የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ ቢሮው አዲስ ኃላፊ መደበ

100
3 ደቂቃ ንባብ

በተስፋለም ወልደየስ

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስተዳደርን በዋናነት በገንዘብ ከሚደግፉ ዓለም አቀፍ ተቋማት አንዱ የሆነው የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ለሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮው አዲስ ኃላፊ መደበ። ተቋሙ ኢትዮጵያን ጨምሮ አራት ሀገራትን ለሚከታተለው ቢሮው የመደበው ሴኔጋላዊው ኦስማን ዲዮንን ነው። 

አሁን በስራ ላይ የሚገኙትን ብሪታኒያዊቷን ካሮሊን ተርክን የሚተኩት ኦስማን ኃላፊነቱን የሚረከቡት ከመጪው ሰኔ ወር መጨረሻ ጀምሮ ነው። ኦስማን ለቦታው የተመረጡት “ፉክክር የተሞላበትን የባንኩን የኃላፊዎች ምርጫ ሂደት አልፈው ነው” ተብሏል።  

አዲሱ ኃላፊ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ቅድሚያ የሚሰጧቸው አራት ጉዳዮች እንደሚሆኑ ለሰራተኞች የተሰራጨው እና “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው የባንኩ ውስጣዊ ማስታወሻ ያመለክታል። ከአራቱ ጉዳዮች ውስጥ ሁለቱ የሚዳስሱት የባንኩ የአዲስ አበባ ቢሮ በቀጥታ በሚመለከታቸው የኤርትራ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሱዳን ሀገራት ሊከናወኑ የሚገባቸውን ተግባራት ነው። 

ፎቶ፦ ወርልድ ባንክ ቬትናም  

የዓለም ባንክ ለአፍሪካ በቀረጸው አዲስ ስትራቴጂ በቀደምትነት እንዲተገበሩ የታቀዱ ጉዳዮች ይፈጸሙ ዘንድ አመራር መስጠት ሌላው የአዲሱ ኃላፊ ትኩረት መሆኑ ተጠቅሷል። ባንኩ ኢትዮጵያን የተመለከተ ስትራቴጂ ለማዘጋጀት የሚያደርገው እንቅስቃሴ እና አፈጻጸሙም እንዲሁ ቅድሚያ ከተሰጣቸው ጉዳዮች ውስጥ ተካትቷል።   

ዓለም አቀፉ ተቋም ስትራቴጂውን የሚያዘጋጀው በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ የልማት አጋሮች እና የባንኩ ደንበኞች ጋር በቅርበት በመስራት እንደሆነ የባንኩ ማስታወሻ ጠቁሟል። ስትራቴጂው ይበልጡኑ ትኩረት የሚሰጠው ለዘላቂ ልማት፣ ስራ ፈጠራ እና የአገልግሎት አቅርቦት መሆኑም ተገልጿል።

ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ ባለፉት አምስት ዓመታት በእጥፍ የጨመረው የዓለም ባንክ፤ ድጋፉ በሀገሪቱ ያሳደረው በጎ ተጽዕኖ፤ ይበልጡኑ እንዲጎለብት ማድረጌን እቀጥላለሁ ብሏል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ ባንኩ የኢትዮጵያ መንግስት የሚመራበትን የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ እንደሚያግዝ በማስታወሻው ተጠቅሷል። 

እነዚህን የትኩረት አቅጣጫዎች ይዘው ወደ አዲስ አበባ የሚመጡት አዲሱ የዓለም ባንክ ጽህፈት ቤት ኃላፊ፤ ኦስማን ዲዮን፤ በተቋሙ ላለፉት 20 ዓመታት አገልግለዋል። በውሃ ሃብቶች ምህንድስና ከፈረንሳዩ ሊዮን ዩኒቨርስቲ የዶክትሬት ዲግሪ ያላቸው ኦስማን የዓለም ባንክን የተቀላቀሉት በውሃ ሃብቶች አስተዳደር ባለሙያነት ነበር።  

ፎቶ፦ ወርልድ ባንክ ኢትዮጵያ 

ኦስማን ላለፉት አራት ዓመታት በቬትናም የሚገኘውን የዓለም ባንክ ጽህፈት ቤት ሲመሩ ቆይተዋል። እርሳቸውን ተክተው ወደ ቬትናም የሚጓዙት ተሰናባቿ የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ቢሮ ዳይሬክተር ካሮሊን ተርክ ናቸው። 

ወዳጆቻቸው ኬሪ እያሉ የሚጠሯቸው ኃላፊዋ የኢትዮጵያ ቆይታቸው በፈተና የተሞላ እንደነበር ስራቸውን በቅርበት ሲከታተሉ የነበሩ የኢኮኖሚ ባለሙያ ይናገራሉ። በአንጻራዊነት “የተረጋጋች” ትባል የነበረችው ኢትዮጵያ እርሳቸው የኃላፊነት ቦታውን ከተረከቡ በኋላ በህዝባዊ ተቃውሞ መናጥ የጀመረችበት ጊዜ ነበር። 

ተቃውሞውን ተከትሎ የታወጁ ሁለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆችን ያሳለፉት ካሮሊን የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ኃይለማርያም ደሳለኝ ከስልጣናቸው ሲለቅቁ ተመልክተዋል። ኃላፊዋ ኃይለማርያምን ተክተው የጠቅላይ ሚኒስትርነት መንበሩን የተረከቡት አብይ አህመድ የተገበሯቸውን አነጋጋሪ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎችንም ተከታትለዋል።

ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ማሻሻያዎች ያለውን በጎ አመለካከት በይፋ ሲገልጽ የቆየው የዓለም ባንክ ባለፉት ሁለት ዓመታት ለኢትዮጵያ በርካታ የገንዘብ ድጋፎች አድርጓል። የባንኩ ከፍተኛ ኃላፊዎችም ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተገናኝተዋል።

ፎቶ፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት

የዓለም ባንክ ባለፈው ታህሳስ ወር ብቻ የአብይ መንግስት ለነደፈው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የሚውል ሶስት ቢሊዮን ዶላር ብድር እንደሚሰጥ አስታውቆ ነበር። ኢትዮጵያ በካሮሊን የዳይሬክተርነት ዘመን ያገኘችውን ድጋፍ የገመገሙት የኢኮኖሚ ባለሙያው፤ የገንዘብ ፈሰሱ ኢትዮጵያን “የዓለም ባንክን ከፍተኛ ድጋፍ ከሚያገኙ ጥቂት ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ አድርጓታል” ይላሉ። ለዚህም በእርሳቸው የአምስት ዓመት የኃላፊነት ጊዜ ሀገሪቱ ከባንኩ ታገኘው የነበረው ብድር ከሰባት ቢሊዮን ዶላር ወደ 13 ቢሊዮን ዶላር ማደጉን በማስረጃነት ይጠቅሳሉ። 

ኢትዮጵያ የዓለም ኢኮኖሚን እያናጋ ያለውን ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመቋቋም የሚያስችላትን የገንዘብ ድጋፍ ከተቋማቸው እንድታገኝም ኃላፊዋ አስችለዋል። የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ለዚሁ ዓላማ የሚውል የ82.6 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ባለፈው መጋቢት ወር መጨረሻ አጽድቋል።

ተሰናባቿ የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ቢሮ ኃላፊ አሁን በስልጣን ላይ ካሉ የመንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር “የቀረበ ግንኙነት” እንዳላቸው ይነገርላቸዋል። የኢኮኖሚ ባለሙያውም ይህንኑ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። ይህም ሆኖ ግን ኃላፊዋ ከኢትዮጵያ መንግስት የሚቀርብላቸውን ተደጋጋሚ የገንዘብ ድጋፍ ጥያቄ ማስተናገድ ላይ “ቁጥብ ነበሩ” ይላሉ። የገንዘብ ድጋፉ ለስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ብቻ እንዲውል የማድረግ አካሄድን ይከተሉ እንደነበርም የኢኮኖሚ ባለሙያው መለስ ብለው አስታውሰዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)