ኢትዮጵያ በሶማሊያ የተከሰከሰው አውሮፕላን አደጋ እንዲመረመር ተስማማች

በሶማሊያ ከትናንት በስቲያ የተከሰከሰው እና ስድስት ሰዎች የሞቱበትን የአውሮፕላን አደጋ ለመመርመር ኢትዮጵያ፤ ከሶማሊያ እና ኬንያ ጋር መስማማቷን በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ (አሚሶም) አስታወቀ። አሚሶም ይህን ያስታወቀው ትላንት ማምሻውን ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። 

ስድስት ሰዎችን ጭኖ ከሶማሊያ ባይዶዋ የተነሳው አውሮፕላን ከሞቃዲሾ በስተደቡብ 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው ባርዳሌ የተባለች ከተማ ለማረፍ ሲቃረብ የተከሰከሰው ሰኞ ሚያዝያ 26፤ 2012 ነው። ኢምብራር በተባለ የብራዚል ኩባንያ የተመረተው አነስተኛ አውሮፕላን በደረሰበት አደጋ ሁለት ፓይለቶች፣ አንድ የበረራ መኃንዲስ እና ሌሎች ሶስት ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

የአውሮፕላኑን መከስከስ በተመለከተ የኬንያ የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን እንዳለው የሕክምና ቁሳቁስ ጭኖ ከሞቃዲሾ የተነሳው ባለ ሁለት ሞተር አነስተኛ አውሮፕላን በኬንያ የተመዘገበ ሲሆን አፍሪካን ኤክስፕረስ የተባለ ኩባንያ ንብረት ነው። አውሮፕላኑ ከባይዶዋ ከተነሳ ከ20 ደቂቃዎች በኋላ ከበረራ ተቆጣጣሪዎች ጋር የነበረው ግንኙነት መቋረጡን የገለጸው ባለሥልጣኑ “ባላረጋገጥንው ምክንያት ተከስክሷል” ብሏል።

የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ሞሐመድ እና የኬንያው አቻቸው ኡሁሩ ኬንያታ የየሀገራቸው የሲቪል አቪዬሽን ተቋማት አደጋውን እንዲመረምሩ ትናንት ተስማምተዋል። የሶማሊያ ጋዜጠኞች እና የፖለቲካ ተንታኞች ግን ኢትዮጵያን ለአውሮፕላኑ መከስከስ ተጠያቂ አድርገዋል። ጋዜጠኞቹ እና ተንታኞቹ አውሮፕላኑ “በአካባቢው ወታደራዊ ልምምድ በማድረግ ላይ በነበረ የኢትዮጵያ ጦር ሳይመታ አልቀረም” ሲሉ ወንጅለዋል። 

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ስለ አደጋው እስካሁን በጉዳዩ ላይ በይፋ የሰጡት ማብራሪያ የለም። በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ (አሚሶም) በኩል ትላንት ማምሻውን የወጣው መግለጫ ግን ኢትዮጵያ የአውሮፕላን አደጋውን እንዲመረመር ከሶማሊያ እና ኬንያ ጋር መስማማቷን ይፋ አድርጓል። ኬንያ እና ኢትዮጵያ ለሰላም ማስከበር ተልዕኮው ወታደር ያዋጡ አገሮች ናቸው።

የአሚሶም ተልዕኮ ኃላፊ አምባሳደር ፍራንቺስኮ ማዴራ “ለሶማሊያ፣ ኬንያ እና ለኢትዮጵያ መንግሥታት አጋርነታችንን እንደምንቀጥል ማረጋገጥ እና የአደጋውን አኳዃን ለማጥራት የሚደረገውን ምርመራ ለመደገፍ እና ለማመቻቸት ቃል መግባት እንፈልጋለን” ብለዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ጉዳዩን እንደሚከታተለው በሶማሊያ ልዩ መልዕክተኛው በኩል አስታውቋል።  

አደጋው እጅግ እንዳሳዘናቸው የገለጹት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ልዩ ልዑክ እና የሶማሊያ የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ አዳም አብደልሙላ “እንደ የተባበሩት መንግሥታት ቤተሰብነታችን የፌደራል መንግሥቱ እና የደቡብ ምዕራብ ግዛት የአደጋውን መነሾ እንዲረዱ የቻልነውን ሁሉ እናደርጋለን” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)