ኢዜማ ምርጫውን ለማራዘም ህገ መንግስቱ እንዲሻሻል ጠየቀ

ተቃዋሚው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ በተያዘለት እቅድ መሰረት ሊካሄድ ባለመቻሉ ምርጫውን ለማራዘም ይቻል ዘንድ ህገ መንግስቱ እንዲሻሻል ጠየቀ። የህገ መንግስት ማሻሻያው የፌደሬሽን ምክር ቤትን እና የክልል ምክር ቤቶችን የስራ ዘመን ማራዘምን የሚሸፍን መሆን አለበት ብሏል። 

ኢዜማ ዛሬ ረቡዕ ሚያዚያ 28፤ 2012 ዓ.ም ባወጣው የአቋም መግለጫ የፌደራል እና የክልል ምክር ቤቶች የስራ ዘመን፤ መጪው ምርጫ ከመካሄዱ ቀድሞ ሲጠናቀቅ፤ “አገርን ማን ያስተዳድራል?” ለሚለው ጥያቄ መፍትሄ ይሆናል ያለውን ሀሳብ አቅርቧል። ለምርጫ መራዘም “የምናቀርበው ህጋዊ እና ፖለቲካዊ አማራጭ ሀገረ-መንግስቱን የሚያስቀጥልና ወደተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የምናደርገውን ሽግግር የሚያግዝ ሊሆን ይገባል” ሲል ፓርቲው በመግለጫው አሳስቧል። 

የህገ መንግስት ማሻሻያን በመፍትሄነት ያቀረበው ኢዜማ ህገ መንግስቱ “ምርጫ እስኪደረግ ድረስ ዘላቂ ውጤት ያላቸውን እና ቀጣይ ምርጨውን አሸንፎ ወደ ስልጣን የሚመጣው መንግስት ላይ ተጨማሪ ኃላፊነት የማይጥሉ ተግባራት ተከልክሎ፤ መንግስት እንዲቀጥል በሚያስችል መልኩ ሊሻሻል ይገባል” ብሏል። ይህ መፍትሄም “ቀጥተኛ፣ ህገ መንግስታዊ፣ የማያዳግም እና ተቀባይነት ያለው ነው” ሲል አጽንኦት ሰጥቷል። 

ኢዜማ ባቀረበው የመፍትሄ ሀሳብ “የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድንገተኛ እና ከአቅም በላይ የሆነ ችግር በሚያጋጥምበት ጊዜ ከአንድ አመት ለማይበልጥ ጊዜ ምርጫውን የማራዘም ስልጣን ሊሰጠው ይገባል” ብሏል። ፓርቲው ህገ መንግስቱን በማሻሻል ሂደት ሊኖሩ ስለሚችሉ ህዝባዊ ስብሰባዎችም መፍትሄ ያለውን ጠቁሟል። ሕዝቡ “በወኪሎቹ እና በተለያዩ የቴክኖሎጂ አማራጮች በመጠቀም እንዲወያይ በማድረግ መሸፈን ይቻላል” ሲል አማራጭ ዘዴዎችን አመላክቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)