የሕይወት ተፈራ አዲስ መጽሐፍ ገበያ ላይ ሊውል ነው

525

በተስፋለም ወልደየስ

“ማማ በሰማይ” (Tower in the sky) በተሰኘው መጽሐፏ ይበልጥ የምትታወቀው ሕይወት ተፈራ የጻፈችው አዲስ ታሪካዊ ልብወለድ ገበያ ላይ ሊውል ነው። መጽሐፉ በ18ኛው ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ የመሪነት ሚና በነበራቸው በእቴጌ ምንትዋብ ታሪክ ላይ ያጠነጥናል።

በክፍለ ዘመኑ ለዘጠኝ ዓመታት ብቻ በንግስና የቆዩት የአጼ ባካፋ ባለቤት እቴጌ ምንትዋብ፤ ከባላቸው ሞት በኋላ በነበሩት 40 ዓመታት በኢትዮጵያ የአስተዳደር እና መሪነት አሻራቸው ጉልህ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ። የወቅቱ የነገስታት መቀመጫ በነበረችው ጎንደር እና ጣና ሐይቅ ላይ ያሰሯቸው እና ያሳደሷቸው አብያተ ክርስቲያናት ዛሬም ስማቸውን የሚያስጠሩ ሆነዋል።

የእቴጌይቱን መጠሪያ ስም የተዋሰው አዲሱ የሕይወት ተፈራ መጽሐፍ የምንትዋብን የግል እና የቤተሰብ ታሪክ፣ በመሪነት በቆዩባቸው አመታት ያጋጠሟቸውን ፈተናዎች፣ ለሀገሪቱ ያበረከቷቸውን አስተዋጽኦዎች እንዲሁም ለጥበብ የነበራቸውን ፍቅር የሚተርክ እንደሆነ የመጽሐፉን ረቂቅ ጽሁፍ ያነበበው ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ይናገራል። በታሪክ የሚታወቁ ግለሰቦችን በፈጠራ ከተጨመሩ ገጸ ባህሪያት ጋር በማሰናሰል የቀረበበት ይህ መጽሐፍ የምንትዋብን ሰውኛ ማንነት ይበልጥ አጎልቶ የሚያሳይ እንደሆነ ደራሲው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጿል። 

እንዳለጌታ ከመጽሐፉ ጀርባ ባሰፈረው ምስክርነትም ይህንኑ አስተያየት የሚያጠናክር አገላለጽ ተጠቅሟል። “የመካከለኛው ዘመን የታሪክ መጋረጃ በዚህ ልክ በሥነ ጹሁፋችን ተገልጦ አያውቅም” የሚለው ደራሲው “ንግሥቶቻችንም በዚህ ልብወለድ ልክ እንደ ሰው በፍቅር ሲፈተኑ፣ በጥበብ ርሃብ ሲናውዙ፣ እንደ ሀገር መሪ ኅያው ሐውልት ለማኖር ሲኳትኑ፣ ሰላምን ለማዝነብ ሲባዝኑ ታይተው አያውቁም” ሲል መጽሐፉን አወድሷል። 

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በስፋት ታሪካቸው ያልተወሳላቸው እቴጌ ምንትዋብ ለተቋማት ግንባታ እና ለስነ ጥበብ እድገት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍ ያለ እንደነበር እንዳለጌታ ያስረዳል። በጥበቡ ረገድ ባለቅኔዎች እና ሰዓሊዎች “ክብደት እና ክብረት እንዲሰጣቸው”፣ ከዚያም ባሻገር ስራዎቻቸውን “ተቋማዊ” በሆነ መልኩ እንዲያቀርቡ እንዳስቻሉ ደራሲው የታሪክ መዛግብትን አጣቅሶ ያስታውሳል። 

ሕይወት ይህን የታሪክ እውነታ ለታሪካዊ ልብወለዷ በግብዓትነት ተጠቅማበታለች። ምንትዋብ ከአጼ ባካፋ ጋር በጋብቻ ከመጣመራቸው በፊት የፍቅር ወዳጃቸው አድርጋ በመጽሐፉ የሳለችው ቀለምን ከሸራ ጋር የሚያዋድድ ሰዓሊ ነው። የራሷን የፖለቲካ ተሳትፎ በተረከችበት “Tower in the sky” በተሰኘው የበኩር ስራዋ ፤ የፍቅር ህይወቷን ሳቢ በሆነ መልኩ የተረከችው ደራሲ፤ በአዲሱ መጽሐፏም ለጥንዶች አፍላ ፍቅር ቦታ ሰጥታለች። 

አዲሱ የሕይወት መጽሐፍ ደራሲዋ ከዚህ ቀደም ከጻፈቻቸው መጻሕፍት “እጅጉን የተለየ ነው” የሚለው እንዳለጌታ ለዚህም ማስረጃ ያላቸውን ከመጽሐፉ ጀርባ ባሰፈረው አስተያየት ዘርዝሯል። “ይዛ የተነሳቻት ባለታሪክም፣ ታሪኩ ያጠነጠነበት ዘመንም ለኢትዮጵያ ሥነ- ጽሑፍ ድንግል ነው። ሳይነካ ቆይቷል” ሲል የሚንደረደረው እንዳለጌታ “የሕይወት ብዕር፣ በእቴጌ ምንትዋብ አማካይነት፣ በፈጠራ ስራዎቻችን ውስጥ ችላ ተብሎ፣ ወይም ተዘግቶ የነበረውን ዘመን ከፍቶና ገርስሶ፣ ቋንቋን፣ ውበትን፣ ጥበብን ፍልስፍናንና እንደፎክሎር ያሉ ዕንቁዎቻችንን አስቆጠረን” ሲል ደራሲዋን አሞካሽቷል። 

ሕይወት ወደ ኋላ ክፍለ ዘመን ተመልሳ ታሪክን ስትፈትሽ እና በዚያ ላይ የተመሰረተ ልብወለድ ስትጽፍ የአሁኑ የመጀመሪያዋ አይደለም። “ኀሠሣ” (Mine to Win) የተሰኘው ሁለተኛ መጽሐፏም መቼቱን በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ አካባቢ ያደረገ ነው። ደራሲዋ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአብነት ትምህርት ቤቶች እና ተዋነይ በተሰኘው እውቅ የቅኔ ተማሪ ህይወት ላይ ያጠነጠነውን ይህን መጽሐፍ ስታዘጋጅ ቦታው ድረስ በመጓዝ ሰፊ ጥናት ማድረጓ በወቅቱ ተገልጾ ነበር። 

ደራሲዋ አዲሱ ስራዋንም አንድ ዓመት ተኩል ገደማ ወስዳ በተመሳሳይ መልኩ ማዘጋጀቷን በቅርብ የሚያውቋት ይናገራሉ። በመጽሐፉ ዋና ገጸ ባህሪ ምንትዋብ የተገነቡ አብያተ ክርስቲያናትን እና ህንጻዎችን በስፍራዎቹ በመገኘት መመልከቷንም ያስረዳሉ። ስለ እቴጌ ምንትዋብ፣ ስለ ዘመኑ፣ ስለ ቋንቋ አጠቃቀማቸው እና ተያያዥ ጉዳዮች የሚያስረዱ መዛግብትን መፈተሿን እና ግለሰቦችንም ማነጋገሯን ያክላሉ።  

መጽሐፍቶቿን በእንግሊዘኛ ቋንቋ ጽፋ ለንባብ ካበቃች በኋላ በአማርኛ ቋንቋ እንዲተረጎሙ ስታደርግ የቆየችው ሕይወት ተፈራ በአዲሱ ስራዋ ለየት ያለ አካሄድ ተከትላለች። 248 ገጾች ያሉትን “ምንትዋብ” መጽሐፍ ሙሉ ለሙሉ የጻፈችው በአማርኛ ነው። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ስለ መጽሐፉ ተጨማሪ መረጃዎች ለማግኘት ለደራሲዋ ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። 

ሆኖም ለደራሲዋ ቅርበት ያላቸው ምንጮች መጽሐፉ አሁን በማተሚያ ቤት እንደሚገኝ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የሕይወትን ቀደምት መጽሐፍት ያተመው ኢክሊፕስ ማተሚያ ቤት የአዲሱን መጽሐፍ አምስት ሺህ ኮፒ የህትመት ትዕዛዝ መቀበሉን ምንጮች ጠቁመዋል። በ15 ቀናት ውስጥ ህትመቱ እንደሚገባደድ የሚጠበቀው ይህ መጽሐፍ በ150 ብር ዋጋ ለገበያ እንደሚቀርብም ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)