ምስራቅ ኢትዮጵያ – ለኮሮና እጅ ያሰጠን ይሆን?

በሐይማኖት አሸናፊ እና ተስፋለም ወልደየስ

የኢትዮጵያ የጤና ሚኒስቴር በያዝነው ሳምንት ይፋ ካደረጋቸው የተረጋገጡ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች መካከል አራቱ ከፑንትላንድ የመጡ ግለሰቦች መሆናቸውን አስታውቋል። ግለሰቦቹ በጅግጅጋ አስገዳጅ የለይቶ ማቆያ ውስጥ ያሉ እንደሆነም ተገልጿል። ምንም አይነት የጉዞ ታሪክ የሌለው እና በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ጉባ ኮሪቻ ወረዳ የሚኖር የ23 ዓመት ወጣትም እንዲሁ በኮሮና ቫይረስ መያዙ በምርመራ ተረጋግጧል። ወጣቱ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት ይኖረው እንደው “እየተጣራ” መሆኑም ተነግሯል።

የጤና ሚኒስቴር ባለፉት ሳምንታት ባወጣቸው መረጃዎች በድሬዳዋ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ስምንት መድረሱንም አስታውቆ ነበር። በምስራቅ ኢትዮጵያ ቁጥራቸው እየጨመሩ የመጡትን በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች የታዘቡት የ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢዎች አካባቢው “ለኮሮና እጅ ያሰጠን ይሆን?” የሚል ጥያቄን አንስተው ከአዲስ አበባ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው መልሱን አፈላልገዋል። ከደወሌ እስከ ቶጎ ውጫሌ፤ ከድሬዳዋ እስከ ጅግጅጋ ተጉዘው የስደት ተመላሾቹን ሁኔታ፣ የጤና መሰረተ ልማቱን ዝግጁነት፣ የሰብአዊ እና ማህበራዊ ዕውነታዎችን ፈትሽዋል። 

ኢትዮጵያን በደወሌ በኩል ከጅቡቲ ጋር በሚያዋስናት የድንበር ኬላ ላይ ካሉ ነገሮች ቀድሞ አይን የሚገባው መንገድ ዳር የተደኮነ ድንኳን ነው። ከኢትዮጵያ የሚወጡ እና የሚገቡ ተሽከርካሪዎችን ለማቆም የተዘረጋ ገመድን ተሻግሮ የተተከለው ድንኳን በውስጡ የህክምና ባለሙያዎችን ይዟል። የህክምና ባለሙያዎቹ የሂያጅ እና መጪውን ሙቀት የመለካት ስራ ያከናውናሉ። 

ከድሬዳዋ ደወሌ በተዘረጋው የአስፋልት መንገድ  በየቀኑ የሚመላለሱ የከባድ መኪና እና ነዳጅ ጫኝ ቦቴ አሽከርካሪዎች በእነዚህ ባለሙያዎች ሳይታዩ አያልፉም።  ከጀቡቲ በየዕለቱ እየተመለሱ ያሉ ስደተኞችም የባለሙያዎቹን የሙቀት መጠን ፍተሻ ማለፍ ግድ ይላቸዋል። ፍተሻው በጅቡቲ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ የመጣው የኮሮና ቫይረስ ይኖርባቸው እንደው ለመለየት በመጀመሪያ ደረጃ ማጣሪያነት ያገልግላል። 

ከፍተኛ የወጪ እና የገቢ ንግድ መተላለፊያ የሆነው እና በሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን አይሻ ደወሌ ወረዳ በሚገኘው በዚህ ድንበር በኩል፤ ባለፈው አንድ ወር በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል። በድንበሩ ዋና መግቢያ እና መውጫ በሮች እንዲሁም ለእንቅስቃሴ ባልተፈቀዱ የድንበሩ ክፍሎች የሚገቡ ስደተኞች በመከላከያ ሰራዊት አባላት ተይዘው ወደ አንድ ቦታ ይሰበሰባሉ፡፡

ከስደት ተመላሽ ኢትዮጵያውያኑ፤ ያለ በቂ ብርድ ልብስ እና ፍራሽ ለቀናት እንዲቆዩ የሚደረግበት ቦታ፤ ጣራ እና ወለል እንጂ በርም ሆነ ግድግዳ የሌለው መጋዘን ነው። ዙሪያውን ክፍት የሆነው መጋዘን ሲገነባ ከኢትዮጵያ ወደ ጅቡቲ እንዲሁም በጅቡቲ አድርገው ወደ ሌሎች የአለማችን ክፍሎች የሚላኩ ምርቶች እንዲቆዩበት ታስቦ ነበር፡፡ አሁን ከጅቡቲ የተመለሱ ከ200 በላይ ስደተኞችን የሚያስተናግድ ለይቶ ማቆያ ሆኗል።

ታዳጊዎቹ ስደተኞች

ከስደት ተመላሾቹ ውስጥ አብዛኞቹ በወጣትነት ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ከእነርሱ መካከል ቁጥራቸው የማይናቅ ታዳጊዎች እንዳሉበት በስፍራው የተገኙት የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢዎች ተመልክተዋል። ከሁለት ወር ከ15 ቀን በፊት ከቤተሰቦቿ ጠፍታ ወደ ጂቡቲ የሄደችው የ13 ዓመቷ አንዳርቱ አብደላ ከታዳጊዎቹ አንዷ ናት። 

አንዳርቱ ገና በለጋ ዕድሜዋ ከስደት የገባቸው ከእድሜ እኩያ ሴት ጓደኞቿ ጋር ወደ ሳውዲ አረቢያ ሄደው የመስራት እቅድ ይዘው ነበር። ጉዞውን ያለ ምንም ክፍያ ብትጀምረውም ሲገባደድ ግን ቤተሰቦቿን በሺህዎች የሚቆጠር ገንዘብ አስወጥታ፤ ያሰበችበት ሳትደርስ ከጅቡቲ ለመመለስ ተገድዳለች። እርሷ እና ጓደኞቿ ከቀያቸው ተነስተው የጂቡቲን መንገድ ከጀመሩ በኋላ ደላሎች ድብደባ እንዳደረሱባቸው የምትናገረው ታዳጊዋ ለቤተሰቦቻቸው ስልክ በማስደወል እስከ 15 ሺህ ብር ማስላካቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድታለች። 

“ቤተሰቦቼ በሬ ሸጠው ገንዘቡን ላኩልኝ። በጅቡቲ በቆየንባቸው ሁለት ወራት ምንም ስራ የለንም። ቤት ውስጥ ነበር ቁጭ ብለን የምንውለው” ስትል የስደት ጊዜዋን አስታውሳለች። ከዚህ የወሰዳቸው ደላላ ገንዘቡን ከተቀበለ በኋላ ባህር ለሚያሻግራቸው ሰው የጀልባ ክፍያ መፈፀሙን ገልፆ እንደጠፋባቸውም ጨምራ ገልጻለች።

እንደ አንዳርቱ ሁሉ “ውጪ አገር” ለመሄድ በማሰብ ከሌሎች ሁለት የሰፈሩ ልጆች ጋር ሆኖ ከቤት ጠፍቶ ወደ ጅቡቲ የተጓዘው የ12 አመቱ ታዳጊ አንዋር የስደት ትርጉሙን እንኳ በቅጡ የሚያውቅ አይመስልም።   

ከትውልድ ስፍራው ሐረርጌ መቻራ ተነስቶ ጅቡቲ እስከሚገኘው ታጁራ የተባለ ቦታ ለመድረስ ሶስት ቀን በእግሩ መጓዙን የሚናገረው አንዋር ወደ ሀገሩ ለመመለስም ተመሳሳይ አካሄድ እንደተጠቀመ ይገልጻል። ከጀቡቲ ተነስቶ ደወሌ የሚገኘው የድንበር ማቆያ የደረሰው ቀን እና ለሊት ሳይል ለሁለት ቀናት በእግሩ ተጉዞ እንደሆነ ያስረዳል። ሲርበው የከባድ መኪና አሽርካሪዎችን እና በመንገድ ላይ ያሉ ቤቶችን በመለመን “ምግብ አገኝ ነበር” ይላል። ለአንድ ሳምንት በቆየበት የደወሌ የለይቶ ማቆያ ሩዝ እየመገቧቸው መሆኑን እና ውሃም እንደሚሰጧቸው ተናግሯል።  

የድንበር ለይቶ ማቆያ

ከስደት ተመላሾቹን ወደ ለይቶ ማቆያ የሚያስገቧቸው፣ የሚበላ እና የሚጠጣ የሚያቀርቡላቸው፣ ማቆያውን ለቅቀው ከህብረተሰቡ ጋር እንዳይቀላቀሉ ጥበቃ የሚያደርጉላቸው የመከላከያ ሰራዊት አባላት ናቸው። የሰራዊቱ አባላት ስደተኞቹ በሰፊው መግባት ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ የራሳቸውን ምግብ እና ውሃ ከማካፈል ውጪ ለተመላሾች የሚሆን የመሰረታዊ ፍጆታ አቅርቦት እንዳልነበራቸው ያስረዳሉ። 

ድንበሩን የሚጠብቀው ጦር የሁለተኛ ሻለቃ ምክትል አዛዥ የሆኑት ሻለቃ ዘሪሁን ተረፈ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት የተወሰነ የምግብ አቅርቦት ለስደተኞቹ የደረሰው ሐሙስ ሚያዚያ 15፤ 2012 ነው። “ሩዝ እና ዘይት የክልሉ መንግስት ልኮልናል። ብርድ ልብስ የተላከልን ቢሆንም ነገር ግን ከ30 በላይ የሚሆኑት አሁንም አልደረሳቸውም” ሲሉ ለስደተኞቹ በቂ አቅርቦት አለመኖሩን ገልጸዋል። 

በምግብ እና ተያያዥ አቅርቦቶች ያሉ እጥረቶች በህክምና አገልግሎት ላይ እንዳለም ሻለቃ ዘሪሁን ይናገራሉ። ከጂቡቲ የሚመጡት ኢትዮጵያዊያን ቁጥር ጋር ሲነፃፀር በወረዳ አስተዳደሩ አቅም የሚቻል ነው ብለው እንደማያምኑ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የመከላከያ ሰራዊት አመራሮች ይናገራሉ፡፡ በተለይም ሻለቃ ዘሪሁን እንደሚሉት ከኮሮና ባልተናነስ በሌሎች ተላላፊ በሽታዎች የሰው ህይወት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ስጋት አላቸው፡፡ 

እስካሁን ድረስ የሰራዊቱ አባላት የተለየ ህመም ያጋጠመው ሰው ሲኖር ለብቻው ለይተው በማስቀመጥ የህክምና ባለሙያዎች ሁኔታውን እንዲከታተል ያደርጋሉ።  ያስረዳሉ። የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢዎች በደወሌ ድንበር በነበራቸው ቆይታ አንድ የወባ ህመም ምልክቶችን የሚያሳይ ስደተኛ በአንድ ክፍል ውስጥ ተለይቶ፣ የህክምና ክትትል እየተደረገለት እንዲቀመጥ መደረጉን ተመልክተዋል። 

ወጣቱ ከዚህ ቀደም የወባ ህመም እንደሚመላለስበት እና አሁንም ምልክቱ ከዛ ጋር በመቀራረቡ የወባ መድሃኒት እንደቀረበለት ሻለቃ ዘሪሁን ተናግረዋል፡፡ ለሶስት ቀን መድሃኒት እየወሰደ ለውጥ ማሳየቱን እና ከኮሮና በሽታ ጋር የሚቀራረቡ ምልክቶች እንዳልተመለከቱም ገልፀዋል፡፡

በደወሌ ድንበር አጠገብ በሚገኘው የለይቶ ማቆያ ውስጥ ከሚገኙ ተመላሾች በተጨማሪ በዚሁ ድንበር ቀደም ብለው የገቡ ከ300 በላይ ስደተኞችም የህክምና ክትትል እና ምግብ ያገኛሉ ተብሏል። ከስደት ተመላሾቹ በደወሌ ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው የኢትዮ-ጂቡቲ የባቡር ጣቢያ ውስጥ በተዘጋጀ የለይቶ ማቆያ ከገቡ ሰንብተዋል። “ወደ ለይቶ ማቆያ ከገቡ ከ15 ቀን በኋላ ለምርመራ ናሙና ተልኳል ቢባልም እስካሁን አልመጣም። አንድ ወር አልፏቸዋል” ሲሉ በአካባቢው ያሉ የመከላከያ ሰራዊት አባል ተናግረዋል። 

ከጅቡቲ የሚመለሱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በየቀኑ እንደሚጨምር የሚናገሩት የሰራዊቱ አባላት መጪው ጊዜ ያሳስባቸዋል። በአንድ ጊዜ በርካታ ስደተኛ ድንበር አቋርጦ የሚመጣ ከሆነ አሁን ባላቸው አቅም እና እያገኙ ባለው አቅርቦት ኢትዮጵያውያኑን በአግባቡ ለማስተናገድ እንደሚቸገሩ ይገልጻሉ።   

ስደተኞች በጅቡቲ  

ጅቡቲ ከመጋቢት 6፤ 2012 ጀምሮ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከጎረቤት አገራት ጋር የሚያዋስኗትን የየብስ፣ የአየር እና የባህር ድንበሮቿን መዝጋቷን ይፋ አድርጋለች፡፡ የድንበር ጠባቂዎቿ ወደ ጅቡቲ የሚደረጉ ጉዞዎችን ይከልክሉ እንጂ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ ሀገራቸው እንደሚመለሱ ከገለጹ እንደሚያሳልፉ ተመላሾች ይናገራሉ። 

ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) በያዝነው የሚያዚያ ወር ውስጥ ብቻ 2,400 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከጅቡቲ “እየተባረሩ” ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን አስታውቋል። ጅቡቲ እርምጃውን የወሰደችው “የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት” በሚል እንደሆነ ተመላሽ ስደተኞች ያስረዳሉ። 

ሀገሪቱ በአፍሪካ ቀንድ ካሉ ሀገራት መካከል አነስተኛ የሆነ የሕዝብ ቁጥር ቢኖራትም በርካታ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎችን በምርመራ በማረጋገጥ ከቀጠናው ሀገራት ከፍተኛውን ደረጃ ይዛለች። እስከ ረቡዕ ሚያዝያ 21፤ 2012 ባለው ጊዜ ብቻ በሀገሪቱ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 1072 ደርሷል። 

በጅቡቲ በየጊዜው እያሻቀበ የመጣው የኮሮና ተጠቂዎች ብዛት “በዚያ የሚገኙም ሆኑ ከስደት እየተመለሱ ያሉ ኢትዮጵያውያን ለቫይረሱ ተጋልጠው ይሆን?” የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም። በጅቡቲ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩ ይገመታል። ላለፉት ሶስት ወራት በጅቡቲ በስደት የቆየው ዘውዱ አማረ በዚያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስለበሽታው በቂ ግንዛቤ እንደሌላቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግሯል። 

ኢትዮጵያውያን ስደተኞች “ገዳይ በሽታ መጣ” ሲባል ይሰማሉ እንጂ ስለ በሽታው እና መተላለፊያዎቹ ከጅቡቲ ወገን መረጃ እንደማያገኙ ይገልጻል። ኮሮናን በሚመለከት የሚተላለፉ መልዕክቶች በአረብኛ ስለሚቀርቡ ኢትዮጵያውያኑ በቋንቋ ችግር የሚባለውን እንደማይከታተሉ ያስረዳል። የኮሮና ቫይረስን መከሰት ተከትሎም ስደተኞቹ “ምንም አይነት የጤና አገልገሎት አያገኙም” ይላል። 

እንደ እርሱ ሁሉ ከጅቡቲ የተመለሱ ኢትዮጵያውያንም የሀገራቸው ልጆች በብዛት በሚኖሩበት መንደር ውስጥ መሰረታዊ አገልግሎቶች ማግኘት ጭምር አስቸጋሪ እየሆነ እንደመጣ ይናገራሉ። በጂቡቲ ዋና ከተማ ጂቡቲ ውስጥ ኢትዮጵያዊያን ከሚኖሩባት ሀሪባ ከምትሰኘው መንደር ወደ ሌላ የከተማይቱ ክፍል ለመሄድ የሚሞክር ሰው በፖሊስ እየተደበደበ እንደሚመለስ ይገልጻሉ። ይህም ስደተኞች በቂ ምግብ እና ውሃ ሳያገኙ ተዘግተው እንዲቀመጡ እንዳደረጋቸው ተመላሾቹ ያስረዳሉ። 

ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በአብዛኛው “በጠባብ ቤቶች ተጨናንቀው የሚኖሩ ናቸው” የሚሉት ተመላሾቹ ይህንንም የሚያደርጉት የቤት ኪራይ ወጪን ለመቀነስ ሲባል እንደሆነ ይጠቁማሉ። በአንድ ቤት ውስጥ በአማካይ ከ10 እስከ 20 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በጋራ እንደሚኖሩ ዘውዱም ቢሆን ያረጋግጣል። አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ወንድ ስደተኞች በጀቡቲ በግንባታ ስራ የተሰማሩ ሲሆን ሴቶች ደግሞ በቤት ውስጥ ስራ እንደሚተዳደሩ ከተመላሽ ስደተኞች የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 

“የኮሮና በሽታ መጣ ሲባል ፓትሮሎቹ ወንዶቹን ከቀን ስራ፤ ሴቶቹን ከሰው ቤት ማስወጣት ጀመሩ። አሁን መንግስት ስለማይረዳቸው ስደተኞቹ እርስ በእርስ እየተረዳዱ ይገኛሉ። መንገድ በሙሉ ተዘግቷል። ቤትም አንዲሁ፣ እዛ የቀሩት ስደተኞች በረሃብ ላይ ነው የሚገኙት” ሲል ተመላሽ ስደተኛው ዘውዱ ያስረዳል። “እኛ ህግ ላይ ነው ያለነው። እነሱ ግን እየራባቸው እየተጠሙ ቁጭ ብለዋል። ውሃም ይሁን ምግብ አይሰጣቸውም” ሲል በጅቡቲ የቀሩ ኢትዮጵያውያንን አሳሳቢ ሁኔታ አጽንኦት ይሰጣል።

በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ የጅቡቲ መንግስት ዋና ዋን እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ በማድረጉ የኢትዮጵያ ስደተኞች ከእጅ ወደ አፍ የሆነው የገቢ ምንጫቸው ሙሉ በሙሉ ደርቋል። ህይወታቸውን ለማዳንም ወደ አገራቸው በእግራቸው ለመመለስ አደገኛውን ጉዞ መርጠዋል። 

የድብብቆሽ ጉዞ

ሲመች ዋናውን አውራ ጎዳና እየተከተሉ አሊያ ደግሞ ውስጥ ለውስጥ እያቆራረጡ ወደ ሀገራቸው ከገቡት ስደተኞች መካከል የተወሰኑቱ እስከ ድንበር ድረስ የተጓዙት በጭነት መኪናዎች ነው። በተለምዶ ኤፍ. ኤስ. አር ተብለው በሚታወቁ የጭነት መኪኖች ስደተኞችን ድንበር ድረስ ሲያጓጓዙ የነበሩት “ጀንደር መሪ” በመባል የሚታወቁት የጅቡቲ ፖሊሶች እንደሆኑ ወደ ጅቡቲ የሚመላለሱ ኢትዮጵያውያን ሹፌሮች ይገልጻሉ። በአምስት የጅቡቲ ፖሊስ የጭነት መኪኖች የተጫኑ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከሁለት ሳምንት በፊት ድንበር ላይ ሲራገፉ መመልከታቸውን ሹፌሮቹ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

“ፖሊሶቹ ይህንን ድሮም ያደርጉ ነበር። ድንገት ይመጡ እና [ህጋዊ] ወረቀት የሌላቸውን መታወቂያ ይጠይቃሉ። ከሌለህ እያፈሱ ይወስዱህና ይመልሱ ነበር። አሁን ግን በበሽታው ምክንያት ነው” ይላል ወደ ጅቡቲ በመላለስ ላለፉት 10 ዓመታት የሰራው ጎልማሳ ሹፌር። ይሄው ሹፌር ተመላሽ ስደተኞች ወደ በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ሳይገቡ በጋላፊ አቅጣጫ በእግር ሲገቡ መመልከቱን ይናገራል። 

ስደተኞቹ በዋናው መንገድ ሲሄዱ ቢታዩ እንደሚያዙ ስለሚያውቁ በእግር መንገድ እያሳበሩ እንደሚጓዙ የጀቡቲ ተመላላሽ ሹፌሮች ያስረዳሉ። “በእግር ሲጓዙ የምታያቸው ጠፍተው ነው” ይላል ጎልማሳው ሹፌር። ከእርሱ ጋር የተጓዘ ሌላ ሹፌር በበኩሉ “እስከ ዛሬ የሚያልፉት በኬላ ነበር። አሁን ግን በኬላ ጀርባ ነው” ሲል የጓደኛውን አስተያየት ያጠናክራል። 

ከሳምንት በፊት ወደ ጅቡቲ ተጉዞ የነበረ አሽከርካሪም ከሁለቱ ሹፌሮች ጋር የሚመሳሰል አስተያየት አለው። የከባድ መኪና አሽከርካሪው ከአምስት እስከ ሰባት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በቡድን እየሆኑ በእግር ጀቡቲን ለቅቀው ሲወጡ መመልከቱን ይናገራል። ስደተኞቹን በአይሱዙ የጭነት መኪና እና ሚኒባስ ከድንበር ወደ ሀገር ውስጥ የሚያጓጓዙ እንዳሉም ይናገራል። 

በድሬዳዋ ያለ አንድ አሽከርካሪ ስደተኞቹን በድብቅ የማጓጓዙን ስራ የሚሰሩት በጫት ማመላለስ ላይ የተሰማሩ የጭነት መኪኖች እንደሆኑ ከራሳቸው ከሹፌሮች አንደበት መስማቱን ገልጿል። የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢዎች በሳምንቱ መጨረሻ ወደ ጅግጅጋ ከተማ በተጓዙበት ወቅት ከዚሁ ጋር የሚመሳሰል ክስተት ታዝበዋል። 

በጅግጅጋ መግቢያ ላይ በሚገኛው እና በተለምዶ ካራማራ ተብሎ በሚታወቀው የፍተሻ እና የጉምሩክ ጣቢያ ላይ ቆሞ በነበረ መካከለኛ የጭነት መኪና አንድ ታዳጊ በጫት መካከል ተሸሽጎ ተመልክተዋል። በጭነት መኪናው ላይ፣ በነጭ ላስቲክ ከተጫኑት የጫት ምርቶች መካከል ተጠቅልሎ የተኛው ታዳጊ፣ መኪናው ሲንቀሳቀስ የፊቱን ሽፍን በመግለጥ ሁኔታውን ለማስተዋል ሲሞክር ታይቷል።

የጫቱ ጭነት ታይቶ እና ቀረጥ ተከፍሎ ወደ ጅግጅጋ እስኪገባ ያለውን ሂደት ዘጋቢዎቹ እስከ መጨረሻው መከታተል አልቻሉም። ጉዳዩ ከተመላሽ ስደተኞች አሊያም ከህገወጥ ስደተኞች ዝውውር ጋር የተያያዘ መሆኑን የሚያረጋግጥ አካልም በስፍራው አልነበረም።  

በጫት ማጓጓዣ መኪናዎች ስደተኞችን በድብቅ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የሚደረግ ሙከራዎች እንዳሉ በደወሌ ድንበር ያሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። የደወሌ ድንበር ለመጠበቅ የተሰማራውን ሰራዊት በምክትል አዛዥነት የሚመሩት ሻለቃ ዘሪሁን ከዋናው መስመር ውጭ በዚህ አይነት ሁኔታ የሚገቡ ስደተኞችን ሰራዊታቸው በየጊዜው በቁጥጥር ስር እንደሚያውል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

 “በሩቅ ርቀት ሁለትም፣ ሶስትም ሆነው አልፈው ሄደው፣ ሩቅ መንደር ላይ ወደ ዋናው አስፋልት መጥተው መኪና ‘ሊፍት” ይጠይቃሉ። መኪናውም ያው ገንዘብ ስለሚከፈለው እየሰበሰበ ሲሄድ እንዲህ በወታደር እያስቆምን ወደዚህ የሚመለስበት ሁኔታ አለ። በዚህ አይነት ሂደት ውስጥ ሶስት፣ አራት ጊዜ ጭኖ ሄዶ፣ ከእነ መኪናው እንዲመለስ አድርገን እዚህ አስገብተን መኪናውን ፖሊስ ጣቢያ እንዲታሰር ያደርግነው አለ” ሲሉ የህግ ማስከበር ሂደቱን አብራርተዋል። 

“ትኩረት ያልተሰጣት” ቶጎ ውጫሌ 

ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድን የምታዋስነው ቶጎ ውጫሌ ሌላው ብዙ ቁጥር ያላቸው ዜጎች የሚገቡባት የድንበር ከተማ ናት። በቀጭን ገመድ የተለየውን ድንበር እያቋረጡ በቀን በአማካኝ እስከ 50 ሰዎች ያህል ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ። ቁጥሩ አንዳንዴ እስከ 90 ሊደርስ እንደሚችል የከተማይቱ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ባለፈው ቅዳሜ ሚያዝያ 17 በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ላቦራቶሪ በተደረገው ምርመራ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው የታወቀው ግለሰብ ወደ ኢትዮጵያ የገቡት በዚህ ድንበር በኩል ነበር። በሶማሌ ክልል የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ የተረጋገጠ ተጠቂ የሆኑት እኚህ ግለሰብ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ ምንም አይነት ምልክት እንዳልነበራቸው በቶጎ ውጫሌ ከተማ የጤና ባለሙያ የሆኑት አብዱራህማን ኑርኑር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልፀዋል። ግለሰቡ በጅግጅጋ ከተማ ባለው ለይቶ ማቆያ ውስጥ በነበሩ ጊዜ በተደረገላቸው ምርመራ የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸውም አስረድተዋል።  

ድንበር አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ ከሚገቡት ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ አሽከርካሪዎች መሆናቸውን የጤና ባለሙያው ይናገራሉ። ድንበሩን የሚያቋርጥ ማንኛውም ሰው ስሙ፣ የሙቀት መጠኑ፣ አድራሻው እንዲሁም ሌሎች ለየዕለት የቫይረሱ ስርጭት ክትትል የሚረዱ መረጃዎች ይሰበሰባሉ። ለተፈቀደ ስራ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች የሙቀት ልኬት ተደርጎላቸው ሙቀታቸው መደበኛ ከሆነ ለይቶ ማቆያ መግባት አይጠበቅባቸውም።

የቶጎ ውጫሌ ድንበር ፑንትላንድን ጨምሮ ከተለያዩ የጎረቤት አገራት በቋሚነት የሚመለሱ ሰዎችን የማስተናገዱን ያህል የየዕለት የንግድ እንቅስቃሴውም ቀላል የሚባል አይደለም። የኢትዮጵያ የገቢና እና የወጪ ንግድ ከሚስተናገድባቸው የጎረቤት አገር ወደቦች መካከል አንዱ በሆነው የበርበራ ወደብ የሚገቡ እና የሚወጡ እቃዎችም መግቢያቸው የቶጎ ውጫሌ በር ነው። አካባቢው ከህጋዊ ንግዱ ባሻገር ከፍተኛ የሆነ የኮንትሮባንድ ንግድ የሚንቀሳቀስበት እንደሆነ የፌደራሉ የጉምሩክ ኮሚሽን በተለያየ ጊዜም ማስታወቁ ይታወሳል።

የተለያዩ ሸቀጦችን በመሸጥ እና በመግዛት እንደ አንድ ከተማ ሆነው የሚኖሩት የኢትዮጵያ እና የሶማሊላንድ ቶጎ ውጫሌ ከተሞች ነዋሪዎች ድንበሩን በዘፈቀደ ለማቋረጥ ሲሞክሩ ይታያሉ። የኢትዮጵያው ቶጎ ውጫሌ ድንበር ላይ የከተማው ሚሊሺያ፣ የመከላከያ ሰራዊት እና የፌደራል ፖሊስ አባላት በዱላ ሰው ሲመልሱ የሚውሉ ቢሆንም በሶማሊላንድ በኩል ግን ያን ያህል የጠነከረ ክልከላ አይስተዋልም።

የቶጎ ውጫሌ ከተማ ከንቲባ ሙክታር ሃቢብ “ዝውውሩን ለማስቆም በጣም ተቸግረናል። ባሳለፍነው ሳምንት ጥይት ተተኩሶ ሁለት ሰው ከቆሰለ በኋላ እንቅስቃሴው የተወሰነ ቀንሷል። ይህም ቢሆን ግን ፍሰቱን ለማስቆም በጣም አስቸጋሪ ሆኗል” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ከንቲባው ይህ ድንበር ከተለያዩ የምስራቅ አፍሪካ አገራት የሚመጡ ሰዎች የሚገቡበት የመሆኑን ያህል የሶማሌ ክልልም ሆነ የፌደራል መንግስት ትኩረት አልሰጡትም ብለው ያምናሉ።

ላለፉት ሁለት ቀናት የሶማሌ ክልል “የመቀበል አቅሜ ሞልቷል” በማለቱ ምክንያት 30 ሰዎችን በከተማቸው ይዘው እንደሚገኙ የሚገልጹት ከንቲባው በጅግጅጋ ከተማ ወደሚገኘው ለይቶ ማቆያ አዲስ ሰው እንዳይልኩ እንደተነገራቸው አስረድተዋል። እስካሁንም ከ1000 በላይ ሰዎች በዚህ ድንበር ገብተው ወደ ጅግጅጋ ከተማ መላካቸውን ገልፀዋል። 

“እኛ እዚህ ይዘን ለማቆየት ደግሞ በጀትም፤ አቅምም የለንም። ስለዚህ ከድንበር እየሰበሰብን ከከተማው ጥግ በሚገኝ ቦታ ለጊዜው እያስቀመጥን ነው። ‘ይህ አካባቢ ትኩረት ይፈልጋል’ ብለን ሪፖርት አድርገናል። አፋጣኝ መፍትሄ ካልተሰጠ ግን ሰዎች በሌላ በኩልም ቢሆን መግባታቸው የማይቀር ነው” ሲሉ አክለዋል።

የሶማሌ ክልል የጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዩሱፍ መሃመድ በበኩላቸው በጅግጅጋ ከተማ በሚገኘው ለይቶ ማቆያ አዲስ ሰው ማስተናገድ ያልተቻለው የተዘጋጀው ቦታ በመሙላቱ ሳቢያ እንደሆነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በዚህም ምክንያት ለጊዜው አገልግሎቱ መቆሙን ጠቁመው በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህንን ለመፍታት ከፌደራል መንግስት ጋር ንግግር መጀመራቸውን አስረድተዋል። 

በድንበር ከተማይቱ ቶጎ ውጫሌ ከተማ የኳስ ጨዋታን ጨምሮ በጋራ የሚደረጉ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ዛሬም ቀጥለዋል። በከተማዋ ባሉ የገበያ ቦታዎች የሚታየው እንቅስቃሴ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ በጥንቃቄ ሲካሄድም አይታይም። በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ድንበሩ ለሰዎች እንቅስቃሴ መከልከሉ ግን ከተማዋን ከዚህ ቀደም ከነበረችበት አቀዝቅዟታል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የቶጎ ውጫሌ ከተማ ከንቲባ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን ከመስጠት ባሻገር ወደ ሕግ ማስከበር እንዳልተገባ አምነዋል። በቀጣይ ግን “ይህንን ለመፈፀም እንሰራለን” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)