በተስፋለም ወልደየስ
ከሕገ መንግስቱ እና ከሕገ መንግስታዊ ስርዓቱ ውጭ የሚደረግ ምርጫ ሀገር እና ህዝብን ለከፋ አደጋ የሚዳርግ በመሆኑ መንግስት የሀገርን እና የህዝብን ደህንነት ለመጠበቅ ሲል ወሳኝ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስጠነቀቁ። ስልጣንን በሁከት እና ብጥብጥ ለመያዝ የሚሞክር ማናቸውንም ኃይል መንግስታቸው እንደማይታገስም አስታውቀዋል። የሽግግር መንግስት ምስረታ የሚለው ሀሳብ ለኢትዮጵያ “የማይሆን እና የማይበጅ ነውም” ብለዋል።
ከሕገ መንግስቱ እና ከሕገ መንግስታዊ ስርዓቱ ውጭ የሚደረግ ምርጫ ሀገር እና ህዝብን ለከፋ አደጋ የሚዳርግ በመሆኑ መንግስት የሀገርን እና የህዝብን ደህንነት ለመጠበቅ ሲል ወሳኝ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስጠነቀቁ። ስልጣንን በሁከት እና ብጥብጥ ለመያዝ የሚሞክር ማናቸውንም ኃይል መንግስታቸው እንደማይታገስም አስታውቀዋል። የሽግግር መንግስት ምስረታ የሚለው ሀሳብ ለኢትዮጵያ “የማይሆን እና የማይበጅ” ነውም ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ዛሬ፤ ሐሙስ ሚያዝያ 29፤ ረፋዱን ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክታቸው በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ሳይካሄደ ከቀረው ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ጋር የተያያዙ ጉዳዩችን በስፋት አንስተዋል። በተለያዩ ወገኖች የሚቀርቡ የመፍትሄ ሀሳቦችን በሶስት ከፍለው በዝርዝር ተመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተው ካነሷቸው ጉዳዮች ውስጥ ሕገ መንግስታዊ እውቅና በሌለው መልኩ ምርጫ ለማድረግ እየተደረገ ነው ያሉትን እንቅስቃሴ ነው። በዚህ መልኩ ስልጣን ለመያዝ የሚደረግ እንቅስቃሴ “ፍጹም ተቀባይነት የለውም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ለመከላከል መንግስታቸው እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቀዋል።
“ሕገ መንግስቱ ከደነገገው ስርዓት ውጪ ያለ ምርጫ፤ ሕገ መንግስታዊ እውቅና በሌለው ህገ ወጥ ምርጫ፤ ስልጣን ለመያዝ የሚደረግ እንቅስቃሴ ፍጽም ተቀባይነት የለውም” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። “በሕገ መንግስቱ እና በሕገ መንግስታዊ ስርዓቱ ካልሆነ በስተቀር የጨረባ ምርጫ ለማድረግ መነሳት ሀገርን እና ህዝብን ለከፋ አደጋ የሚዳርግ በመሆኑ መንግስት የሀገርን እና የህዝብን ደህንነት ለመጠበቅ ወሳኝ እርምጃ ለመውሰድ ይገደዳል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

በህገ ወጥ ምርጫ ስልጣን የመያዝ እንቅስቃሴ “ሕገ መንግስቱን፤ የሀገሪቱን ሌሎች ህጎች እና ዓለም አቀፍ ህጎችን የሚጥስ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስታቸው በሕገ መንግስቱ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ኃላፊነቱን ለመወጣት እርምጃ እንደሚወስድ ጠቁመዋል። ይህንን ማድረግ መንግስታቸው “የማይደራደርበት ህገ መንግስታዊ ግዴታ” እንደሆነም አስገንዝበዋል።
“የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት በአንቀጽ 50 የፌደራል መንግስት ስልጣን እና ተግባር ሲዘረዝር ቁጥር አንድ አድርጎ ያስቀመጠው ሕገ መንግስቱን የመጠበቅ እና የመከላከል ኃላፊነት ነው። ይሄንን ኃላፊነት ለመወጣት እና አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ነን” ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ስልጣንን ያለ ምርጫ፤ ከህግ አግባብ ውጪ ለመያዝ ያስባሉ” ላሏቸው ኃይሎችም ጠንከር ባሉ ቃላት መልዕክት አስተላልፈዋል።
“የኮሮና ቫይረስ ስጋት ተጋርጦብን፣ የሀገር ሉዓላዊነት እና ደህንነት ለአደጋ በተጋለጠበት ጊዜ ‘ስልጣን ያለ ምርጫ እና ከህግ አግባብ ውጪ፤ በሁከት እና ብጥብጥ ካልሰጣችሁኝ’ የሚል ማንኛውንም ኃይል እንደማንታገስ ከወዲሁ በግልፅ መንገር እንፈልጋለን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ “ለዚህም በሁሉም ረገድ በቂ ዝግጅት ያለን መሆኑን እንዲታወቅ እንፈልጋለን” የሚል ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።
የሽግግር መንግስት ምስረታን በአማራጭነት የሚያቀርቡ ወገኖች መኖራቸውን በቪዲዮ መልዕክታቸው የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አካሄዱ “በሕገ መንግስቱ ያልተደነገገ እና ህገ መንግስታዊም ያልሆነ ነው” ሲሉ ውድቅ አድርገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ያለ ምርጫ እንዲሁ ተጠራርቶ ስልጣን የሚከፋፈልበት ህጋዊም ሆነ ህገ መንግስታዊ አካሄድ የለም” ብለዋል። “ ‘የፖለቲካ ፓርቲ ብቻ ስለሆንኩ ስልጣን ይገባኛል’ የሚለው ፈሊጥ ዲሞክራሲያዊም፤ ሕገ መንግስታዊም አይደለም” ሲሉም አክለዋል።
“ሕገ መንግስቱ ስልጣን በምርጫ ብቻ እንደሚገኝ ይደነግጋል። ይሄንን መሰረታዊ መርህ በጣሰ ሁኔታ፣ ስልጣን ‘እንደ ድግስ ትሩፋት ለሁላችንም ይዳረስ’ የሚለው አካሄድ በሀገራችን ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት የምናደርገውን ጥረት ወደ ኋላ የሚመለስ፤ ከህዝብ እና ከሀገር ይልቅ የስልጣን ፍላጎት የሚያስቀድም አስተሳሰብ ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሽግግር መንግስት ምስረታን የሚያቀነቅኑ ወገኖችን ወርፈዋል። “የሽግግር መንግስት የሚለው ሀሳብ ከህግ አንጻር ብቻ ሳይሆን ካለንበት ነባራዊ ሁኔታ፤ በንድፈ ሀሳብም ሆነ ከሽግግር ተሞክሮ አንጻር ለኢትዮጵያ የሚሆን እና የሚበጅ አይደለም” ሲሉም ደምድመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)