የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ኢትዮጵያ ወደ ዋሽንግተኑ ድርድር እንድትመለስ ግፊት ሊያደርጉ ነው

የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ የአባይ ውሃ አጠቃቀም ድርድርን በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ሊወያዩ ነው። ውይይቱ ኢትዮጵያ በአሜሪካ እና ዓለም ባንክ አሸማጋይነት ወደሚደረገው ድርድር እንድትመለስ የማግባባት አላማ ያለው ነው ተብሏል።  

የታችኞቹ የአባይ ተፋሰስ አገራት የሆኑትን ግብጽ እና ሱዳንን ባሳተፈው ድርድር ላይ ስትካፈል የቆየችው ኢትዮጵያ “ከአሜሪካ በኩል ጫና እየደረሰብኝ” በማለት ከባለፈው የካቲት ጀምሮ ራሷን አግላለች። ኢትዮጵያ ከድርድሩ ብትቀርም  በአባይ ወንዝ ላይ እያስገነባች የሚገኘውን የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ደረጃ የውሃ ሙሌት በመጪው ሐምሌ ወር ለመጀመር ቁርጠኛ መሆኗን በተደጋጋሚ ገልጻለች። 

የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር የግድቡን የመጀመሪያ ደረጃ ውሃ ሙሌት በተመለከት ኢትዮጵያ ያሰናዳችውን የስምምነት ረቂቅ  እንደማይቀበሉ ባለፈው ሳምንት ቢገልጹም ከኢትዮጵያ አቻቸው ጋር የመወያየት ዕቅድ እንዳላቸው ግን የሱዳን መንግሥት ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ሀምዶክ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር የሚወያዩት “የሶስትዮሽ ድርድሩ በአፋጣኝ እንዲጀመር ለማሳሰብ” እንደሆነ መግለጫው ጠቁሟል። 

ፎቶ፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት

የሱዳን እና የግብጽ ከፍተኛ ባለስልጣናት በጉዳዩ ላይ ዛሬ መምከራቸውም በመግለጫው ተጠቅሷል። በቪዲዮ የተካሔደውን የሁለቱ ሀገሮች ውይይት የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የግብፁ አቻቸው ሙስጠፋ ማዶብሊ መርተውታል። በውይይቱ ላይ የየሀገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና የስለላ ተቋማት ኃላፊዎችም ተሳትፈዋል።  

ውይይቱ የተደረገው ሶስቱ ሀገራት በህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላል እና አሰራር ላይ ያሏቸውን ልዩነቶች መፍታት የሚያስችላቸውን ድርድር እንዲቀጥሉ ለማድረግ ታቅዶ እንደሆነ የሱዳን መንግስት መግለጫ አትቷል።  በሱዳን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ድረ ገጽ ይፋ የሆነው ይህ መግለጫ “በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ፣ የሱዳን እና የግብፅን ጥቅሞች እውቅና ከሚሰጥ አንዳች ሥምምነት መድረስ እንደሚያስፈልግ ሁለቱ ወገኖች አጽንኦት ሰጥተዋል” ብሏል። 

ከሶስት ቀናት በፊት ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ የነበረው የሱዳን ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር ከተነጋገረባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ  አንዱ እንደነበር  ተገልጿል። የልዑካን ቡድኑ የተመራው በሱዳን የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር አምባሳደር ዑመር ባሕር ማኔስ ነበር። 

ፎቶ፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት

የዛሬው የሱዳን መንግስት መግለጫ “የሶስቱ ሀገራት  ድርድር በዋሽንግተን ዲሲው ስምምነት መሰረት መቀጠል አለበት” ቢልም ኢትዮጵያ ግን ከዚህ የተለየ አቋም ማራመድ ከጀመረች ሰነባብታለች። የኢትዮጵያ የውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ አገራቸው ወደ ዋሽንግተኑ ድርድር ፊቷን የማዞር ሐሳብ እንደሌላት በቅርቡ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

ከሳምንት በፊት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በግድቡ ጉዳይ ላይ ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ ሚኒስትሩ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት “አሜሪካ ስላለው ሂደት ሰነባበትን እኮ ከተውነው» ብለው ነበር። “ቀጣይ ድርድር የሚኖረው በሶስቱ ሀገሮች መሀል ነው» ያሉት ስለሺ አሸማጋይ ካስፈለገ “ጉዳዩን ወደ አፍሪካ በመመለስ ነው” ሲሉ ኢትዮጵያ የአደራዳሪ ለውጥ እንደምትሻ ገልጸዋል።

የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ ዛሬ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የአፍሪካ ሀገራት አምባሳደሮች በተሰጠ ገለፃም ይኸው የኢትዮጵያ አቋም ተንጸባርቋል። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት በውይይቱ የተሳተፉ አምባሳደሮች “በህዳሴ ድግብ ዙሪያ አደራዳሪ የሚያስፈልግ ከሆነ የአፍሪካ ሀገራት እና የአፍሪካ ህብረት ይህንን የመወጣት አቅም አላቸው” የሚል አስተያየት ከማብራሪያው በኋላ መስጠታቸውን ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)