በሶማሌ ክልል ምክር ቤት ምን ተከሰተ?

በሐይማኖት አሸናፊ

ከ10 ወራት በኋላ ዛሬ ሐሙስ ግንቦት 13፤ 2012 አስቸኳይ ስብሰባውን ያካሄደው የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ጉባኤ በከፍተኛ ተቃውሞ ተስተጓጉሎ እንደነበር የዓይን እማኞች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ። ለጉባኤው መታወክ ምክንያት የሆነው ለአስቸኳይ ስብሰባ ከተያዙ አጀንዳዎች በተጨማሪ ሌሎች ሶስት አጀንዳዎች መጨመር አለባቸው ባሉ እና በቀሪዎቹ የምክር ቤቱ አባላት መካከል ያለመግባባት በመፈጠሩ መሆኑን የዓይን እማኞቹ ተናግረዋል። 

በምክር ቤቱ ምክትል አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ፍርደውሳ መሐመድ አማካኝነት ለጉባኤው በመጀመሪያ ቀርበው የነበሩ አጀንዳዎች ስድስት ነበሩ። ከአጀንዳዎቹ መካከል የምክር ቤቱን አፈ ጉባኤ የስራ መልቀቂያ መርምሮ ማፅደቅ፣ የክልሉን መንግስት ሪፖርት ማዳመጥ እና የአዳዲስ የካቢኔ አባላትን ሹመት ማፅደቅ ይገኙበታል። አምስት የተለያዩ አዋጆችን እና የምክር ቤቱን ቃለ ጉባኤ ማፅደቅም በአጀንዳዎቹ ውስጥ ተካትተዋል።

ምክር ቤቱ መርምሮ እንዲያጸድቃቸው የቀረቡለት አዋጆች ውስጥ የአነስተኛ ንግድ ተቋም ኤጀንሲ፣ የአደጋ መከላከል እና ዝግጁነት የገንዘብ ፈንድን የተመለከቱ እንደዚሁም የቤቶች ልማት ኤጀንሲን እና የሸሪአ ፍርድ ቤቶችን እንደገና ለማቋቋም የቀረቡ ድንጋጌዎች ናቸው። የምክር ቤቱ አባል የሆኑት ዶ/ር ኒምአን ሃመሬ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት ያለመግባባቱ የተከሰተው በሶስት አጀንዳዎች ላይ ነው። ካወዛገቡት አጀንዳዎች መካከል የክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ ከስልጣን እንዲነሱ ወይም እንዲቀጥሉ “የማስተማመኛ ድምፅ (vote of confidence)” እንዲሰጥ የሚለው አንዱ እንደሆነ ገልጸዋል።  

ፎቶ፦ የሶማሌ ክልል መገናኛ ብዙሃን 

አጀንዳ አንድ

የሶማሌ ክልል ምክር ቤትን ከመስከረም 2011 ጀምሮ በአፈ ጉባኤነት የመሩት አብዲ መሐመድ ከአንድ ወር በፊት ድንገተኛ የስራ መልቀቂያ ማስገባታቸው የክልሉን ፖለቲካ በቅርበት በሚከታተሉ ወገኖች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል። አፈ ጉባኤው የስራ መልቀቂያ ማቅረባቸው በክልሉ መገናኛ ብዙሃን ጭምር በይፋ ተነግሮ ነበር። የስራ መልቀቂያቸው ዕጣ ፈንታ ምን እንደሆነ በግልጽ ሳይነገር የክልሉ የማዕድን እና ኢነርጂ ቢሮ ሃላፊ ሆነው መሾማቸው በሶማሌ ክልል ቴሌቪዥን መዘገቡ ሲተች ከርሟል።

ይህ አካሄድ በዛሬው የክልሉ ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤ ተቃውሞን ቀስቅሷል። የተቃውሞው መነሻ ምክንያትም “አፈጉባኤውን የማንሳት እና የመሾም ስልጣን የምክር ቤቱ ሆኖ ሳለ ምክር ቤቱ መልቀቂያቸውን ሳይቀበል እንዴት የስራ አስፈፃሚው አባል ሆኑ?” የሚል መሆኑን ዶ/ር ኒምአን ያስረዳሉ። የክልሉን ሕገ መንግስት አንቀጽ 50 የሚጠቅሱት የምክር ቤቱ አባል “የአፈ ጉባኤው መልቀቅ በድምፅ ጸድቆ ለአዲስ አፈ ጉባኤ መዶሻቸውን ማስረከብ እንጂ ቀድሞ በስራ አስፈፃሚው የሚወሰን ነገር አይደለም” ይላሉ። 

የምክር ቤቱ አባላት የአፈ ጉባኤውን መልቀቂያ ተቀብለው እንዲያጸድቁ በመጀመሪያ አጀንዳነት ቢቀርብላቸውም የአካሄድ ጥያቄዎችን በማንሳት ጭምር ተቃውሞ ማቅረባቸውን የዓይን እማኞች ገልጸዋል። ጉባኤው ሲጀመር “ምክትል አፈ ጉባኤዋ መምራት የለባቸውም”፣ “የቀድሞው አፈ ጉባኤ ከምክር ቤት አባላት ጋር መቀመጥ የለባቸውም”፣ “በምትካቸው አዲስ አፈ ጉባኤ መሾም አለበት” የሚል ተቃውሞ ተነስቷል።

ፎቶ፦ የሶማሌ ክልል መገናኛ ብዙሃን 

አጀንዳ ሁለት እና ሶስት

ተቃውሟቸውን ስብሰባ ረግጠው በመውጣት የገለጹት የምክር ቤቱ አባላት በተጨማሪ አጀንዳነት እንዲመዘግብ የጠየቁት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን መቆጣጠር የተመለከተ ጉዳይን ነበር። ዶ/ር ኒምአን እንደሚሉት ራሳቸውን ጨምሮ ቁጥሩ በርከት ያለ የምክር ቤቱ አባል ይህ ጉዳይ እንዲካተት ለመጠየቅ እጅ ቢያወጡም እድል እንዳልተሰጣቸው እና ይህም እንዳበሳጫቸው ገልፀዋል። 

“ልክ በአብዲ ኢሌ ጊዜ እንደነበረው ነው የሆነው። ቫይረሱ ከተከሰተ ወዲህ የመጀመሪያ የምክር ቤቱ ስብሰባችን ነው፤ ይሄም ሆኖ የቫይረሱ ጉዳይ አጀንዳ አልነበረም” ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

ሶስተኛው አጀንዳ የክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳደር ሙስጠፌ መሃመድ ላይ “እምነት አጥተናል” ያሉ አባላት የመተማመኛ ድምጽ እንዲሰጥ የጠየቁበት ነው። በሙስጠፌ የሚመራውን ስራ አስፈፃሚ የሾመው የክልሉ ምክር ቤት በካቢኔያቸው ላይ “እምነት አለው ወይም የለውም” የሚለውን ለመወሰን ጥያቄው ቢቀርብም በአጀንዳነት ግን አለመያዙን የዓይን እማኞች ገልጸዋል።

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ለምን ይህ ጥያቄ ተነሳ የሚለውን ለማወቅ ያደረገችው ማጣራት እንደሚያሳያው ለወራት በምክር ቤቱ አባላት እና በክልሉ ከፍተኛ የስራ አመራሮች መካከል ከፍፍሎች መኖራቸውን ተረድታለች። የክልሉ ፕሬዘዳት አቶ ሙስጠፌ “የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸውን ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ሾመዋል” በሚል እና ከሙስና ጋር ስማቸው የሚነሳ ሰዎችን ተጠያቂ አላደረጉም የሚሉትን ጉዳዮች በተመለከተ በሁለት ጎራዎች መካከል ሰፊ የቃላት ምልልሶች ሲደረጉ መሰንበቱን ዶ/ር ኒምአንንም አረጋግጠዋል። 

በምክር ቤቱ የተከሰተው ውጥረት የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩትም ለመባባሱ ምክንያት ከሆኑ ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል የክልሉ ገዢ ፓርቲ ጉዳይ እንደሚገኝበት “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በክልሉ ካሉ ታማኝ ምንጮቿ ተገንዝባለች። የክልሉ ገዢ ፓርቲ ሶዴፓ የብልፅግና ፓርቲን በተቀላቀለበት ጊዜ የቀድሞው የፓርቲ አመራሮች በአብዛኛው አለመካተታቸው ቅራኔ መፍጠሩ ይነገራል። ይህም የተመረጡበትን ሂደት ያጠቃልላል። አንድ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር እንዳሉትም የብልፅግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኮሚቴ እና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በተወሰኑ ሰዎች ፍላጎት ተመርጠዋል ወይም በእርሳቸው ቃል “Hand-picked ናቸው” ።

እንደምጮቻችን ገለጻ ከሆነ አዳዲስ የተመረጡ የስራ አስፈጻሚ አባላት ላይ ቅሬታዎች ሲነሱ ቆይቷል። በአብዛኛው ከፍተኛ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው እና አዳዲስ ኣባላት ተመልምለው ወደ አገር አቀፉ የብልጽግና ፓርቲ መላካቸው በቀሪው የፓርቲ አባላት ዘንድ ቁጣን መቀስቀሱን ምንጮቻችን ያስረዳሉ።  

ፎቶ፦ የሶማሌ ክልል መገናኛ ብዙሃን 

በምክር ቤቱ የተነሳው ተቃውሞ ምን ይመስላል?

የዛሬው ጉባኤ ሲጀመር 181 ሰው መገኘቱን መቁጠራቸውን የሚናገሩት ዶ/ር ኒምአን ከዚህ ውስጥ “120 የሚሆኑት በተቃውሞ ረግጠው ወጥተዋል” ብለዋል። ምክትል አፈ ጉባኤዋ “ሶስት አጀንዳዎች ይጨመሩ የሚለውን ወደ ጎን ብለዋል” የሚል ተቃውሞ ተነስቶባቸዋል። የተጨማሪ አጀንዳዎች ጉዳይ ቸል ተብሎ ምክር ቤቱ ይዞት በቀረባቸው ስድስት አጀንዳዎች ላይ በተሰጠ ድምጽ “56 ድጋፍ ብቻ ማግኘቱን ቆጥሬ አረጋግጬያለሁ” ብለዋል ዶ/ር ኒምአን። 

“ከዚህ በኋላ የምትቃወሙ ወይም ድምፅ የማትሰጡ ተብሎ አልተቆጠረም። የምክር ቤቱ ሰራተኞች ቁጥሩን ለምክትል አፈ ጉባኤዋ ሄደው ነግረዋቸዋል። 156 ሰው አጀንዳውን ስለደገፈ ወደ ዝርዝር እንገባለን ሲባል 120 የምንሆነው አንድ በአንድ ስብሰባውን ጥለን ወጥተናል” ሲሉ ዶ/ር ኒምአን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።  

ከስብሰባው ሲወጡም በስምንት ፒክ አፕ ተሽከርካሪዎች የተጫኑ የልዩ ሃይሎች መምጣታቸውን እና ሶስት የምክር ቤቱ አባላት ላይ እና ጋዜጠኞች ላይ ድብደባ መድረሱን ዶ/ር ኒምአን ይናገራሉ። አብዲሽኩር የተባሉ የምክር ቤቱ አባል ከፍተኛ ድብደባ እንደደረሰባቸውም የሚገልጹት ዶ/ር ኒምአን የጋዜጠኞቹ የስራ መሳሪያዎቻቸውም ተነጥቀዋል ብለዋል።  

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ማረጋገጥ እንደቻለችው በቁጥጥር ስር ከዋሉት ጋዜጠኞች መካከል ባለቤትነቱ በቅርቡ የሴቶች እና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር ሆነው የተሾሙት የወ/ሮ ፊልሰን አብዱላሂ የሆነው የነበድ ቴሌቪዥን የካሜራ ባለሞያ ይገኙበታል። የቴሌቪዥን ጣቢያው ዋና ስራ አስፈጻሚ በነበድ ቲቪ የፌስቡክ ገፅ ላይ በስራ ላይ እያሉ የተያዙት ባለሞያ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል።

በሶስቱ አጀንዳዎች ላይ ተቃውሞ ካነሱት 40 የሚሆኑት ተመልሰው ወደ ስብሰባው የገቡ ሲሆን 80 የሚሆኑት ግን ጥለው መውጣታቸውን አንድ የዓይን እማኝ ይናገራሉ። ዶ/ር ኒምአን በበኩላቸው “ተመልሰው የገቡት በፀጥታ ሃይሎች ውክቢያ ሲሆን መግባታቸው ወይም ያለመግባታቸው ሳይሆን ስብሰባውን ረግጠው በመውጣት ተቃውሞ ማሰማታቸው ነው” ሲሉ ይከራከራሉ።

የዛሬውን የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ውሎ እና ተከሰቱ ስለተባሉ ሁኔታዎች የተጠየቁት የክልሉ የፀጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አብዱላሂ ሀሰን በምክር ቤት አባላት ዘንድ ያለመግባባቱን ተፈጥሮ እንደነበር አምነዋል። ሆኖም በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን የቀረበው “የተጋነነ ነው” የሚል እምነት አላቸው።    

“በአዲስ አበባ ካሉ ተቃዋሚዎች ጋር አብረው የሚሰሩ የምክር ቤቱ አባላት ያነሱት ረብሻ ነው። ስብሰባውን ረግጠው ከወጡት መካከል አብዛኛዎቹ ተመልሰዋል”

አቶ አብዱላሂ ሀሰን – የሶማሌ ክልል የፀጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ

“በአዲስ አበባ ካሉ ተቃዋሚዎች ጋር አብረው የሚሰሩ የምክር ቤቱ አባላት ያነሱት ረብሻ ነው። ስብሰባውን ረግጠው ከወጡት መካከል አብዛኛዎቹ ተመልሰዋል፣ ለጊዜው ማረጋገጥ ባልችልም ከ40 የማይበልጡት ናቸው የቀሩት እንጂ ቀሪዎቹ ወደ ስብሰባ ተመልሰው እየተሳተፉ ነው” ሲሉ ሃላፊው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። “ስብሰባውን አቋርጠው ከወጡትም ሆነ ሌላ ማንም ሰው በቁጥጥር ስር አልዋለም” ሲሉም ቀደም ሲል ጉዳዩን አስመልክቶ የወጡ መረጃዎችን አስተባብለዋል።

በምክር ቤት አባላት መካከል ያለመግባባቱን የፈጠሩት ሁለት አጀንዳዎች እንደነበሩ የገለፁት ምክትል ሃላፊው የመጀመሪያው የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ከስራ መደባቸው ላይ መልቀቅ መሆኑን አቶ አብዱላሂ አስረድተዋል። ሁለተኛው ያለመስማማት የፈጠረውን አጀንዳ ከመግለፅ ተቆጥበው “እኔ የምክር ቤት አባል ስላልሆንኩ የተፈጠረውን በሙሉ አልተከታተልኩም። ስብሰባው ሲጠናቀቅ ሪፖርት እስከሚቀርብ እየጠበቅኩ ነው” ብለዋል። ያለመስማማቱ በምክር ቤት ውስጥ እንጂ በሶማሌ ክልል ዋና መቀመጫ ጅግጅጋ ከተማ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መቀጠሉን አቶ አብዱላሂ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ማምሻውን ጉባኤውን ያጠናቀቀ ሲሆን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫም ዶ/ር ኒምአን አብዱላሂን ጨምሮ 12 የምክር ቤቱን አባላት ያለመከሰስ መብት አንስቷል። “ሁከት በመፍጠርና ሥርዐት አልበኝነት እንደሁም በሌሎች ወንጀሎች ተጠርጥረዋል” ያላቸውን ሰዎች ነው ያለመከሰስ መብታቸውን ማንሳቱን ያስታወቀው። 

አህመድ መሀመድ ላይሊ፣ አህመድ አዳን አህመድ፣ አብዲወሊ መሀመድ ፋራህ፣ አህመሀድ ሀሰን መሀመድ፣ ሻፊ አሺር፣ ነዲር ዩሱፍ ኣደም፣ አብዲረሳቅ አብዱላሂ በይሌ፣ ዩሱፍ ኢልሚ ኢሳቅ፣ አህመድ ሀሰን ኑር፣ ዩሱፍ አህመድ ሂርሲ፣ ኒምዓን አብዱላሂ ሀመሬ እና አብዱራህማን ኡራግቴ ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳ አባላት ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)