ፖሊሶች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እና ምዕመናን ላይ “ከፍተኛ እርምጃ እየወሰዱ ነው” ተባለ

በተስፋለም ወልደየስ

በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ መደረግ ከጀመረ ወዲህ የፖሊስ ኃይሎች “በቤተ ክርስቲያን በር ላይ በመቆም በመንፈሳዊ አገልጋዮች እና በምዕመናን ላይ ከፍተኛ እርምጃ እየወሰዱ ነው” ሲል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የተዘጋጀ ሪፖርት ወቀሰ። ሪፖርቱን ያዘጋጀው የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በቤተ ክርስቲያኒቱ የተቋቋመው ግብረ ኃይል ነው። 

“የኮቪድ 19 የኮሮና ቫይረስ የተስፋ ልዑክ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ግብረ ኃይል ከተቋቋመበት ከመጋቢት 12 ጀምሮ ያከናወናቸውን ተግባራት በዘረዘረበት ሪፖርት ላይ ነው በጸጥታ ኃይሎች ላይ ወቀሳውን የሰነዘረው። ግብረ ኃይሉ በ16 ገጾች የተጠናቀረውን ሪፖርቱን መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ለሚገኘው የቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዕተ ጉባኤ ዛሬ ረቡዕ ግንቦት 5፤ 2012 አቅርቧል። 

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ሪፖርት፤ “ማንም እገዛ ሳይጠይቃቸው” በቤተ ክርስቲያን መግቢያዎች ላይ የሚቆሙ ፖሊሶች በአገልጋዮች እና በምዕመናን ላይ ከክልከላ እስከ ስድብ እና ድብደባ የደረሱ “የኃይል እርምጃዎች እየወሰዱ ይገኛሉ” ሲል ወንጅሏል። የፖሊስ ኃይሎቹ “በቤተ ክርስቲያን በር ላይ በመቆም፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሃይማኖታዊ ሥርዓተ አምልኮ በሚጻረር መልኩ፤ ጥንቃቄ አድርገው የሚያገለግሉ የዘወትር ልዑካን፤ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብተው በተወሰነው ቁጥር መጠን አገልግሎት እንዳያከናውኑ [አድርገዋል]” በማለት ሪፖርቱ ይከስሳል። 

ሪፖርቱ የእምነቱ ተከታዮች ቤተክርስቲያኒቱ የምትሰጠውን የተለያዩ አገልግሎቶች እንዳያገኙ ፖሊሶች “እያስቸገሩ ይገኛሉ” ሲልም ኮንኗል። “ይህንንም የሚያደርጉት በራሳቸው ተነሳሽነት እና ቤተ ክርስቲያናችንን ዝቅ ያደረጉ በመሰላቸው የሌላ እምነት ተከታዮች ነው” የሚለው ሪፖርቱ ለዚህም በማሳያነት ከትንሳኤ በዓል በፊት በነበሩ ሶስት ቀናት ብቻ በአዲስ አበባ እና አካባቢው ባሉ ስድስት አብያተ ክርስቲያናት የተፈጸሙ፣ “አግባብነት የሌላቸው” ያላቸውን ድርጊቶች ዝርዝሯል።  

“በጥበቃነት የተመደቡ አንዳንድ የፖሊስ አካላት የታዘዙበትን ዓላማ በመተው ምእመናን ለቁጣ የሚጋብዙ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ ነበር” ያለው ሪፖርቱ የፖሊስ ኃይልን የሚያሰማራው አካል ተጨማሪ ችግር የሚሆኑ ጉዳዮች ከመከሰታቸው በፊት ሁኔታውን በአግባቡ እንዲያጤን ሪፖርቱ ጠይቋል። “ሌላ እምነት ያላቸው ፖሊሶች መመደባቸው በምእመናን ዘንድ ትልቅ ቅሬታን ሊፈጥር እንደሚችል” የሚጠቅሰው ሪፖርቱ አሁንም ቢሆን ግን የፖሊሶቹ እርምጃ “ ‘ሆን ተብሎ እኛን ለመጉዳት እየተሠራ ነው’ የሚል አንድምታ እየተሰጠው” እንዳለ አብራርቷል።

ከአሁኑ በኋላ “ጥንቃቄ የሚያሻቸውን ጉዳዮች በአጽንዖት ተመልክቶ መፍትሔ መሻት ያስፈልጋል” የሚለው ሪፖርቱ በአብያተ ክርስቲያናት በፖሊሶች የሚፈጠረውን ችግር ለመቅረፍ የመፍትሔ ሀሳቦች ያላቸውን ጠቁሟል። ፖሊሶች “በቤተ ክርስቲያን በጥበቃነት መቆማቸው አግባብ አለመሆኑን” የሚያነሳው አንደኛው የመፍትሔ ሀሳብ በእነሱ ምትክ ጥበቃው በሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች እና በአካባቢው ወጣቶች እንዲከናወን ይጠይቃል። 

ይህ የማይቻል ከሆነ “የእምነቱ ተከታይ የሆኑ እና የቤተ ክርስቲያኗን ሥርዓት ጠንቅቀው የሚያውቁ የፖሊስ አባላት ብቻ” ለጥበቃ እንዲመደቡ ሪፖርቱ ሀሳብ አቅርቧል። “እነዚህ የፖሊስ አባላትም ቢሆኑ የቤተ ክርስቲያኑን ዙሪያ ከመጠበቅ በዘለለ በጭራሽ ወደ ቅጽረ ቤተ ክርስቲያን እንዳይገቡ” የሚጠይቀው ሪፖርቱ “መጠበቅ አለባቸው ከተባለ እንኳን በምእመናን ላይ ምንም አይነት የኃይል ርምጃ መውሰድ የሚችልበት አሠራር እንደሌለ ከተማ አስተዳደሩ ለፖሊሶች ትእዛዝ ይስጥ” ብሏል።  

ይህ ሁሉ ሆኖ የሚገጥሙ ችግሮች ካሉ “ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አጥቢያው ከተቋቋመው ግብረ ኃይል ጋር በመነጋገር እንዲፈቱ እንዲደረግ” በሪፖርቱ ላይ ተመልክቷል። ሪፖርቱ በጸጥታ ኃይሎች ተከሰተ ያለውን ችግር ለመፍታት ያቀረበውን የመፍትሔ ሀሳብ ያጠቃለለው “ጥፋት ፈጽመዋል” ባላቸው የፖሊስ አካላት ላይ “እንደጥፋታቸው መጠን ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድባቸው” በመጠየቅ ነው። 

አስራ ሶስት አባላት ያሉበት “የኮቪድ 19 የኮሮና ቫይረስ የተስፋ ልዑክ” ያቀረበውን ሪፖርት ያደመጡት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ማሳለፋቸውን ጉባኤውን በቅርበት የተከታተሉ አንድ ምንጭ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ ዛሬ ይጠናቀቃል ተብሎ ከሚጠበቀው ጉባኤ በኋላ ይፋ እንደሚደረግም ጨምረው ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)