁም የተለያዩ ትራሶችን የሚገዙ ነዋሪዎችን መመልከት የተለመደ እንደሆነ ከ10 ዓመታት በላይ በንግድ ስራ ላይ የቆዩት አብዱል ቀሃር አማን ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም የምግብ አስቤዛዎች ጾሙ በሚገባበት ሳምንት እንደሚሸመቱ በተለምዶ ታይዋን ተብሎ በሚጠራው የገበያ አዳራሽ አካባቢ በሚገኝ መደብር ውስጥ ሸቀጣ ሸቀጦችን በመሸጥ የሚተዳደሩት አብዱል ቀሃር ይጠቁማሉ፡፡ 

በድሬዳዋ ከተማ እስካሁን ድረስ ስምንት ሰዎችን መያዙ የተረጋገጠውን የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመቀነስ ሲባል በሚደረጉ ጥንቃቄዎች ምክንያት ገበያዎች መቀዝቀዛቸውን ነጋዴው ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ቀደም ብሎ በከተማዋ ውስጥ እንቅስቃሴ ይከለከላል በሚል ስጋት አብዛኛው ሰው በተለይም የምግብ ፍጆታዎችን ገዝቶ በማስቀመጡ ምክንያት አሁን የተወሰኑ ቶሎ የሚበላሹ ነገሮችን ለመግዛት ነው ወደ ገበያ እየወጣ ያለው›› ይላሉ፡፡ ‹‹ነገር ግን አሁንም ቢሆን ከአንድ ሳምንት በፊት ከነበረው ሰው በዛ ያለ ሰው ይገበያያል›› ሲሉ የዛሬውን የገበያ ውሎ ከቀናት በፊት ከነበረው ጋር ያነጻጽራሉ፡፡

ድሬዳዋን በታማሚ ብዛት ከአዲስ አበባ ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ያስቀመጣት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፤ በከተማይቱ የግብይት እንቅስቃሴ ላይ ተጽእኖ አሳድሯል፡፡ የታይዋን የገበያ አዳራሽ በኮሮና ቫይረስ ስርጭት ስጋት ለ15 ቀናት ተዘግቶ ቆይቷል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ የገበያ አዳራሹ ከሚያዝያ ሰባት ጀምሮ እንዲከፈት ሲወስን የነጋዴውን የኢኮኖሚ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት እንድሆነ አስታውቋል፡፡

አስተዳደሩ በገበያ አዳራሹ መግቢያ ላይ የለጠፈው ማስታወቂያ በየሱቆቹ ውስጥ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ማድረግ እንደሚገባ ያሳስባል፡፡ ግብይቶች ርቀት ጠብቀው እንዲከናወኑ፣ እጅ መታጠቢያዎችን በማዘጋጀት፣ የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችን (ማስኮችን) እና የእጅ ጓንቶችን እንዲያደርጉም ያዝዛል፡፡ 

በታይዋን የገበያ አዳራሽ የሚታዩ አብዛኞቹ ነጋዴዎች የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችን ባያደርጉም በዚያው የሚገኙ ልብስ ሰፊዎች ግን ለገዢዎች የሚሆኑ ማስኮችን በየዓይነቱ በማዘጋጀት ስራ ተጠምደው ተስተውለዋል፡፡ ልብስ ሰፊዎቹ አንድን የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ በ25 ብር ይሸጣሉ፡፡ በአብዛኛው ባንኮች መሸፈኛዎችን እንደሚያዝዙ የገለፁት አንድ የልብስ ሰፊ፤ መንገድ ላይ ለሚያዞሩ ቸርቻሪ ነጋዴዎችም ማስኮቹን እንደሚያስረክቡ ይናገራሉ፡፡

በገበያ አዳራሹ ውስጥ የሚታየው አነስ ያለ የሸማቾች ቁጥር በጎኑ በተቀለሱ መደብሮች ከሚስተዋለው ግርግር ጋር ይቃረናል፡፡ የገበያ ቦታዎቹን ተዘዋውረው የተመለከቱት የኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘጋቢዎች የተጨናነቁ የእግረኛ መንገዶችን፤ ሰዎች ተጠጋግተው አንዳንዴም በግፊያ የሚሸምቱባቸውን መደብሮችን ተመልክተዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩም በተሽከርካሪዎች ትልልቅ የድምጽ ማጉያዎችን በመጫን በገበያ መካከል አካላዊ ርቀት እንዲጠበቅ ትምህርት ሲሰጥ ታዝበዋል፡፡ 

በጫት መሸጫ ቦታዎች ቁጥሩ ቀላል የማይባል ሸማች የሚገበያይ ሲሆን ምሽት ድረስ የሚዘልቅ ግብይት ይካሄዳል፡፡ ባለ ሶስት እግር ተሸከርካሪዎች አንድ ሰው ብቻ ሲጭኑ በተለምዶ ፎርስ ተብሎ የሚታወቀው ባለ ሶስት እግር ተሸከርካሪ ሁለት ሰው ብቻ ያሳፍራሉ፡፡ ከዚያ ውጪ ያሉ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ከመጫን አቅማቸው ሃምሳ በመቶ ብቻ በመያዝ ሰራቸውን ያከናውናሉ፡፡ 

የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ያጠለቁ ነዋሪዎች እንዲሁም በሻርፓቸው ፊታቸውን በግማሽ የሸፈኑ እናቶች አልፎ አልፎም ቢሆን ይታያሉ፡፡ የካፍቴሪያዎች እና ሆቴሎች ሰራተኞች ደንበኞቻቸው እንዳይጠጋጉ እንዲሁም እጆቻቸውን እንዲታጠቡ ሲያድርጉም ተስተውለዋል፡፡ በመንገድ ላይ ትኩስ ነገሮችን እና ፈጣን ምግቦችን የሚያቀርቡ አገልግሎት ሰጪዎችም ተመሳሳዩን አካሄድ ተግባሪ ሆነዋል፡፡

በድሬዳዋ ለረመዳን ጾም ዝግጅት የሚያደርጉ ነዋሪዎች በእስልምና ሃይማኖት ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን የረመዳን ወርን ለመቀበል በጉጉት ተሞልተው ሲገበያዩ ተስተውለዋል፡፡ ነዋሪዎቹ በረመዳን ወር ከእስከዛሬው በተለየ ሶላታቸውን በቤታቸው እንደሚያደርጉ ለኢትዮጵያ ኢንሳይደር ተናግረዋል፡፡ በድሬዳዋ ከተማ ታዋቂ ከሆኑት መስጊዶች መካከል የሆነውን መስጊድ ጁምዓን ጨምሮ በሁሉም መስጊዶች አዛን ከሚያደርጉ አባቶች ውጪ መግባት መከልከሉንም ነዋሪዎቹ ጨምረው ገልጸዋል፡፡ 

ከዚህ ቀደም በነበሩ ዓመታት በረመዳን ዋዜማ ተራዊሕ ሶላት በመስጊዶች ይካሄድ ነበር፡፡ ተርሃዊ ቢያንስ ለአንድ ሰዓት የሚቆይ እና ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ የሚደረግ ሶላት ነው፡፡ በዚህ አመት ግን ተርሃዊ እንደማይኖር ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ያነጋገረቻቸው ነዋሪዎች አስረድተዋል፡፡ (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)