ኢትዮጵያ የስደተኞች ጥገኝነት ፖሊሲ እና ስነ ስርአቷን ግልፅ እንድታደርግ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠየቀ

በሐይማኖት አሸናፊ

ኢትዮጵያ ከ10 ዓመት በላይ ለኤርትራውያን ስደተኞች ስትሰጥ የነበረውን የቡድን ጥገኝነት ማቆሟን ተከትሎ የጥገኝነት ፖሊሲ እና ስነ ስርአቷ ላይ ለውጥ አድርጋ እንደሆነ በግልፅ እንድታስታውቅ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠየቀ። ጥያቄውን ለኢትዮጵያ መንግስት ያቀረበው በኤርትራ ያለውን የሰብአዊ መብት አያያዝ እንዲከታተል በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ስር የተቋቋመው ልዩ ራፖርተር ጽህፈት ቤት ነው።  

የኤርትራን ጉዳይ የሚከታተሉት ልዩ ራፖርተር ዳንኤላ ካራቬትዝ ከሶስት ሳምንት በፊት ለኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በላኩት ደብዳቤ፤ ኢትዮጵያ ለኤርትራዊያን ስደተኞች ስትሰጥ የነበረውን ጥገኝነት የሚመራበትን ስነ ስርአት እና ፖሊሲ፤ ከጥር 2012 ዓ.ም. መጨረሻ ጀምሮ በተግባር መቀየሯን መረዳታቸውን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ የተከተለችው ይህ አካሄድም እንዳሳሰባቸው ጠቁመዋል።   

በሚያዚያ 21፤ 2012 ዓ.ም የተፃፈው እና “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ደብዳቤ ኢትዮጵያ ለኤርትራውያን ስደተኞች ስታደርግ የቆየችውን እገዛ በበጎ መልኩ ያነሳል። የኤርትራን የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች እንዲከታተሉ በጥቅምት 2011 የተመደቡት ቺሊዊቷ ልዩ ራፖርተር ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ስላለው ለውጥ በጎ ጎኖች ለተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ምክር ቤት መግለፃቸውን በደብዳቤያቸው አስታውሰዋል። ነገር ግን በቅርቡ የታዩት አካሄዶች “ኢትዮጵያ አዲስ ባፀደቀችው የስደተኞች አዋጅ እና የኤርትራዊያን ስደተኞችን መብት በማክበር ያሳየቻቸውን ለውጦች የሚቀንስ ነው” ብለዋል፡፡

“ኢትዮጵያ ለኤርትራዊያን ስደተኞች ለረጅም ጊዜ በሯን ክፍት ማድረጓን እና በኤርትራውያን ስደተኞች ዘንድም እንደ አስተማማኝ መሸሸጊያ የተወሰደች አገር ሆና መቆየቷን ሳላደንቅ አላልፍም” ሲሉ ልዩ ራፖርተሯ በደብዳቤያቸው ላይ አስፍረዋል። “ከጥቂት ወራት ወዲህ የተከሰቱት ለውጦች ግን በተለይም ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን አደጋ ላይ ጥሏል” ብለዋል። 

“ኢትዮጵያ ለኤርትራዊያን ስደተኞች ለረጅም ጊዜ በሯን ክፍት ማድረጓን እና በኤርትራውያን ስደተኞች ዘንድም እንደ አስተማማኝ መሸሸጊያ የተወሰደች አገር ሆና መቆየቷን ሳላደንቅ አላልፍም። ከጥቂት ወራት ወዲህ የተከሰቱት ለውጦች ግን በተለይም ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን አደጋ ላይ ጥሏል” – ዳንኤላ ካራቬትዝ

“ላቅ ላለ አደጋ ተጋልጠዋል” በሚል በደብዳቤው የተጠቀሱት ከቤተሰቦቻቸው የተጠፋፉና ለብቻቸው የተሰደዱ ህፃናት እና ታዳጊዎች እንዲሁም የህክምና እርዳታ የሚሹ ስደተኞች ናቸው። የእነዚህ ስደተኞች ሁኔታ ኢትዮጵያ አለም አቀፍ መለኪያዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ የጥገኝነት ስነ-ስርአት እና ፖሊሲዋን የተመለከተ ግልፅ መመሪያ በማውጣት፣ ይፋ እንድታደርግ ለመጠየቅ ምክንያት እንደሆነ ዳንኤላ አብራርተዋል። በመስክ ላይ ለሚገኙ ሰራተኞችም ግልፅ የሆነ የስራ መመሪያ እንዲሰጣቸውም ጥያቄ አቅርበዋል። 

የልዩ ራፖርተሯ ደብዳቤ ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ አዳዲስ ስደተኞች የጥገኝነት ምዝገባ እንደማይደረግላቸው እና በአፋር እንዲሁም በትግራይ ክልል ባሉ መጠለያዎች መሰረታዊ አገልግሎቶች እያገኙ አለመሆኑን ያስረዳል። “በእንዳባጉና እና አሳይታ የስደተኛ መጠለያ ካምፖች የሚገኙ የኢትዮጵያ የስደተኞች ኤጀንሲ ሰራተኞች ኤርትራውያን ስደተኞች የሚያቀርቡትን የጥገኝነት ምዝገባ ጥያቄ አይቀበሉም፤ ወደ ኤርትራ እንዲመለሱም ነግረዋቸዋል” ሲሉ ልዩ ራፖርተሯ በደብዳቤያቸው ወቅስዋል። 

በድንበር ላይ የሚቀርቡ የጥገኝነት ማመልከቻዎችን ያለመቀበል “ስደተኞችን መልሶ ወደ መጡበት እንደ መላክ ይቆጠራል” ሲሉ አጽንኦት የሚሰጡት ዳንኤላ ኢትዮጵያ ያሉባትን አለም አቀፍ ግዴታዎች እና አለም አቀፍ ህጎችን ባከበረ መልኩ የኤርትራውያን ስደተኞችን መብት እንድታከብር ጠይቀዋል። በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት በተቀባይ ሀገራት ለስደተኞች የሚሰጠው እውቅና የወል ጥገኝነት ወይም “ፕሪማ ፋሼ” ተብሎ ይታወቃል።

ይህ አሰራር ስደተኞች በግላቸው ለጥገኝነት የሚያበቃ ምክንያት ሳይጠየቁ በተቀባይ አገር ወይም በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ተቋም የሚስተናገዱበት አካሄድ ነው። ለዚህም ከሚሰደዱበት ሀገር ባለ ሁኔታ፣ አገር አልባ ሲሆኑ እና በመሰል ምክንያቶች የተለዩት አገር ዜጋ ወይም የተባለው ቡድን አካል በመሆናቸው ብቻ ለጥገኝነት ብቁ ሆነው ሲገኙ በግላቸው ወደ አገራቸው ቢመለሱ ሊያጋጥማቸው የሚችል ከባድ አደጋን ማስረዳት ሳይጠበቅባቸው ጥገኝነት ያገኛሉ። 

ባለፈው መጋቢት ወር የወጣ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት ሪፖርት እንደሚያመለክተው ባለፈው የፈረንጆቹ 2019 ዓመት ብቻ 70,129 ጥገኝነት ጠያቂ ኤርትራውያን ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል። በኢትዮጵያ በአጠቃላይ 170 ሺህ ገደማ ኤርትራውያን ስደተኞች እንዳሉ ሪፖርቱ ይገልጻል። ከእነዚህ ውስጥ 70 ሺህ ያህሉ ከመጠለያ ጣቢያዎች ውጪ የሚኖሩ ሲሆኑ 18 ሺህ ገደማ የሚሆኑት ደግሞ በከተሞች ውስጥ እንደሚኖሩም ይጠቁማል። 

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ኤርትራውያን ስደተኞችን የሚያስተናግዱ ስድስት መጠለያዎች ያሉ ሲሆኑ አራቱ በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው። በትግራይ ውስጥ ካሉ የስደተኞች መጠለያዎች አንዱ የሆነው ህፃፅ 26 ሺህ ገደማ ስደተኞች ያስተናግድ እንደነበር መረጃዎች ያመልክታሉ። የህፃፅ የስደተኞች መጠለያን የኢትዮጵያ የስደተኞች እና የስደት ተመላሾች ኤጀንሲ መዘጋቱን ይፋ ሊያደርግ አስቦ የነበረ ቢሆንም ከኮቪድ 19 መከሰት ጋር በተያያዘ መዘግየቱን መረዳታቸውንም ልዩ ራፖርተሯ በደብዳቤያቸው ጠቅሰዋል።  

“ይህ ውሳኔ ሲወሰንም ስደተኞችን የማወያየት ስራ ያልተሰራ ሰሆን አሁንም ክቡርነትዎን የምጠይቀው ስደተኞችን የሚመለከቱ ውሳኔዎች ሲወሰኑ እነሱን ማወያየት እና ስደተኞችን የማስለቀቅ ስራዎች በፈቃደኝት ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት” ሲሉ ዳንኤላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ጠይቀዋል።

ከህፃፅ የስደተኞች መጠለያ እንዲለቅቁ የሚደረጉ ስደተኞች ወደ ማይ አኒ እና አዲ ሃሩሽ መጠለያዎች እንዲዘዋወሩ የሚደረግ ከሆነም በእነዚህ ቦታዎች ያለው የመሰረተ ልማት እስከሚስተካከል ጊዜ እንዲሰጥ እንዲሁም የሰብዓዊ ድርጅቶች ምግብ እና መሰረታዊ አገልግሎቶችን እንዲያቀርቡ እንዲፈቀድም በደብዳቤያቸው አሳስበዋል። ልዩ ራፖርተሯ የኮሮና ቀውስ እስኪፈታ ድረስ ስደተኞችን የማዘዋወር ስራው እንዲቆምም ተማጽኗቸውን አቅርበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)