በሐይማኖት አሸናፊ
ኢትዮጵያ የታላቁ የህዳሴ ግድብን የውሃ ሙሌት በመጪው ሰኔ 2012 ለመጀመር በመወሰኗ “ለቀጠናው ሰላም እና መረጋጋት አደጋ ደቅናለች” ስትል ግብጽ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አቤቱታ አስገባች። የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሽኩሪ አርብ ሚያዚያ 23፤ 2012 ለምክር ቤቱ በላኩት አቤቱታ የዓለማቀፉ ማህበረሰብ “ኢትዮጵያን ይምከርልን” ሲሉም ጠይቀዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፊርማ ያረፈበትን እና 15 አባሪ ገጾች ያሉትን አቤቱታ ለጸጥታው ምክር ቤቱ ያስገቡት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የግብጽ አምባሳደር በሆኑት መሃመድ እንድሪስ ናቸው። በአባሪው ግብጽ ከዚህ ቀደም ያካሄደቻቸውን ድርድሮች እንዲሁም “አቤቱታዬን ያስረዱልኛል” ያለቻቸውን ዝርዝሮች አካታበታለች።
“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ይህ የግብጽ የአቤቱታ ሰነድ የግብጽ አቤቱታ የአለማቀፉ ማህበረሰብ የድርጊቱን አሳሳቢነት ለኢትዮጵያ እንዲያስረዳ እና ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድቡ ላይ ለብቻዋ ምንም አይነት ውሳኔ እንዳትወስን ይጠይቃል። ሰነዱ በህዳሴው ግድብ ላይ የሚከናወን የውሃ ሙሌት የታችኛው ተፋሰስ አገራት ሳይመክሩበት በኢትዮጵያ በኩል እንዳይጀመርም ያሳስባል።
ግድቡ ሲገነባ ጀምሮ ኢትዮጵያ “የታችኛውን ተፋሰስ አገራት ሳታማክር ወደ ስራ መግባቷ የዓለማቀፍ ሕግን የጣሰ ድርጊት ነበር” ስትል ግብጽ በአቤቱታ ደብዳቤዋ ወንጅላለች። ሆኖም ተጣሰ ያለችውን የዓለማቀፍ የሕግ ማዕቀፍ በደብዳቤዋ ሳትጠቅስ ቀርታለች።
ግብጽ የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ በኋላ በቀና ልቦና ከኢትዮጵያ ጋር ግድቡን የተመለከቱ ድርድሮችን ማድረጓን ገልጻለች። በእነዚህ ድርድሮች ላይ ግብጽ “ያለግትርነት፣ በገደብ የለሽ መልካም ፈቃድ እና በእውነተኛ የፖለቲካ ቆራጥነት፤ ፍትሃዊ እና ሚዛናዊ ስምምነት ላይ እንዲደረስ ስትሞክር ቆይታለች” ስትልም ለፀጥታው ምክር ቤት አስረድታለች። ነገር ግን እነዚህ ድርድሮች ሳይሳኩ በመቅረታቸው አሜሪካ እና የአለም ባንክን በድርድሩ ላይ እንዲሳተፉ መጋበዟን አስታውሳለች።
የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታ አልሲሲ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለውን አለመግባባት ለመፍታት አሜሪካ በሽምግልና እንድትሳተፍ የሀገሪቱን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን በይፋ የጠየቁት ባለፈው መስከረም ወር ነበር። በተከታዩ ወር የአሜሪካው የገንዘብ ሚኒስትር ስቲቭን ሙንቺን ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን በዋሽንግተን ዲሲ ተገናኝተው እንዲነጋገሩ ባቀረቡት ግብዣ መሰረት ሶስቱ ሀገራት የመጀመሪያ ድርድራቸውን በጥቅምት 2012 አካሂደዋል።
በዋሽንግተን ዲሲ ለአራት ጊዜያት ያህል በተካሄዱት ተከታታይ ድርድሮች “አሜሪካ እና የዓለም ባንክ በታዛቢነት ብቻ” እንደሚሳተፉ ቢነገርም በስተኋላ ላይ የአሜሪካ ሚና “ከአሸማጋይነትም ተሻግሯል” የሚል ቅሬታ ሲሰማ ቆይቷል። አሜሪካ በህዳሴው ግድብ ውሃ አሞላል ላይ አወዛጋቢ አንቀጾችን እንደያዘ የተነገረለት ስምምነት እንዲፈረም ግፊት ማድረጓም በኢትዮጵያ በኩል አልተወደደም። በድርድሩ ላይ ሲሳተፉ የቆዩ ከፍተኛ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት አሜሪካ ስምምነቱን በተመለከተ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ማድረጓን በይፋ ተናግረዋል።
ግብጽ በአቤቱታ ሰነዷ ላይ ይህን የኢትዮጵያን አቋም ተችታለች። “የአሜሪካ አጋሮቻችን ከአለም ባንክ ባገኙት የቴክኒክ ግብዓት ላይ ተመስርተው ያዘጋጁትን ቀመር ኢትዮጵያ ሳትቀበል ቀርታለች” ስትል ግብጽ ነቅፋለች። ኢትዮጵያ የካቲት 19 እና 20 በዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደው የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ሳትገኝ መቅረቷንም አንስታለች።
ግብጽ ለጸጥታው ምክር ቤት ባቀረበችው አባሪ ሰነድ አራተኛ ገጽ ላይ “ይህ ስምምነት ሁሉንም አካላት ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ ተመጣጣኝ ቀመር የያዘ እና የሶስቱንም ሀገራት ጥቅም እኩል የሚያስጠብቅ ነው” በማለት ተሟግታለች። የስምምነቱ መፈረም “በናይል ተፋሰስ ታሪክ ወሳኝ ነጥብ ነው” ስትልም በተመሳሳይ ገጽ ላይ አጽንኦት ሰጥታለች። በሰነዱ የመጨረሻ ክፍልም ኢትዮጵያ ስምምነቱን እንድትፈርም ጠይቃለች።
ጉዳዩን በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ስለሺ በቀለ “ይህ ጉዳይ የተያዘው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በፀጥታው ምክር ቤት ስለሆነ ምንም አይነት አስተያየት መስጠት አልችልም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተጠባባቂ ቃል አቃባይ አምሳሉ ትዕዛዙ “ይህ መሰረተ ቢስ ክስ ነው” ሲሉ የግብጽን አቤቱታ አጣጥለዋል።
አቶ አምሳሉ “አቤቱታው መቅረቡን እናውቃለን። የግብጽ አካሄድ ይጠቅማል ብለን አናስብም። ኢትዮጵያም አስፈላጊውን ምላሽ ለተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት የምታስገባ ይሆናል” ሲሉ ለ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የህዳሴው ግድብ “የኢትዮጵያ ህዝብ ፕሮጀክት ነው” ያሉት ቃል አቀባዩ የግብጽ አቤቱታ “የውሃ ሙሌቱን የሚያዘገይ አይደለም” ብለዋል። “የህዳሴ ግድቡ ጉዳይ የሶስቱ አገራት ጉዳይ እንደመሆኑ መፈታት የሚገባውም በሶስቱ አገራት መካከል ነው” ሲሉም አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)